ፈልግ

ሊቀ አቡነ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በደቡብ ኮርያ እና በቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ 60ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲምፖዚዬም ሊቀ አቡነ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በደቡብ ኮርያ እና በቅድስት መንበር ዲፕሎማሲ 60ኛ ዓመት መታሰቢያ ሲምፖዚዬም 

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ ዲፕሎማሲ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተስፋ መሣሪያ እንደሆነ ገለጹ

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ዋና ጸሐፊ ሊቀ አቡነ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ በደቡብ ኮርያ እና በቅድስት መንበር መካከል ግንኙነት የተጀመረበትን 60ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ደቡብ ኮርያን ጎብኝተው፥ በሀገሪቱ እና በቅድስት መንበር መካከል የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት 60ኛ ዓመት በዓል ላይ ተገኝተው ሲምፖዚየሙ ተካፋዮች ንግግር አድርገዋል። የቅድስት መንበር የመንግሥታት እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ በኮርያ ባሕል 60 ቁጥር ልዩ ትርጉም እንዳለው በመግለጽ በጀመሩት ንግግር፥ ወደ አዲስ የሕይወት ዑደት እና ወደ ሙሉ ምዕራፍ መሸጋገርን የሚገልጽ ነው" ብለው፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም ይህ ቁጥር ሙሉ ፍጻሜ ለማግኘት የሚደረግ ዝግጅትን የሚያመለክት፣ የመደጋገፍ እና የመተሳሰብ ሃሳብን የሚገልጽ ነው" ብለዋል።

ትዝታ እንደ ምስጋና

ሊቀ ጳጳስ ጋላገር በንግግራቸው፥ ይህ 60ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በኮርያ መንግሥት እና በብጹዓን ጳጳሳት የተደገፈ የታሪክ ጥናት እና ጥበቃ ፕሮጀክት መጠናቀቁን አስታውሰዋል። ፕሮጀክቱ በቫቲካን ሐዋርያዊ ቤተ መዛግብት፣ በሐዋርያዊ ቤተ መጻሕፍት እና በሴኡል የሚገኘው የጳጳሳዊ እንደራሴ ሰነዶችን ይመለከታል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር በደቡብ ኮርያ ውስጥ ሦስት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝቶች መካሄዳቸውን አስታውሰው፥ የመጀመሪያው እና ሁለተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1984 እና በ1989 ዓ. ም. ካደረጓቸው ጉብኝቶች በተጨማሪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 ዓ. ም. ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደ ነበር በማስታወስ፥ የኮርያ ርዕሠ መስተዳድሮች በስልሳ ዓመታት ታሪክ ውስጥ በቫቲካን ያደረጓቸውን ጉብኝቶች ገምግመዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2000 ዓ. ም. ኪም ዴ ጁንግ እና ሙን ጃኢን በ2018 እና 2021ዓ. ም. ያደረጓቸውን ጉብኝቶች አስታውሰው፥ ወንጌል በደቡብ ኮርያ በከፍተኛ ጥንካሬ ሥር መስደዱን ሊቀ ጳጳስ ጋላገር ገልጸዋል።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ደቡብ ኮርያ የተልዕኮ ምድር በመሆን ለብዙ ሚስዮናውያን የመነሻ አገር እንደሆነች። የምርምር ፕሮጀክቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1948 ዓ. ም. ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሮንካሊ ለደቡብ ኮርያ የልዑካን ቡድን እና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዑካን ቡድን የሰጡትን ዕርዳታ የሚገልጹ ሠነዶች በቁፋሮ መገኘታቸውን ገልጿል።

የቤተ ክርስቲያን እና ዲፕሎማሲ የተስፋ ምልክቶች

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር ቀጥለውም፥ ያለፈውን ታሪክ መጠበቅ እና ማስታወስ ምን ያህል የወደ ፊት ተስፋዎች እና ተግዳሮቶች ለመጋፈጥ እንደሚያስችል ገልጸው፥ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ፍሬን የሚሰጥ ተግባር ሊሆን እንደማይችል አጽንኦት ሰጥተዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “አልፎ አልፎ የሚታዩ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት” ብለው የሚጠሩትን የጠቀሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር፥ እንደ የጦር መሣሪያ ውድድር፣ የኒውክሌር ሥጋት እና ሽብርተኝነትን የመሳሰሉ ክስተቶች ባሉበት ሁኔታ፥ ቤተ ክርስቲያን እና የዲፕሎማሲው መዋቅር አንድ ላይ መሆን እንዳለባቸው ገልጸው፥ የተስፋ ምልክት ማለትም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ ጦርነቶችን በውይይት መስወገድ እንደሚቻል የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በዚህ አተያይ፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዲፕሎማሲ፥ የሰው ልጅ አብሮ እንዲኖር የሚስችል መሣሪያ እና በሁሉም አጋጣሚዎች የመረጋጋት፣ የደኅንነት እና የሰላም የጋራ ምኞትን የሚያረጋግጥ ድምጽ” እንደሆነ ገልጸው፥ ሰላም በሃይል ሚዛን የሚመጣ ሳይሆን በፍትህ ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ሰላም መሆን አለበት ብለዋል።

በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ዋና ጸሓፊ ሊቀ ጳጳስ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ በቅድስት መንበር እና በደቡብ ኮርያ መካከል “በአሁኑ እና በወደፊቷ ዓለም በተለይም በምሥራቅ እስያ ክልል የሚያጋጥሙትን ታላላቅ ፈተናዎች በመጋፈጥ ትብብር እየጨመረ እንደሚሄድ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

22 November 2023, 15:42