ፈልግ

መስከረም 26/2016 ዓ. ም. የቀረበ የሲኖዶስ ጉባኤ መግለጫ መስከረም 26/2016 ዓ. ም. የቀረበ የሲኖዶስ ጉባኤ መግለጫ 

ሲኖዶሳዊነት፥ ጽንሰ ሐሳብ ሳይሆን የመደማመጥ እና የአንድነት ልምድ መሆኑ ተገለጸ

ቫቲካን ውስጥ ከመስከረም 23/2016 ዓ. ም. ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኘው 16ኛው የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ፥ ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ. ም. ያካሄደውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ መግለጫ አውጥቷል። ጠቅላላ ጉባኤው በመግለጫው፥ ሲኖዶሳዊነት ጽንሰ ሐሳብ ሳይሆን የመደማመጥ እና የአንድነት ልምድ መሆኑ ገልጾ፥ በማከልም የግል አስተያየቶቻቸውን የሚገልጹበት ሳይሆን ነገር ግን የሚረዱበት እና ወደ እግዚአብሔር ዘንድ አብረው የሚጓዙበት ቦታ እንደሆነ አስረድቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ቤተሰብ፣ ሲኖዶሳዊነት፣ መደማመጥ፣ ኅብረት፣ ድሆች፣ ወጣቶች፣ ማኅበረሰብ እና ፍቅር የሚሉት ቃላት የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ የተግባር ሠነዱን የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲደመድሙ የተወያየባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መሆናቸው ታውቋል። በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በመግለጫቸው፥ የጉባኤው የመጀመሪያ ቀናት ተሳታፊዎች የቤተ ክርስቲያኗን የተለያዩ ገፅታዎች ተመልክተው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስጋናቸውን ያቀረቡባቸው ቀናት እንደነበሩ ተናግረዋል።

የሥራ ቡድኖች ሪፖርቶች

መስከረም 26/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ከተካሄደው ሦስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ አስቀድሞ በትናንሽ የሥራ ቡድኖች ጠዋት በነበረው ክፍለ ጊዜ ውይይቶች ተካሂደዋል። ውይይቱ በዋናነት ቡድኖቹ ባከናወኗቸው ሥራዎችን ላይ የቀረቡትን ሪፖርቶች በማጠናቀቅ ላይ ያተኮረ ሲሆን እያንዳንዱ ቡድን ከ10-12 አባላትን ያቀፈ እና ሲሆን ይህም የወንድማማችነት ተወካዮችን የሳተፈ እንደ ነበር ተመልክቷል። በእያንዳንዱ ቡድን ውስጥ በአብላጫ ድምፅ የጸደቁት ሪፖርቶቹ ለሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ከቀረቡ በኋላ በቀጣይነትም በትልቁ ጉባኤ ላይ በሚቀርብ ሠነዱ ውስጥ ተካትተው ውይይት የሚደረግበት እንደሚሆን ታውቋል።

የሪፖርቶቹ ጭብጦች

በሪፖርቶቹ ውስጥ ከተካተቱት ጭብጦች መካከል፥ ለካኅናት እና ለዘርዓ ክህነት ተማሪዎች በየደረጃው የሚሰጡ ስልጠናዎች፥ በቤተሰብ አባላት ውስጥ በተጠመቁት ሁሉ መካከል ያለውን የጋራ ኃላፊነት እና የሐዋርያዊ አገልግሎት ተዋረድ በኅብረት ውስጥ እራሱን እንዴት ማስቀመጥ እንደሚችሉ የሚገልጹ ጭብጦች ያለበት እንደነበር ተመልክቷል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ሲኖዶሳዊነት የሚለውን ቃል ከቃል አንፃር በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲቃኙት ተጠይቀዋል። በዚህም የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮች ቢሮክራሲነትን መግታት ብቻ ሳይሆን አዳዲስ ቅርጾችን እና አዳዲስ የኅብረት ተሳትፎዎች በቤተ ክርስቲያኒቷ የሺህ ዓመት ታሪክ ውስጥ ለማጤን ኃይል የመስጠት አስፈላጊነት በጉልህ ተመልክቷል።

ወጣቶች እና የዲጂታሉ ዓለም እውነታ

ወጣቶችን የማሳተፍ አስፈላጊነት ላይ ትኩረት የሰጠ ሲሆን፥ ሪፖርቶቹ የዘመናዊ ዲጂታል እውነታን በማጤን፣ ከስልጣን ጽንሰ-ሀሳብ ወደ አገልግሎት በመሸጋገር ማንኛውንም ዓይነት የቤተ ክህነት ገናናነትን በማስወገድ ላይ ያተኮሩ እንደ ነበር ተመልክቷል። እንዲሁም ምእመናን እና ሴቶች በቤተ ክርስቲያን አንድነት ውስጥ ስላላቸው ሚና እና ቤተ ክርስቲያን እራሷን ለድሆች እና ለስደተኞች አገልግሎት እንዴት እንደምታቀርብ የሚጠይቁ ጥያቄዎች ያሉባቸው እንደ ነበር ተመልክቷል። ሲኖዶሱ ቀጥሎም ቤተ ክርስቲያን በሁለት “ሳንባዎች” ማለትም በምሥራቅ እና በምዕራብ ቤተ ክርስቲያናት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር ታውቋል።

