ፈልግ

በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበውን የሲኖዶስ ጉባኤ የቅዳሴ ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበውን የሲኖዶስ ጉባኤ የቅዳሴ ጸሎት   (Vatican Media)

ካርዲናል ራይ፥ ሲኖዶሳዊ ጉዞ ለዓለም አቀፍ ችግሮች ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ ገለጹ

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የአንጾኪያው ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ ራይ፥ ቫቲካን ውስጥ ለ16ኛው የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ተካፋዮች በተዘጋጀው የመስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ቃለ ምዕዳናቸውን አካፍለዋል። ሰኞ መስከረም 28/2016 ዓ. ም. በቀረበው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ በዓለማችን ውስጥ የሚያጋጥሙ በርካታ ችግሮችን ለመጋፈጥ ክርስቲያኖች ሲኖዶሳዊ የአኗኗር ዘይቤን ልንከተል ይገባል በማለት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳታፊዎች አራተኛውን ጠቅላላ ጉባኤ፥ ሰኞ መስከረም 28/2016 ዓ. ም. ከመጀመራቸው አስቀድመው በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ተካፍለዋል። በቢዛንታይን ሥርዓተ አምልኮ መሠረት የቀረበውን መስዋዕተ ቅዳሴን የመሩት በአንጾኪያ የግሪክ መልቃይት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዮሴፍ አብሲ ሲሆኑ፥ በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የአንጾኪያው ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ ራይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመከሩ ሠራተኞች እንዲጸልዩ ባቀረበው ግብዣ ላይ በማስተንተን ቃለ ምዕዳናቸውን አካፍለዋል።

በዓለማችን ውስጥ የሚታዩ ስቃዮችን ማሰብ

የአንጾኪያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ ራይ መስዋዕተ ቅዳሴውን ለተካፈሉት ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ይከተሉት ለነበሩ ብዙ ሰዎች እንደራራላቸው እና ለደቀ መዛሙርቱም፥ “መከሩ ብዙ ነው፣ ሠራተኞች ግን ጥቂቶች ናቸው” በማለት የመከሩ ጌታ ለመከሩ ሠራተኞችን እንዲልክ መለመኑን አስታውሰዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ ራኢ በማከልም፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል የቤተ ክርስቲያኗን ወቅታዊ ሁኔታ እና የማኅበረሰቡን ተግዳሮቶች ለመረዳት መነሻ ነጥብ እንደሚሆን አስረድተው፥ የተትረፈረፈውን ምርት ከቤተ ክርስቲያን እና ከክርስቲያን ማኅበረሰቦች በኩል ትኩረት ሊሰጥባቸው እና እርምጃ ሊወሰድባቸው ከሚገቡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ጋር በማዛመድ አሰላስለዋል።

እነዚህ ጉዳዮች በጦርነት ወቅት ፍትሃዊ ሰላምን ማስፈን፣ የአየር ንብረት ለውጥን መፍታት እና አካባቢን መንከባከብ እና መጠበቅ፣ በዝባዥ የሆኑ ኢኮኖሚ ሥርዓቶችን ማስወገድ፥ ስደት እና መከራ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን መርዳት እና የተለያዩ ጥቃቶች የሚደርስባቸውን ሰዎች ቁስል ማከም የሚሉት ይገኙበታል። ብፁዕ ካርዲናል ራይ አክለውም፥ መከሩ ሰብዓዊ ክብርን ማሳደግ፣ በማኅበረ ቅዱሳን እና በሃይማኖቶች መካከል ውይይትን ማጎልበት፣ የተገለሉ እና ተጋላጭ የሆኑትን መንከባከብ እና ወቅታዊ የሆኑ የማኅበረሰብ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ መተባበር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በመንፈስ ቅዱስ የሚመሩ የመከሩ ሠራተኞች

የአንጾኪያው ማሮናዊት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ ራይ፥ መከሩን ለመሰብሰብ የተጠሩትን ሠራተኞች ግምት ውስጥ በማስገባት እንደተናገሩት፥ የቅዱስ ሲኖዶስ የተግባር ሰነድ፥ እነዚህ የመከሩ ሠራተኞች በኢየሱስ ክርስቶስ  የተላኩ እና እያንዳንዱ ሠራተኛ በመንፈስ ቅዱስ የተመራ እንደነበር አስታውሰዋል። ብፁዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ ራኢ እንዳሉት፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ለቤተ ክርስቲያኑ በአደራ የተሰጠ የተልዕኮ እና የጠቅላላ ሲኖዶሳዊ ጉዞ ዋና ተዋናይ መሆኑንም አስረድተው፥ እያንዳንዱ ሠራተኛ ሲኖዶሳዊ የአኗኗር ዘይቤን ለመከተል ከመንፈስ ቅዱስ ስልጠና እና መመሪያ መቀበል አለበት” ብለዋል። እንዲህ ያለው ሥልጠና፣ “ለኅብረት፣ ለተልዕኮ፣ እና ለተሳትፎ ሕይወት መመሥረት እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን መታደስ እምብርት ላይ ያለውን ሲኖዶሳዊ መንፈሳዊነትን ያካትታል” ብለዋል።

ተልዕኮአችን የሌሎችን ቁስል ማከም ነው

በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የአንጾኪያው ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ ራይ፥ በቃለ ምዕዳናቸው መደምደሚያው ላይ፥ ክርስቲያኖች በዓለማችን ላይ ለደረሰው መከራ እና የሕዝቦች የስቃይ ሕይወት እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ርኅራኄ እንዲሰማቸው አደራ ብለዋል።

የድሆች፣ በማኅበረሰብ የተገለሉት፣ የስደተኞች፣ የጦርነት ሰለባ የሆኑ የንጹሐን ሰዎች እና መጠለያ የሌላቸው ሰዎች መከራ የኢየሱስ ክርስቶስን ርኅራኄ በማስታወስ ሊያነሳሳን ይገባል ብለው፥ በማከልም “እነዚህን ቁስሎች እንድንፈወስ እና የጋራ ቤታችን የሆነች ምድራችን በሰላም እና በመረጋጋት የምንኖርባት የተሻለች ዓለም እንድንጥር ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዳችንን መርጦናል” በማለት ብጹዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ ራይ ቃለ ምዕዳናቸውን ደምድመዋል።

10 October 2023, 17:28