ፈልግ

በሲኖዶስ ጉባኤ ወቅት አባላቱ በንዑሥ ቡድኖች ተመድበው ውይይት በማድረግ ላይ  በሲኖዶስ ጉባኤ ወቅት አባላቱ በንዑሥ ቡድኖች ተመድበው ውይይት በማድረግ ላይ   (Vatican Media)

ቅዱስ ሲኖዶስ፥ ቤተ ክርስቲያን መጓዝ የምትችልበት አዲስ መንገድ መኖሩን ገለጸ

የቫቲካን መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ዓርብ ጥቅምት 16/2016 ዓ. ም. ለጋዜጠኞች ባደረጉት ገለጻ፥ የጉባኤው የእስካሁን ጭብጥ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ቀርቦ ድምጽ እንደሚሰጥበት ተናግረዋል። ለጋዜጠኞች ገለጻ ካደረጉት መካከል አንዱ የሆኑት አባ ቲሞቲ ራድክሊፍም በበኩላቸው የሲኖዶሳዊነትን እውነተኛ ዓላማ በሚገባ የመረዳት ፍርሃትን ያስወግዳል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች፥ ዓርብ ጥቅምት 16/2016 ዓ. ም. ጠዋት በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት የጉባኤው አባላት ባሰሙት ንግግር፥ ዕለቱ የጾም እና የጸሎት ዕለት መሆኑን በማስታወስ፥ "ስለ ሰላም ያለማቋረጥ ሳንታክት መጸለይ ይኖርብናል" ብለዋል። ከዚህ ጋር በማያያዝ የቫቲካን ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ማታ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በአንድነት የጸሎት እና የቅዱስ ቁርባን ስግደት እንደሚኖር ለመላው የጉባኤው ተሳታፊዎች አስታውቀዋል።

ዶ/ር ሩፊኒ፡- በጉባኤው የመጨረሻ ጭብጥ ላይ ድምጽ መስጠት

በሲኖዶሱ የሥራ ሂደት ላይ ለጠቅላላ ጉባኤው ሪፖርታቸውን ያቀረቡት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ከጸሎት ሥነ ሥርዓቱ እና ከንዑሣን ቡድኖች ውይይት ቀደም ብሎ መጪው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የሚኖረውን የሲኖዶስ ሂደት ቀጣይ ምዕራፍ በተመለከተ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶች እና ሃሳቦች የሚሰበሰቡበት ክፍለ ጊዜ እንደሆነ ገልጸው፥ የጉባኤውን የመጨረሻ ረቂቅ ሪፖርት ዝግጅትን በተመለከተ አንዳንድ መረጃዎችን ሰጥተዋል።

በሪፖርቱ የመጀመሪያ ረቂቅ ላይ በተደረገው ውይይት 1,125 የጋራ እና 126 የግል አስተያየቶች መሰብሰባቸውን ከምስጋና ጋር ገልጸው፥ የጉባኤው አስተያየቶች የማሰባሰብ ሥራ በሂደት ላይ እንደሚገኝ እና የተሻሻለውን ሪፖርት በጽሑፍ ለማዘጋጀት ለተሰማሩት ጸሐፊዎች እና ባለሙያዎች ጉባኤው ምስጋናውን በጭብጨባ ማቅረቡን ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ገልጸዋል። በሲኖዶሱ ጉባኤበ የበዓል አከባበር መመሪያ አንቀጽ 33 አንቀፅ 2 ላይ በተደነገገው መሠረት፥ ኮሚሽኑ የመጨረሻ ሪፖርት ጽሑፍን በአብላጫ ድምፅ እንዲያፀድቅ እንደሚደርግ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ተናግረው፥ ቅዳሜ ጥቅምት 17/2016 ዓ. ም. ጠዋት በእንግሊዝኛ እና በጣሊያንኛ ቋንቋዎች የተዘጋጁ ኦፊሴላዊ ቅጂዎች ለጉባኤው አባላት በሙሉ እንደሚታደል ገልጸዋል። 

