ፈልግ

ለሲኖዶስ ጉባኤ ተካፋዮች ማብራሪያ ሲሰጥ ለሲኖዶስ ጉባኤ ተካፋዮች ማብራሪያ ሲሰጥ 

ቤተ ክርስቲያን እጅግ ውብ የምትሆነው በሮችዋን የበለጠ ስትከፍት እንደሆነ ተገለጸ

በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ የሲኖዶስ ጉባኤን ሂደት በማስመልከት ለጋዘጤኛች ማብራሪያ ሰጥተዋል። ማክሰኞ መስከረም 29/2016 ዓ. ም. ለጋዜጠኞች ባደረጉት ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ንዑሥ የሥራ ቡድኖችን ውይይት በማስመልከት ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ከእርሳቸው ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የአሜርካው ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ቶቢን የተለያዩ ልምዶችን እና ባሕሎችን በማነጻጸር ሊያበርክቱ የሚችሉትን ሃብት ከተናገሩ በኋላ፥ ከኮሎምቢያ የመጡት እህት ኢቼቨሪ፥ የድሆችን ጩኸት የማዳመጥ ጥሪን በተመለከተ አጽንዖትን ሰጥተው ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በአሜሪካ የኒው ዮርክ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ጆሴፍ ዊሊያም ቶቢን፥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ውበት የሚገለጸው በሮቿን የበለጠ ክፍት በማድረግ ሰዎችን ስትቀበል እንደሆነ ገልጸው፥ ቤተ ክርስቲያን በሮችዋል የበለጠ ክፍት እንድታደርግ ይህ ሲኖዶስ እንደሚያግዛቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። ንዑስ ቡድኖቹ ሰኞ መስከረም 28 ጠዋት እና ማክሰኞ መስከረም 29/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ በማትኮር፥ በግልጽ የሚታይ የቤተ ክርስቲያን ኅብረት በሚለው ርዕሥ ሥር፥ “ከእግዚአብሔር እና ከሰው ልጆች ሁሉ ጋር የአንድነት ምልክት እና መሣሪያ እንዴት መሆን እንችላለን?” በሚለው ሃሳብ ላይ ውይይት አድርገዋል።

ንዑሥ ቡድኖች በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ

የጠቅላላ ጉባኤው ንዑሥ ቡድኖች፥ በትምህርት፣ በአካባቢጥበቃ እና እንክብካቤ፣ በባሕል ብዝሃነት እና በኅብረተሰቡ ከተገለሉት እና ከስደተኞች ጋር በኅብረት መጓዝ በሚሉት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል። ከዚህም በተጨማሪ አጭር ሪፖርቶችን የሚያቀርቡ የኮሚሽኑን አባላት መርጠዋል። ውይይት በሚደረግባቸው መሪ ሃሳቦች ላይ በመመሥረት የተዋቀሩ ንዑሥ ቡድኖች በሁለተኛው ምዕራፍ ንኡሳን ክፍሎች ኅብረትን በማስመልከት ከተወያዩ በኋላ ማክሰኞ ከሰዓት በኋላ በአምስተኛው፣ በስድስተኛው እና በሰባተኛው ጠቅላላ ጉባኤዎች ላይ አስተያየታቸውን አቅርበዋል።

በሁሉም ተሳታፊዎች መካከል ታላቅ መጋራት ነበር

ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት፥ በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ሦስተኛቸው በሆነው በዚህ የሲኖዶስ ጉባኤ አባላቱ ሃሳባችውን የሚገልጹባቸው ብዙ ዕድሎች መኖራቸውን ገልጸው፥ በተለይም በንዑሥ ቡድኖች ውስጥ ለታዩት ዕድሎች አፅንዖት ሰጥተዋል። "በግል ተሞክሮዬ መሠረት በሁሉም የጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ታላቅ መጋራት አለ" ሲሉ የተናገሩት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ይህ መታየት የጀመረው ከቅድመ ሲኖዶስ እንደ ነበር ገልጸዋል። ብፁዕ ካርዲናል ቶቢንም በኩላቸው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ “ጉባኤው ከላይ ወደ ታች የተመራ ሳይሆን ነገር ግን ጠቅላላ ሂደቱ ከሥር ከምዕመናን ተሳትፎ የጀመረ በመሆኑ ውጤታማ ስለመሆኑ እርግጠኞች ነን” ብለው፥ “በመሆኑም የታሰርኩ ወይም የታፈንኩ መስሎ አይታየኝም” ብለዋል።