የሲኖዶሱ መሪ እና እረኛ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ናቸው

በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በሰጡት መግለጫ፥ ቅዳሜ መስከረም 26/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ የተካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤን ከተካፈሉት መካከል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አንዱ እንደነበሩ ገልጸው፥ ቫቲካን ውስጥ የተገኙት የሚዲያ ባለሙያዎች የሲኖዶሱን ጠቅላላ ጉባኤ ሂደት በማስመልከት ላሳዩት የማብራሪያ መንገድ ቅዱስነታቸው ምስጋና ማቅረባቸውን ዶ/ር ሩፊኒ ተናግረዋል። ቅዳሜው መስከረም 26/2016 ዓ. ም. በቀረበው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፥ የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ እህት ሌቲሲያ ሳላዛር፣ በሰሜን አሜሪካ የቅዱስ ቤርናርዲኖ ሀገረ ስብከት የጠቅላላ የሲኖዶስ ሂደት ምስክር እና የጠቅላላ ሲኖዶሱ የማስታወቂያ ኮሚሽን ጸሐፊ ወ/ሮ ሺላ ፒሬስ መገኘታቸው ታውቋል።

ለዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈለግ

የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፥ ይህ አራተኛው የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ልምዳቸው መሆኑን በመጥቀስ፥ ይሄኛው ጉባኤ ካለፉት ጉባኤዎች እንዴት እንደሚለይ ገልጸው፥ “በዚህ አጋጣሚ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ አሁን ባለንበት ታሪካዊ ወቅት ለእግዚአብሔር ፈቃድ ፍለጋ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል” ብለዋል።

“ጫናን የማሳደር አጀንዳን ይዞ የመጣ ማንም የለም” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ፥ “እኛ ወንድሞች እና እህቶች እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ ያለውን ፈቃድ እያዳመጥን፥ ሲኖዶሱ የሚያፈራው መልካም ፍሬ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ተቀባይነት ይኖረዋል” ብለዋል። ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ በማከልም፥ ለመንፈስ ቅዱስ በመገዛት እርሱን በማዳመጥ ቦታ እራሳችንን ማስቀመጥ ያስፈልጋል” ብለዋል። የዚህ ጉዞ ግብ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ እስከ 2024 ዓ. ም. ድረስ ለተወሰኑ ችግሮች የተሻለ መልስ መፈለግ እንደሆነ ተናግረው፥ ውጤቱም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የተቀራረበ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የጸሎት አስፈላጊነት

ያለ ጸሎት ሲኖዶሳዊነት የለም ሲሉ ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቀጥለውም፥ "እንደ ቤተ ክርስቲያን ሳናቋርጥ በማስተዋል ሂደት ውስጥ ዘወትር እንገኛለን" ብለው፥ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሲመልሱ፥ የሲኖዶሳዊ ጉባኤ ሂደትን ለማክበር ሲባል እና የሪፖርቱን አንደኛውን ክፍል ብቻ ማጤን፥ ከሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ የአካሄድ ሥርዓት ውጭ መውጣት እንደሚሆን ተናግረው፥ ከትናንሽ የውይይት ቡድኖች የቀረቡት ሪፖርቶች ወዲያ እንደማይታተሙ ነገር ግን የሁሉም ሪፖርቶች ውህደት ሠነድ ወደ ፊት እንደሚታተም አስረድተዋል።

“ሲኖዶስን የሚወስነው ወይም ጉባኤን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት አይደለም” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን፥ በውይይት ቡድኖች እና በጠቅላይ ጽ/ቤቱ መካከል የጋራ መስተጋብር መኖሩን ገልጸዋል። ከዚህም በላይ እያንዳንዱ ተሳታፊ ሥልጣን የሚያገኘው ከጳጳሳዊ ሹመት ሳይሆን በጥምቀት ከተሰጠው ጸጋ እንደሆነ አስረድተዋል። በዚህም ረገድ ጉባኤን በመካፈል ላይ ከሚገኙት 364 ጠቅላላ አባላት መካከል ሹመት የሚሰጣቸ 52 አባላት መሆናቸውን ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ አስታውሰዋል።

ችግሮችን ለማየት የሚያግዝ አዲስ መንገድ

ተመሳሳይ ጾታ ጉዳይን በማስመልከት በጉባኤው ላይ የተነሱ ርዕሠችን እንዴት እንደሚመለከቷቸው የተጠየቁት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን፥ በቫቲካን የተገኙት በሲኖዶሳዊነት ላይ የሚካሄደውን የሲኖዶስ ጉባኤን ለመካፈል እንደሆነ በመናገር ከሲኖዶሳዊነ ርዕሥ መውጣት እንደማይፈልጉ ገልጸዋል። ሲኖዶሳዊነት ማለት የግል አስተያየቶችን መግለጽ ሳይሆን እግዚአብሔር ወደ ሚጠብቀን ሥፍራ ለመድረስ በኅብረት መጓዝ እንደሆነም ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አስረድተው፥ “በተመሳሳይ ጾታ ጉዳይ ላይ እግዚአብሔር ራሱ በጋራ የማስተዋል አቅጣጫውን ያሳየናል” ብለዋል።

በተጨማሪም፣ በተለይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ይሚያግዙ አዳዲስ የአሠራር ዘዴን ለመፈለግ ካለመው የሲኖዶስ ጉባኤ የሚጠበቀውን የተጋነነ ነገር ሕዝቡ እንዲቀንስ በማለት የአፍሪካ እና ማዳጋስካር ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ሲምፖዚየም ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ አሳስበዋል።

 

09 October 2023, 17:49