ፈልግ

የሲኖዶሱ አሥራ አምስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ፥ የሲኖዶሱ አሥራ አምስተኛ ጠቅላላ ጉባኤ፥   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ቅዱስ ሲኖዶስ፥ ቤተ ክርስቲያን ከድሆች ጋር መሆኗን አስታወቀ

በሮም ከመስከረም 23 ጀምሮ በመካሄድ ላይ የሚገኘው 16ኛ የሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ፥ ቅዳሜ ጥቅምት 10/2016 ዓ. ም. በሰጠው ማብራሪያ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሴቶች ሚና እና ሕጻናትን ጨምሮ አቅመ ደካሞችን ከወሲባዊ ጥቃት መጠበቅ በሚሉ ርዕሦች ላይ የተካሄዱ ውይይቶችን በማስመልከት ማብራሪያዎች ተሰጥተውባቸዋል። የጉባኤው ተሳታፊዎች በተጨማሪም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሰላም በተዘጋጀው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይም ተካፋይ ሆነዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለጉባኤው ተሳታፊዎች ዓርብ ጥቅምት 9/2016 ዓ. ም. በቀረበላቸው ልዩ ጥሪ መሠረት፥ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ የመካከለኛው ምሥራቅ ወጣቶች ተስፋ እንድሳይቆርጡ፥ ስደትን ብቸኛ አማራጭ አድርገው እንዳይወስዱ፥ እንደ ቤተ ክርስቲያን እና እንደ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወጣቶች ወደ ሰላም የሚደርሱበትን መንገድ በማሳየት መርዳት እንደሚገባ አሳስቧል። በቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ክርስቲያን መሬይ ባስተዋወቁት ዝግጅት ላይ የቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ቅዳሜ ጥቅምት 2016 ዓ. ም. ለጋዘጤኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዓርብ ጥቅምት 9/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተካሄደው አሥራ አምስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ዩክሬን፣ የአማዞን አካባቢ አገሮች እና ከሌሎች የጦርነት ወይም የስቃይ አካባቢዎች የተገኙ አንዳንድ ጠንካራ እና ጥልቅ ስሜት ያላቸው ምስክርነቶች ቅርበው እንደነበር ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በማብራሪያቸው ገልጸው፥ በጉባኤን 329 አባላት መካፈላቸውን ገልጸዋል። ቅዳሜ ጥቅምት 10/2016 ዓ. ም. በተካሄደው 12ኛ ስብሰባ ማጠቃለያ ላይ 35 ንዑሥ ቡድኖች በተግባር ሠነዱ ምዕራፍ B3 ላይ ያደረጉት ውይይት ሪፖርቶችን ለጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ አቅርበዋል። በውይይት ላይ 310 አባላት የተሳተፉ ሲሆን፥ የማጠቃለያ ሠነድ የማዘጋጀት ሥራም መካሄዱ ታውቋል። ሰኞ ጥቅምት 12/2016 ዓ. ም. ጠዋት የሲኖዶሱ ተሳታፊዎች፥ በምያንማር የያንጎን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ተገኝተዋል።

ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር በመተባበር

በሲኖዶስ አዳራሽ ውስጥ በተደረጉት ንግግሮች ላይ፥ በቤተ ክርስቲያናት ባለሥልጣናት እና ተባባሪዎቻቸው መካከል ያለውን የውሳኔ አሰጣጥ ግንኙነት እና የጋራ ኃላፊነትን በተመለከተ ገለጻ መደረጉን የቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ጠቅሰው፥ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊነት ሥልጣንን የሚያስቀር ሳይሆን ነገር ግን ዋና አውድ እንደሚያደርግ፥ ልዩነቶች ቢኖሩም ወደ መግባባት ለመድረስ ውይይት አስፈላጊ ስለሆነ መፍራት እንዳማይገባ ተናግረው፥ ግጭቶችን ወደ ሰላም በሚለውጥ መንፈስ ቅዱስ ላይ በመተማመን በውይይት ወደ ፊት መራመድ ይገባል በማለት ለጉባኤው እትሳታፊዎች በሙሉ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

ለጋራ መደማመጥ ቀዳሚ ትኩረትን የሰጠው ጉባኤው፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀባይነት እንደሌላቸው የሚሰማቸውን ወይም የቤተ ክርስቲያን አባል እንዳልሆኑ የተነገራቸውን እንደ የሌላ ሃይማኖት ተከታይ ስደተኞችን፣ ድሆችን፣ አድልዎ የሚደረግባቸውን ሰዎች እና የአካል ጉዳተኞችን ማዳመጥ እንደሚገባ አሳስቧል። የተመሳሳይ ጾታ ዝንባሌ ባለባቸው ግለሰቦች ላይ ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ከማድረስ ይልቅ እንደ እግዚአብሔር ፍጡራን ክብር እና መልካም አቀባበል ሊደረግላቸው እንዳማይገባ ስብሰባው መወያየቱን የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ጠቅሰዋል።

