ፈልግ

ካርዲናል አዩሶ፥ “የሃይማኖት መሪዎች ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃን ለማስተዋወቅ ያግዛል”

ብፁዕ ካርዲናል ሚገል አንጄል አዩሶ፥ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥን “COP28” በማስመልከት በአቡ ዳቢ ካዘጋጁት ጉባኤ ቀደም ብሎ የዓለም ሃይማኖቶች መሪዎች ያካሄዱት ጉባኤ ወንድማማችነትን እና የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎችን ለማስተዋወቅ እና በጋራ ለመሥራት ዕድል እንደሚስጥ ለቫቲካን ኒውስ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ፥ በአቡ ዳቢ የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ የተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ማግሥት ለቫቲካን የዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት፥ ከዓለም የሃይማኖቶች መሪዎች ጋር ያካሄዱት ውይይት፥ በተለያዩ እምነቶች መካከል የጋራ ዓላማን ለማሳካት አንድነትን የሚያጎለብት በመሆኑ አወድሰውታል።

ጥቅምት 26 እና 27/2016 ዓ. ም. የተካሄደውን የዓለም ሃይማኖቶች መሪዎች ስብሰባን ያዘጋጀው የሙስሊም የሀገር ሽማግሌዎች ምክር ቤት ሲሆን፥ ድጋፍ ያደረጉትም የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝደንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን መሆናቸው ታውቋል።

በስብሰባው ከክርስትና፣ ከእስልምና፣ ከሂንዱ፣ ከቡዳ፣ ከጃይን እምነቶች እና ከሌሎች በርካታ ሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦች የመጡ ወደ 30 የሚጠጉ መሪዎች እና ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል። ስብሰባውን የተሳተፉ የዓለም ሃይማኖቶች መሪዎች እና ተወካዮች፥ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን “COP28” የተካፈሉ የመንግሥታት መሪዎች ምድራችንን ከጉዳት ለመጠበቅ ቆራጥ እርምጃን እንዲወስዱ በማሳሰብ የላኩትን መግለጫ በጋራ ፈርመዋል።

የዓለም ሃይማኖቶች መሪዎች በመግለጫቸው፥ የኢነርጂ ሽግግሮችን ማፋጠን፣ ምድርን መንከባከብ እና ከጥፋት መጠበቅ፣ ከተፈጥሮ ጋር ተስማቶ ለመኖር ወደሚያስችሉ ሞዴሎች እንዲሸጋገሩ እና ንጹህ ሃይልን በፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የተሻለ ዓለም ለመገንባት መሥራት

ብፁዕ ካርዲናል ሚጌል አዩሶ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ቅድስት መንበር ለፍጥረት ከምታደርገው እንክብካቤ በተጨማሪ የሰው ልጆችን ወንድማማችነት ለማስተዋወቅ በዓለም አቀፍ ደረጃ መሥራቷን ገልጸዋል።

“በልዩነት፣ በግጭት እና በሌሎች የተለያዩ ጉዳዮች ምክንያት በዓለም ውስጥ ችግሮች መከሰታቸውን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ሚጌል አዩሶ፥ አንድነትን ለማጎልበት ወደዚህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ መጥተናል” ብለዋል።

በጳጳሳዊ ምክር ቤት የሐይማኖት ተቋማት የጋራ ውይይት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ፕሬዝደንት ብጹዕ ካርዲናል ሚገል አንገል ኣዩሶ፥ የአየር ንብረት ለውጥ በማስመልከት የዓለም ሃይማኖቶች መሪዎች ያካሄዱት ጉባኤ፥ የተለያዩ ባህሎች፣ አገሮች እና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች ያሏቸውን ሕዝቦች አንድ አድርጎ ለአንድ ዓላማ እንዲሠሩ ከማድረጉ በላይ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጥፋት በመጠበቅ እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ውስጥ ባሉ የሃይማኖት መሪዎች አስተባባሪነት ሊወሰዱ የሚችሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን በማቀድ የተሻለን ዓለም ለማስተዋወቅ ጥረት አድርጓል” ብለዋል።

 

 

 

09 November 2023, 16:13