ፈልግ

በቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽ/ቤት ስለ ሲኖዶሱ ውይይቶች ማብራሪያ ሲሰጥ  በቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽ/ቤት ስለ ሲኖዶሱ ውይይቶች ማብራሪያ ሲሰጥ   (Vatican Media)

ሲኖዶሳዊነት የማይደጋገም አዳዲስ የዕለት ተዕለት ልምድ መሆኑ ተገለጠ

በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘው 16ኛ የሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ፥ ሰኞ ጥቅምት 5/2016 ዓ. ም. ጠዋት፥ ሚሲዮናዊነት፣ የሃይማኖቶች የጋራ ውይይት እና ሴቶች በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ያላቸው ሚናን በሚሉት ርዕሦች ላይ ከተወያየ በኋላ ከሰዓት በኋላ በቀረበው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ውይይት በተደረጉባቸው ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ጉባኤው ከዚህም በተጨማሪ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና 45ኛ ዓመታቸውን አስታውሷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሲኖዶሳዊነትን ትክክለኛ ትርጉም፣ የብዝሃነት ሃብት፣ የተጠመቁት ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸው ሚና፣ የሚስዮናውያን አገልግሎት፣ የክርስቲያኖች የአንድነት እንቅስቃሴ እና የሃይማኖቶች የጋራ ውይይት፣ የሴቶች የድቁና አገልግሎት እይታ እና የዲጂታል ዘመን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም የማይችሉ የድሃ አገራት ወጣቶች የሚሉት ርዕሠ ጉዳዮች ሰኞ ጥቅምት 5/2016 ዓ. ም. በጉባኤው ከተነሱት የሲኖዶሱ የተግባር ርዕሦች መካከል ጥቂቶቹ እንደነበሩ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ጽ/ቤት ለጋዜጠኞች በሰጠው ማብራሪያ አስታውቋል።

የመጀመሪያዎቹ ሪፖርቶች ታይተዋል

በጉባኤው ላይ ከንዑሥ ቡድኖች የቀረቡ የመጀመሪያዎቹ ሪፖርቶችም መታየታቸውን በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ አብራርተዋል። የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ለሕጻኑ ኢየሱስ ቅድስት ተሬዛ መታሰቢያ እንዲሆን በማለት “በእግዚአብሔር መሐሪ ፍቅር መታመን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸውን ይፋ በማድረጋቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን አመስግነዋል።

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በተጨማሪም ጥቅምት 5/2016 ዓ. ም. የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ሥልጣን የተቀበሉበት 45ኛ ዓመት መታሰቢያ እና አንዳንድ ካህናትም የክህነታቸውን መታሰቢያ የሚያከብሩበት ዕለት መሆኑን ለጉባኤው ተካፋዮች ተናግረው የጉባኤው አባላትም ደስታቸውን በጭብጨባ ገልጸዋል። ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ አክለውም፥ እስካሁን የተጓዙትን የሲኖዶሱ ሂደት፥ የማዳመጥን ጥራት እና ውበት በማስመልከት የሲኖዶስ ንዑሥ ኮሚቴ ዓርብ ጥቅምት 2/2016 ዓ. ም. ያቀረበውን ሪፖርት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ሲኖዶሳዊነት የማይደጋገም ልምድ ነው

ሰኞ ጥቅምት 5/2016 ዓ. ም. ለጋዜጠኞች በተሰጠው የማብራሪያ ዝግጅት ላይ ከነበሩት እንግዶች መካከል በስሪላንካ የነገረ መለኮት ምሁር የሆኑት አባ ቪማል ቲሪማና የተገኙ ሲሆን፥ አባ ቪማል፥ “ሲኖዶሳዊነት የሚገለጸው በተግባር ሲያከናውኑት ነው” የሚለው ሃሳብ መሠረት በማድረግ፥ በታላቅ የጸሎት ድባብ ውስጥ ምስጋናን በማቅረብ፣ በመንፈሳዊ የውይይት ዘዴ በመታገዝ፣ የሲኖዶሱን ሂደት ወይም ሲኖዶሳዊ የአኗኗር ዘይቤ በተግባር ስንኖር ቆይተናል ብለዋል። አባ ቲሪማና በማከልም፥ ካርዲናሎች፣ ጳጳሳት እና ምእመናን በንዑሥ ቡድኖች ተመድበው በጠረጴዛዎች ዙሪያ መወያየታቸው ሲኖዶሳዊነትን እንዴት እንደሚገልጽ ተናግረው፥ በተለይም የሴቶችን ልምድ በማጉላት፥ ሲኖዶሳዊነት ከላይ ወደ ታች በሚለው የአስተዳደር ዘይቤ የሚገለጽ ሳይሆን አንድ ላይ በተሰበሰበች እና የሕዝቦች ብርሃን በሆነች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እርስ በርስ በመደጋገፍ የመኖር ልምድ እንደሆነ አስረድተዋል። አባ ቲሪማና ቀጥለውም የሲኖዶሱ ሂደት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የግል አጀንዳ ሳይሆን የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ቀጣይ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ጸሎት እና ዝግጅት ማድረግ