የድሆችን ጩኸት እናዳምጣለን

የሲኖዶሱ ጽሕፈት ቤት መደበኛ ምክር ቤት አባል ከሆኑት ከብፁዕ ካርዲናል ቶቢን በተጨማሪ፥ የላቲን አሜሪካ ገዳማውያት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዝደንት እና የረዳት እመቤታችን ማርያም ማኅበር አባል የሆኑት ኮሎምቢያዊት እህት ግሎሪያ ሊሊያና ፍራንኮ ኢቼቬሪ በመግለጫው ላይ ተገኝተው የሲኖዶሱን ሂደት በማስመልከት ምስክርነታቸው ያቀረቡ ሲሆን፥ ሂደቱ በማስመልከት በሰጡት ምስክርነት፥ በ16ኛው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች መካከል እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ የመኖር ፍላጎት መኖሩን ተናግረው፥ “ሰውን የሚያደርግ፣ የሚያከብር፣ አንድ የሚያደርግ እና ለሌላው በር የሚከፍት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመንፈስ ቅዱስ በመመራት የመናገር ልዩ ዘዴን መሠረት በማድረግ የተጀመረው የሲኖዶሱ ጉባኤ በንዑሥ ቡድኖች ውስጥ የጋራ ክብርን፣ ከመግባባት የሚገኝ መከባበርን እና የጋራ እውቅና በመስጠት የሚገኝ ኅብረትን በትክክል እንገነዘባለን” በማለት እህት ኢቼቬሪ ተናግረዋል። በሁለተኛው ምዕራፍ ላይ በተደረገው ውይይት፥ “ልባችን ውስጥ የድሆችን ጩኸት እንድንሰማ የሚጎተጉተን ጥሪ አለ” ያሉት እህት ኢቼቬሪ፥ በውይይታቸው ላይ፥ የድሆች ስቃይ፣ ስደት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር እና ከማኅበራዊ ሕይወት መገለል የሚሉ ድምጾች ጎልተው ይሰሙ ነበር” ብለዋል።

በባሕሎች መካከክ የሚደረግ ውይይት ማራኪነት

ከእህት ኢቼቬሪ ጋር በተመሳሳይ ንዑሥ ቡድን ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ቶቢን፥ ቡድናቸው ውስጥ ከሩሲያ የመጣች ወጣት፣ ከዩክሬን የመጡ እናት፣ ከጋና የመጡ ጴንጤቆስጣዊ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ፣ ከማሌዢያ የመጡ የነገረ መለኮት መምህር እና ከሲንጋፖር የመጡ የቡድኑ አስተባባሪ እንደሚገኙበት ገልጸው፥ “በእንደዚህ ዓይነት የተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ሆኖ እና ሌሎችን ማዳመጥ መቻል መልካም ዕድል ነው” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በአሜሪካ የባሕል ብዝሃነት በሚታይባት ዲትሮይት ግዛት ውስጥ ማደጋቸውን እና ለ45 ዓመታት በክኅነት አገልግሎት መቆየታቸውን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ቶቢን፥ የራሳቸው ባልሆኑ ባሕሎች መካከል መኖር ዘወትር ያስደንቃቸው እንደ ነበር ተናግረው፥ ይህ የሲኖዶስ ጉባኤም ከዚህ በፊት ያልተሳተፉበት ልዩ ሲኖዶስ እንደሆነ ገልጸዋል።

በቤተ ክርስቲያን የወንድማማችነት ምርጫ ውስጥ ለሁሉም ቦታ አለው

ብፁዕ ካርዲናል ቶቢን ወደ ኒውአርክ ካቴድራል ለንግደት በሚመጡ ሰዎች መካከል በጾታዊ ዝንባሌያቸው ምክንያት የተገለሉ ሰዎች መኖራቸውን እንደተመለከቱ ገልጸው፥ በቡድናቸው ውስጥ አንድ ካኅን፥ “ይህች ቤተ ክርስቲያን ውብ ናት ነገር ግን በሮችዋ ሲከፈቱ ይበልጥ ታምራለች” ማለታቸውን አስታውሰዋል።ብፁዕ ካርዲናል ቶቢን በመግለጫቸው ማጠቃለያ፥ በአግላይ ብሔርተኝነት፣ በጭፍን ጥላቻ፣ ድንበር ለመፍጠር የሚተጉ መሪዎች ባሉበት ዓለም ውስጥ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው የወንድማማችነት ምርጫ እና ሲኖዶሳዊነት፥ ሁላችንም ወንድማማቾች እና እህትማማቾች መሆናችንን እንድንረዳ የሚያስችለን አማራጭ ነው” ብለው፥ "እራሳችንን እንደ ወንድሞች እና እህቶች በምንመለከትባት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሁሉም ሰው ቦታ አለው" በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

 

 

11 October 2023, 17:31