ፈልግ

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ገጽታ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ገጽታ  

ቫቲካን ለሥራ ፈለጊዎች የሚያገለግል የማመልከቻ ማስገቢያ አዲስ ድረ-ገጽ አስተዋወቀ

የቫቲካን የምጣኔ ሃብት ጽሕፈት ቤት የተለያዩ የሥራ መደቦችን በመጥቀስ መመዝገብ የሚፈልጉ የሥራ ፈላጊዎች ማመልከቻን ለመቀበል የሚያስችል አዲስ ድረ-ገጽ አስተዋውቋል። "ከእኛ ጋር ይሥሩ" በሚል ስያሜ ይፋ የሆነው ድረ-ገጹ፥ በተለያዩ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶች ተቀጥረው ከሚሠሩ ምእመናን በተጨማሪ ሌሎች ምዕመናንም የትምህርት ማስረጃቸውን አቅርበው ይፋ በሚደረጉ የሥራ መደቦች መወዳደር እንደሚችሉ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቫቲካን የምጣኔ ሃብት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ማክሲሚኖ ካባሌሮ ሌዶ እንዳብራሩት፥ በኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ ባለው ማዕከላዊ ጭብጥ፥ ሠራተኞችን በተመለከተ ከማሻሻያ መንገዶች መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት ማሻሻያውን ተግባራዊ ለማድረግ እና ተልዕኮውን ለመወጣት እንደሆነ የገለጹት የጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፥ በቅድስት መንበር ተገቢ ብቃት፣ ተነሳሽነት እና ከሁሉም በላይ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች ያስፈልገናል ብለዋል።

"አንድ ሰው በቅድስት መንበር እንዴት ሊቀጠር ይችላል? ምን ዓይነት የሥራ ዘርፎች አሉ?" ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ የሰጡት የቅድስት መንበር የሰው ሃብት ክፍል ዳይሬክተር አቶ ሉዊስ ሄሬራ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀው 'ከእኛ ጋር ይሥሩ' በሚለው ድረ-ገጽ በኩል መልስ ማግኘት እና ማወቅ እንደሚቻል ተናግረዋል። ክፍት የሥራ መደቦች እና አስፈላጊው የእጩዎች መመዘኛ መረጃዎች በድረ-ገጹ ላይ መገለጹን ተናግረው፥ ፍላጎት ያለው ማንኛውም ሰው ማመልከቻውን በድረ-ገጹ በኩል ማቅረብ እንደሚችል አስረድተዋል።

የማመልከቻ ሂደትን ቀላል ማድረግ

በቫቲካን የምጣኔ ሃብት ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው፥ ሁሉም ሰው በተለይም ፍላጎት ያደረበት ሰው ወደ ድረ-ገጹ በመግባት የሚፈለጉ የሥራ መደቦችን ማወቅ እንደሚችል፣ ለዚህ የተለየ ሚና እና እውነተኛ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች መምረጥ እንደሚቻል ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል።

በቅድስት መንበር የሰው ሃብት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሉዊስ ሄሬራ፥  ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች እና ቢሮዎች ልዩ ልዩ ባለሙያዎችን ለምሳሌ የቋንቋ ወይም የቴክኒክ ክህሎት ያላቸውን ሰዎች ማግኘት ቀላል እንዳልነበረ ገልጸው፥ አዲሱ ድረ-ገጽ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ግንኙነት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል። ለቦታው ተስማሚ የሚሆን ሰው እስከሚያገኝ እና የሥራ መደብ ይፋ እስከሚደረግ ድረስ ተወዳዳሪዎች የትምህርት ማስረጃን በድረ-ገጹ በኩል አስገብተው መጠበቅ እንደሚችሉ አቶ ሉዊስ ተናግረዋል። "ከእኛ ጋር ይሥሩ" የሚለው ድረ-ገጹ በቅድስት መንበር ውስጥ በሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ተቀጥረው ለመሥራት ፍላጎት ላላቸው ምእመናን የተሰጠ ክፍል ሲሆን ከቫቲካን ውጭ ያሉ እጩዎችንም ለመቀበል ያለመ እንደሆነ አክለው አስረድተዋል።

የውስጥ ተንቀሳቃሽነት

ከዚሁ ጎን ለጎን የምጣኔ ሃብት ጽሕፈት ቤቱ የውስጥ እንቅስቃሴን ለማስፋት እየሠራ ሲሆን፥ የሥራ መደብ ክፍት በሚሆንበት ጊዜ ማስታወቂያው ቶሎ እንዲደርስ ለማድረግ፥ በቅድስት መንበር መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያለውን ግልጽነት ለማረጋገጥ፥ አዲሱ የምጣኔ ሃብት ጽሕፈት ቤት ድረ-ገጽ በጽሕፈት ቤቱ ተግባራት እና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ላይ ካለው መረጃ በተጨማሪ በኢኮኖሚያዊ እና ፋይናንስ ጉዳዮች ላይ የቁጥጥር እና አስተዳደራዊ ሕጎችን ለማቅረብ እንደሚያግዝ ታውቋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት ወር 2020 ዓ. ም. የጸደቀው የቅድስት መንበር እና የቫቲካን ከተማ የቅጥር ውሎች ግልጽነት፣ የቁጥጥር እና የውድድር ሂደቶች ላይ ያሉ ደንቦችን ተርጉሞ ተግባራዊ ያደርጋል።

 

25 October 2023, 16:52