በዚህ መንገድ ሁሉም የጉባኤው ተካፋዮች የመጨረሻ ሪፖርት እትምን ለማንበብ በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት መደረጉን እና ከሰዓት በኋላ ድምጽ ለመስጠት በተሻለ ሁኔታ እንደሚዘጋጁበት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ አስረድተዋል። ጽሑፉ ጉባኤው መካከል እንደገና ተነብቦ በእያንዳንዱ አንቀፅ ላይ ድምጽ እንዲሰጥበት የሚያስችል ምስጢራዊ በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ የታገዘ ድምፅ መቀበያ ዘዴ መዘርጀቱን ገልጸዋል። እያንዳንዱ የጉባኤው አባል በእያንዳንዱ አንቀጽ ላይ ድምፁን መስጠት እንዳለበት በሲኖዶስ ጉባኤ መመሪያ አንቀጽ 35 አንቀፅ 3 መሠረት ድምጸ ተአቅቦ እንደማይፈቀድ፥ በዚሁ መመሪያ አንቀጽ 35 አንቀጽ 4 መሠረት፥ እያንዳንዱ አንቀጽ በድምጽ መስጫው ላይ ከሚገኙት አባላት መካከል ሁለት ሦስተኛው አብላጫ ድምጽ ማግኘት እንዳለበት ተናግረዋል።

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ አክለውም፥ ለሲኖዶሱ አባላት የተዘጋጀውን የአስተንትኖ ጊዜን አባ ቲሞቲ ራድክሊፍ እንደሚመሩት ገልጸው፥ በአስተንትኖ ወቅትም ከዚህ በፊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዶሚኒካን ማኅበር አባላት የላኳቸውን በጣሊያንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በፈረንሳይኛ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች የታተሙ አራት መልዕክቶችን የያዘ መጽሐፍ ለአባላቱ አባላት በስጦታ መልክ እንደሚሰጧቸው ገልጸዋል።

እሑድ ጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. ከጠዋቱ አራት ሰዓት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የሲኖዶሱ ማጠቃለያ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚቀርብ የቫቲካን ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ገልጸው፥ ዓርብ ጠዋት የሚካሄደውን የጉባኤው የሥራ ሂደት የአሌክሳንደሪያ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ልኡክ የሆኑት አባ ኢብራሂም ይስሐቅ ሴድራቅ በፕሬዝደንትነት እንደሚመሩት ገልጸዋል።

ጉዞ ወደ ታላቁ ሲኖዶሳዊ ተሳትፎ

የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሸይላ ፒሬስ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ገለጻ፥ የንዑሥ ቡድኖች የውይይት ማዕቀፎች እና ይዘቶች በሙሉ በሚቀጥለው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በሮም በሚካሄድ የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ ያተኮሩ እንደነበር ገለጸው፥ የዕለቱ ጭብጦች ለቀጣይ ዘዴዎች እና እርምጃዎች ሃሳቦችን የሚጋሩ እንደ ነበርም አስረድተዋል።

ከጉባኤው ተሳታፊዎች መካከል ብዙዎቹ የሚቀጥለው ጉባኤ ቆይታ አራት ሳምንት ከመሆኑ ይልቅ ሦስት ሳምንታት እንዲሆን አስተያየታቸውን ማቅረባቸውን ተናግረው፥ በጉባዔው ውስጥ በሚደረጉ ንግግሮች የተሻለ ተሳትፎ እንዲኖር፥ ለንዑሥ ቡድኖች ተጨማሪ የውይይት ጊዜ እንዲሰጣቸው እና በቋንቋ ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን በእያንዳንዱ ግለሰብ ዳራ ላይ የተመሠረቱ ተጨማሪ የንዑሥ ቡድኖች ስብሰባዎች እንዲኖሩ ሃሳብ መቅረቡን ተናግረዋል።