ዓለም አቀፉ የገዳማውያት የበላይ አለቆች ሕብረት ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት እህት ፓትሪሲያ መሬይ፥ ሲኖዶሳዊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እውን እየሆነ ሲመጣ ማየታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረው፥ የገዳማውያት ጉባኤ አባል እንደመሆናቸው ሲኖዶሳዊነትን ከሃያ ዓመታት በላይ በተግባር ሲገልጹት እንደቆዩ፥ በተለይም ውሳኔዎችን ሲያደርጉ እና በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች መደምደሚያ ላይ ሲደርሱ መቆየታቸውን ገልጸዋል። 

ኢየሱስ ክርስቶስን እና መንፈስ ቅዱስን የሕይወታቸው ማዕከል አድርጎ ማስቀመጥ እና በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር የት እንደሚጠራ ለማወቅ በአንድ የገዳማውያት ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉት አባላት ድምጽ ማዳመጥ የብዙ ጉባኤያት ተግባር ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል። እህት ፓትሪሲያ አክለውም፥ ሲኖዶሳዊነት በዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሰራጭ ማየታቸው የበለጠ ደስታን እንደሚሰጥ ገልጸው፥  በኅብረት መኖር የሚፈልጉትም ይህ መንገድ እንደሆነ፥ እነርሱም የተሳትፎ፣ የኅብረት እና የተልዕኮ መንገድ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ጨለማውን የሚያበራ ብርሃን

በቼክ ሪፓብሊክ የፕራግ ከተማ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዘዴነክ ዋሰርባወር፥ የውይይት ሠነዱ መላውን ሲኖዶስ የሚያሳትፍ መሆኑን በማየታቸው እና ለሕጻኑ ኢየሱስ ቅድስት ተሬዛ መታሰቢያነት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይፋ ባደርጉት “በእግዚአብሔር መሐሪ ፍቅር መታመን” በተሰኘው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ልባቸው መማረኩን ተናግረው፥ በጉባኤው የተግባር ሂደት “ተልዕኮ” የሚለው ቃል ቁልፍ ነጥብ መሆኑን በግልፅ መረዳታቸውን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዘዴነክ ባቀረቧቸው ሁለት ምክንያቶች በተለይም የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳኑ እንደ መመሪያ ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል በመግለጽ፥ የመጀመሪያው ቅድስት ተሬዛ ወደ ቀርሜሎሳውያን ገዳም ስትገባ ነፍሳትን የማዳን ፍላጎት ስላላት በመሆኑ እና 400 የማኅበሩ አባላት በየቀኑ ለሌሎች መልካምን በመመኘት እና ድነታቸውን በመፈለግ እንደሚገናኙ መገንዘባቸውን ተናግረዋል። ሁለተኛው ምክንያት ቅድስት ተሬዛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1856 ዓ. ም. በነፍሷ ውስጥ የተሰማትን የጨለማ ምሽት የሚያመለክት እንደሆነ ተናግረው፥ አንዳንዶች እንደሚናገሩት “ጨለማ ውስጥ ለምትገኝ የሦስተኛው ሺህ ዓመት ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሱ ብርሃን ይዞ መጥቷል” በማለት ተናግረዋል።

ለሕሙማን ትኩረት መስጠት

የተመሳሳይ ጾታ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች “ሕመም" በማስመልከት ውይይት ተደርጎ ከሆነ ተብሎ ከጋዘጤኞች ጥያቄ የቀረበላቸው እህት ፓትሪሲያ፥ ሁሉም ባይሆን በብዙ የውይይት ጠረጴዛዎች ዙሪያ የተመሳሳይ ጾታ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ቁስል እና ሕመም  በግልም ሆነ በቡድን በቀረቡት ውይይቶች አማካይነት መታየቱን እና መደመጡን ገልጸዋል። እህት ፓትሪሲያ አክለውም፥ ጉዳቱ ይቅርታን መጠየቅ የሚያስፈልገው መሆኑን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ማሳየት ትችላለች ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱ፥ ይህን በማስመልከት ውይይቶች መካሄዳቸውን ተናግረው፥ “በደረሰው ሕመም እና ስቃይ ጥልቅ ግንዛቤ አለ” በማለት አፅንዖት ሰጥተዋል።

ከሌላ ጋዜጠኛ፥ የተመሳሳይ ጾታ ጥንዶች ቡራኬን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዶ/ር ፓዎሎ ሩፊኒ፥ ጉዳዩ የሲኖዶሱ ማዕከላዊ የውይይት ጉዳይ እንዳልሆነ ተናግረው፥ የሲኖዶሱ ቀዳሚ ርዕሦች ስለ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች ስልጠና፣ ስለተቀቡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ ለድሆች ስለሚሰጥ ቀዳሚ አማራጭ እና ስለ ቅኝ ግዛት የሚሉ እንደሆነ አብራርተዋል። ካቶሊካዊ አስተምህሮ በሲኖዶሱ መካከል ውይይት እየተካሄደባቸው ያሉት ርዕሦች ሁሉ ዋና ማዕከል እንደሆነ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ጨምረው ገልፀዋል።

የቻይና ብጹዓን ጳጳሳት

ከዚህም በላይ በሲኖዶሱ ላይ የተገኙትን ከቻይና የመጡ ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በተመለከተ፥ በሚቀጥለው ማብራሪያ በስፋት እንደሚናገሩ ገልጸው፥ የቻይና ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት በጉባኤው ላይ የተገኙት፥ ወደ ሀገረ ስብከቶቻቸው ሲመለሱ በሚያበረክቱት ሐዋርያዊ አገልግሎት ላይ ለመወያየት መሆኑን በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ አስረድተዋል።    

 

17 October 2023, 17:48