ከጉባኤው ተካፋዮች ከቀረቡት ሃሳቦች መካከል አንዱ የጉባኤው የመጨረሻ ጭብጥ ሠነድ ለሁሉም ሰው በተለይም ወጣቶች ሊረዱት በሚችሉት ቋንቋ በአጭር ይዘት እንዲዘጋጅ፥ በአዳራሹ ውስጥ በመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ የተደረጉት ውይይቶችን ወደ ምዕመናን ዘንድ የማቅረብ አስፈላጊነት እና ከእግዚአብሔር ሕዝብ ተጨባጭ ሕይወት ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ያለው ሊሆን እንደሚገባ ሃሳብ መቀረቡን አስረድተው፥ የሲኖዶሳዊነት መንገድ በመከተል በየደረጃው የሚገኙ የምዕመናን ማኅበረሰቦች እንዲያሳተፉ፥ በቀኖና ሕግ በተደነገገው የወጣቶች፣ የሴቶች እና የዲያቆናት ተሳትፎ ሲኖዶሳዊነትን እና የጋራ ሃላፊነትን ተግባራዊ ማድረግ የሚሉ ሃሳቦች መቅረባቸዋን የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሸይላ ፒሬስ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ገለጻ ማጠቃለያ ላይ አክለው ገልጸዋል።

የቅዱስ ቤኔዲክት ልምድን ወደ ጉባኤው ማምጣት

በጣሊያን ከቪቦልዶኔ ቅዱስ ቤኔዲክት ገዳም የመጡት እናት ማርያ ኢግናሲያ አንጄሊኒ ለጉባኤው አባላት  መንፈሳዊ ድጋፍ በሰጡበት ወቅት እንደ ተናገሩት፥ ሚናቸውን ከጉባኤው አባላት ጋር በመደማመጥ እና በጋራ ጸሎት በመሳተፍ ሲወጡት እንደነበር ገልጸው፥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ባገኙት የገዳም ሕይወት ተሞክሮአቸው ከመጀመሪያው አንስቶ የቅዱስ ቤነዲክቶስን የሕይወት ልምድ እንደሚያስቡ ገልጸዋል።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ፍጹም ኢምንት የሆነውን የገዳም ሕይወት ልምድ መሠረት በማድረግ አስተያየታቸውን ለጉባኤው አባላት ማካፈል መቻላቸውን እናት ማርያ ኢግናሲያ ገልጸው፥ ከዚህ አንፃር የሲኖዶሱ የለውጥ ባህሪ የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት የመለወጥ፣ እርስ በርስ የመገናኘት እና የአንድነት ስሜት በማሳደግ ልዩነቶች ማየት በሚያስችል የልብ መከፈት፣ እውነትን በመመልከት ችሎታ በታሪክ ውስጥ ውስብስብ እና ሊገለጹ የማይችሉ ጊዜያትን እምነትን በሚጠይቅ ከፍተኛ ራዕይ የእግዚአብሔርን በሥጋ መገለጽን ለመመስከር መቻላቸውን አስረድተዋል።

እናት አንጀሊኒ ቀጥለውም፥ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደዚህ ዓይነት አስከፊ የታሪክ ጊዜያትን ለመተርጎም ጥልቅ እና መልካም መመዘኛዎችን እንደሚሰጡ አስረድተው፥ ካርዲናሎች፣ ጳጳሳት፣ የነገረ መለኮት ሊቃውንት እና ምእመናን ከልዩነቶቻቸው ጋር በኅብረት ተሰብስበው መወያየታቸውን በማወደስ በጣሊያን ከቪቦልዶኔ ቅዱስ ቤኔዲክት ገዳም የመጡት እናት ማርያ ኢግናሲያ አንጄሊኒ ገለጻቸውን ደምድመዋል።

ሲኖዶሳዊ ዘይቤን በጋራ መማር

በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ከሚገኝ የዶሚኒካን ገዳም የመጡት አባ ጢሞቴዎስ ፒተር ጆሴፍ ራድክሊፍ በሲኖዶስ በሲኖዶሱ ጉባኤ ወቅት መንፈሳዊ ረዳት ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፥ ለጋዜጠኖች ባደረጉት ገለጻ፥ ሲኖዶሳዊነት ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት የተመሠረተ የዶሚኒካን ማኅበር የአኗኗር ዘይቤ አካል መሆኑን ጠቅሰው፥ እስካሁን ከተሳተፏቸው አራት የሲኖዶስ ጉባኤዎች የዛሬው የተለየ መሆኑን ተናግረዋል። በቤተ ክርስቲያን ላይ ልዩ ለውጥ እንዲመጣ ያደረገ ጉባኤ እንደሆነ ገልጸው፥ ከላቲን አሜሪካ እና እስያ አኅጉራት የመጡ ካርዲናሎች እና ወጣት ሴቶች አንድ ላይ ተቀምጠው ሲወያዩ ማየት፥ ከሰዎች ልምድ አንፃር ቤተ ክርስቲያንን የሚቀይር እንደሆነ ተናግረዋል። የጳጳሳት ሲኖዶስ እና የጳጳሳት ኅብረት ተወካይ መሆን ማለት በብቸኝነት ሳይሆን እንደ ጳጳስ በምዕመናኑ ስም እርስ በርስ መደማመጥን፣ መነጋገርን እና አብሮ መማርን የሚገልጽ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ይህ ማለት በዚህ ጉባኤ ላይ ጥቂት ውሳኔዎችን በማድረግ መለያየት ሳይሆን፥ ቤተ ክርስቲያን እንዴት በአዲስ መንገድ መራመድ እንደምትችል ለመረዳት፥ የሌሎችን ድምጽ የምትሰማ ቤተ ክርስቲያን እንደምትሆን፣ አባሎቿም በተለያዩ ባሕሎች መካከል እርስ በርሳቸው የሚደማመጡ እና ትውፊትን የሚያዳምጡበት ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ውሳኔዎችን እንዴት እንደምትወስድ የምትማርበት ጊዜ እንደሆነ ገልጸው፥ በመማር ሂደት ውስጥ መሰናክሎች እና ስህተቶች እንደሚኖሩ አስረድተዋል።

የመማር ሂደት ዛሬ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ የምንኖረው በዓመፅ በተሞላ ዓለም ውስጥ እንደሆነ፥ በሰዎች መካከል የመግባባት ስሜት መጥፋቱን፥ እንደ መካከለኛው ምስራቅ፣ ዩክሬን እና ብዙ የአፍሪካ አገራት፣ በገዛ ገራቸው ታላቋ ብሪታኒያ እና አሜሪካ ውስጥ ልዩነቶች መኖራቸውን እየተመለከቱ እንደሆነ ገልጸው፥ በተወሰነ መልኩ እርስ በርሳችን መነጋገር እና መደማመጥ እንዳለብን መማር እንደሚገባ፥ ይህ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን ቁስል ለማከም ብቻ ሳይሆን መላውን የሰው ልጅ ለመለወጥ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።

ቤተ ክርስቲያን የመሆን አዲስ መንገድ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2005 ዓ. ም. ጀምሮ በፈረንሳይ የታይዜ ማኅበረሰብ መሪ በመሆን ያገለገሉ እና ጉባኤውን እንደ ልዩ ተጋባዥ ሆነው መካፈላቸውን የገለጹት ወንድም አሎይስ የጉባኤውን ሂደት በማስመልከት ባቀረቡት ገለጻ፥ በአዳራሹ ውስጥ የተሐድሶ መሪ በወንድማማችነት ስሜት መገኘታቸው፥ የሲኖዶሱ ጥልቅ የኅብረት ልምድ እንደሆነ ተናግረው፥ ይህም የሲኖዶሱ ጉባኤ እንዴት በእውነት ለክርስቲያኖች ሁሉ እና ለዓለም ክፍት እንደ ነበር የሚመሰክር ጉልህ ምልክት እንደሆነ አስረድተዋል። በዚህ ረገድም ወንድም አሎይስ መስከረም 19/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተካሄደውን ልዩ የአብያተ ክርስቲያናት እና የማኅበረሰቦች ተወካዮች የተገኙበትን የጋራ የጸሎት ሥነ ሥርዓት አስታውሰው፥ ይህም ሁላችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም መጠመቃችንን እና “የአንድ አካል ክፍሎች” በሚለው ግንዛቤ ላይ በመመሥረት በክርስቲያኖች አንድነት እንድንራመድ የሚፈቅድ ነው ብለው፥ በተለይ በመደማመጥ፣ እራስን ዝቅ በማድረግ፣ እርስ በእርስ ለመወያየት ያለንን ፈቃደኛነት የሚገልጽ፥ በአንድነት የሚገኘውን ደስታ ለመካፈል ያለን ፍላጎት በሲኖዶስ ጉባኤ ጎልቶ ታይቷል ብለዋል። ይህ ዘይቤ ወደ ብዙ የዓለም ክፍሎች እንደሚስፋፋ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ የሲኖዶሱ ሂደት ወደ ቤተ ክርስቲያን አዲስ መንገድ የሚመራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሲኖዶሳዊ ዘዴን የምንፈራበት ምክንያት የለም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያደነቁላቸውን የማኅበራዊ መገናኛ መጽሐፍ ያሳተሙት አባ ራድክሊፍ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ በጋራ የውይይት መድረክ መሳተፋቸውን ገልጸው፥ አንዳንዶች ጥርጣሬ ቢያድርባቸውም ሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያኗን ወደ አዲስ ምዕራፍ የመምራት ዕድልን በተመለከተ ወንድም አሎይስ ማድነቃቸውን በድጋሚ ተናግረዋል። ከተለያዩ የባህል ዳራዎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች በተሻለ ሁኔታ ለመረዳዳት መሞከራቸውን፥ ሲኖዶሱ በልባቸው ውስጥ ለውጥ እንዳመጣ እርግጠኛ መሆናቸውን ገልፀው “ሁላችንም በጋራ ልንጓዝ ይገባል” ብለዋል።

አንዳንድ ሰዎች የሲኖዶሱ ዘዴ ስላልገባቸው እንደሚፈሩ በማስረዳት፥ የሲኖዶስ ክርክር ፖለቲካዊ ይዘት ያለው እና መለያየትን ያስከትላል ብለው እንደሚፈሩ ገልጸው፥ ግን ተቃራኒው እየሆነ እንዳለ፥ "ሲኖዶስ የጸሎት እና የእምነት ክስተት ነው" በማለት አባ ራድክሊፍ አጽንዖት ሰጥቷል።

የዚህን ሲኖዶስ ፅንሰ-ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ለአንድ ሰበካ ካኅን ምን ዓይነት ተግባራዊ ምክሮችን እንደሚሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ የሲኖዶሱ ተደጋጋሚ ጭብጥ ቤተ ክህነት የራሱን ፍላጎት በሌሎች ላይ የሚጫንበት ባለመሆኑ የሀገረ ስብከት ካህናትን ሊያስደነግጥ እንደማይገባ ተናግረው፥ የሀገረ ስብከት የክህነት ውበት እና የወንጌል አገልግሎት ሥራን በመደገፍ እያንዳንዱን አወንታዊ ገጽታ ማጉላት ያስፈልጋል ብለዋል።

አባ ራድክሊፍ ስለ ሲኖዶሱ ይዘት አገላለጽ ሲጠየቁ፥ ከውይይቶቹ የርዕዮተ ዓለም ግጭት ተፈጥሯል ብለው እንደማያምኑ ጠቁመው፥ ብቅ ያሉት የባህል ልዩነቶች እንደ ነበሩ፥ የካቶሊክ ሃይማኖት ውበት፣ ባህሎችን የሚያበለጽጉ ልዩነት ስላላቸው ከመላው ዓለም የመጡ ሰዎችን በመቀበል ላይ ነው ብለዋል። ለአንድ የተለየ ባህል ብቻ ሊሆን የሚችል ይዘት ካለው በሌላ ቦታ ለሚገኝ ባሕል ሊሆን እንደማይችል እና የሌሎችን በሕል ማክበርን መማር በሲኖዶስ ውስጥ ከሌለ ርዕዮተ ዓለማዊነት የበለጠ ጎልቶ ሊታይ እንደሚችል አስረድተዋል።

አባ ራድክሊፍ የተመሳሳይ ጾታ ዝንባሌ ያላቸውን ሰዎች ወደ ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት ማስገባት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ ጉዳዩ ማግለልን የሚመለከት ሳይሆን፥ ፆታዊ ስሜታቸውን የማንነታቸው መለያ ያደረጉ ሰዎች መኖራቸውን እና በእነርሱ ውስጥ ጥርጣሬን እና ፍርሃትን መፍጠሩን አስረድተዋል። የነገረ መለኮት ምሁር እና የቅዱስ ዶሚኒኮስ ማኅበር አባል የሆኑት አባ ራድክሊፍ፥ ሲኖዶሳዊነት ልምምድ ብቻ ሳይሆን በዋነኛነት የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት መሆኑን በመግለጽ፥ ሁሉም ሰው ከተለያዩ ቦታዎች ለሚመጡ ሰዎች ሕይወታቸውን እና ልምዳቸውን ለማካፈል ያላቸውን ፈቃደኝነት በድጋሚ አድንቀዋል።

እናት አንጀሊኒ፥ ወጣቶችን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ ሲኖዶሳዊነ "እኔ" ከማለት “እኛ” ወደ ማለት የተሸጋገርንበት ሂደት መሆኑን ገልጸው፥ የችግሩን አሳሳቢነት ለመገንዘብ ማስቻላቸውን አስረድተዋል። ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለይ በዲጂታል ዘመን በአዲስ ሚዲያዎች አማካይነት አዲሱን ትውልድ ሊረዱት በሚችሉት ቋንቋ መቅረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ በዚህ ረገድ ሲኖዶሱ የለውጥ መንገድ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ ድምጽ ከመስጠት መታቀብ እንደማይቻል አረጋግጠው፥ እያንዳንዱ ቡድን በውውይት ወቅት ያቀረበው ሃሳብ መኖሩን ጠቅሰው፥ በተግባር ከዚህ ተነስቶ ወደ ቀጣዩ ጉባኤ የሚወስድ መንገድ እንዳለ እና በአህጉራቱ እና ሀገረ ስብከቶች ውስጥ ተጨማሪ ግንዛቤን ማስጨበጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። አንዱ ጉልህ ገጽታ ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የእግዚአብሔር ሕዝቦችን በሲኖዶሳዊ ጉዞ እንዴት ማሳተፍ እንደሚቻል ማሰብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አባ ራድክሊፍ የሰው ልጆችን ቁስል የመፈወስ አስፈላጊነትን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፥ "በተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት የቆሰሉ ሰዎችን ማግኘት እና መንከባከብ አስፈላጊ ነው" ብለው፥ ስደተኞችን ከባሕር ላይ አደጋ ለማዳን የተሰማራውን የሲኖዶሱ ተሳታፊ ሉካ ካሳሪኒ ልምድ በመጥቀስ፥ የእርሱ ልምድ እርስ በርስ በመተሳሰብ የሌሎችን ቁስል ለመፈወስ እንደሚያስችል ተናግረው፥ በመከራ የቆሰሉ ሰዎች ድምጽ ማዳመጥ በፈውሳቸው ጊዜ እንድንረዳቸው ያስችለናል ሲሉ ተናግረዋል።

የሲኖዶሱን አስተያየት፥ ሕጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃትን ፈጽመዋል የተባሉት በአባ ሩፕኒክ ጉዳይ ላይ በቀረበው መግለጫ መካከል ሊኖር የሚችለውን ቀጥተኛ ግንኙነት በተመለከተ ምላሽ የሰጡት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የወሰኑትን ሕገ ቀኖናዊ ደንብ በመጥቀስ፥ ሲኖዶሱ በግለሰብ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱ ለዓመታት ስትፈጽም የቆየችውን የመብት ጥሰት ችግር ለመፍታት እና የንስሐ መንገድን እንዲጓዙ የሚያግዙ የአዳዲስ ደንቦች ተግባራዊነት ላይ እንደተወያየ ገልጸው፥ አክለውም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰዎች ላይ የሚደርስ በደል በመዋጋት ትልቅ ሚና መጫወታቸውን የቫቲካን ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ አጽንዖትን ሰጥተው ተናግረዋል።

 

28 October 2023, 18:36