በስብሰባው ከተነሱት ጉልህ ርዕሦች መካከል አንዱ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያለውን አንድነት የተመለከተ እንደ ነበር ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ተናግረው፥ ከሐዋርያው ጴጥሮስ ጋር መሠረታዊ ኅብረት የሌላቸው ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተ ክርቲያን እንደሚያቆስሉ መጻፉን አስታውሰው፥ ክፍፍል፣ ጭፍን ጥላቻ እና ጦርነት ለበዛበት ለዛሬው ዓለማችን አንድነት እና ኅብረት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል።

ቤተ ክርስቲያን ከድሆች ጋር መሆን

ቀጥሎም የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሼይላ ፒሬስ በማብራሪያቸው፥ በአዳራሹ ውስጥ ውይይት ከተደረገባቸው ርዕሠ ጉዳዮች መካከል ሴት ምዕመናን እና ገዳማውያት እህቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ሚና በተመለከተ በተለይም በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውስጥ ድምፃቸውን ማሰማት እንደሚቻሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የቤተ ክኅነት ብቻ ውሳኔ ሰጭነት በስብሰባው ላይ ሲቀርብ እንደ ነበር የገለጹት ወ/ሮ ፒሬስ ይህን በተመለከተ በዘርዓ ክህነት ዝግጅት ወቅት ዘላቂ ስልጠና እና ትምህርት በመስጠት የሚታየውን ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረው፥ በሕጻናት እና አቅመ ደካሞች ላይ የሚደርሰውን በደል ለመዋጋት የሚያስችሉ ተገቢ መዋቅሮች ሊኖሩ እንደሚገባ አጽንዖትን ተሰጥተዋል። የሚደርሱ በደሎችን እና አሳዛኝ ሁኔታዎች ለመቅረፍ አዳዲስ መዋቅሮችን በማስተዋወቃቸው ተሳታፊዎቹ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ጎልማሶችን እና ህጻናትን ጨምሮ ሁሉንም ግለሰቦች ከጉዳት ለመጠበቅ በየደረጃው ያሉ ተነሳሽነቶችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አባላቱ ትኩረት በመስጠት መወያየታቸውን የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሼይላ ፒሬስ በማብራሪያቸው አስረድተዋል።

በስብሰባው ላይ የተነሳው ሌላው ተደጋጋሚ ጭብጥ በዲጂታል ዘመን ውስጥ ያለውን ተልዕኮ የተመለከተ ሲሆን፥  ይህም በእውነተኛ ሕይወት ውስጥ ሰዎችን የሚያካትት ምናባዊ ዓለም ብቻ መሆን እንደሌለበት የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ሼይላ ፒሬስ ገልጸው፥ ስብሰባው በጋራ አስተያየቱ ቤተ ክርስቲያን ድሆችን የማገልገል ተልዕኮዋን በድጋሚ በማረጋገጥ አቅመ ደካሞችን ለመርዳት በምንከተለው መንገድ እግዚአብሔር ፍርዱን የሚሰጥ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በልዩነት ውስጥ ያለ አንድነት

በደቡብ አሜሪካ ፔሩ የሀዋንካዮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ እና የአማዞን አካባቢ አገራት ብጹዓን ጻጻሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት የሆኑት የኢየሱሳውያን ማኅበር አባል ብፁዕ ካርዲናል ፔድሮ ሪካርዶ ባሬቶ ሲኖዶሱ ከሁለት ዓመታት በላይ ሲዘጋጅ መቅየቱን አስታውሠው፥ መጀመሪያ በቁምስናዎች፥ ከዚያም በሀገረ ስብከቶች እና ቀጥሎም በአህጉር ደረጃ ለሁለት ዓመታት ዝግጅት ሲደረግበት መቆየቱን ገልጸው፥ በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን የሚናገራትን መልዕክት በማድመጥ ላይ እንደነበሩ ተናግረዋል። ጳጳሳት የአንድ ክልል ሐዋርያዊ መሪዎች ሲሆኑ በተመሳሳይ ጊዜም ከር ዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በመተባበር ለዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን አስረድተዋል። በ16ኛው የሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አብዛኞቹ ጳጳሳት ቢሆኑም ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ምእመናን እና ካኅናት መገኘታቸውን ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ባሬቶ ተጨባች ልምዶችን ለመሰብሰብ ዕድል በማገኘታቸው ምስጋናቸውን ያቀረቡት ብፁዕ ካርዲናል ፔድሮ ሪካርዶ ባሬቶ፥ በዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የብሔር፣ የባሕል እና የቋንቋ ልዩነቶች ቢታዩም፥ ሁሉንም በአንድ መንፈስ የሚያዋሕድ ቅዱስት ሥላሴ እንደሆነ በመግለጽ፥ እግዚአብሔር እራሱ ኅብረት፣ ተልእኮ እና ተሳትፎ በመሆኑ ይህ ሲኖዶሳዊ ልምድ በእግዚአብሔር አንድነት ውስጥ ያለውን የልዩነት አድማስ ከፍቶልናል ብለዋል።

52 ዓመታት የክህነት እና 23 ዓመታት የጵጵስና አገልግሎታቸውን ያስታወሱት ብፁዕ ካርዲናል ፔድሮ ሪካርዶ ባሬቶ፥ ቤተ ክርስቲያን ከውስጥም ሆነ ከውጪም በሚያጋጥሟት ችግሮች መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን እና የሰው ልጆችን እያገለገለች ወደፊት በመገስገስ ላይ ትገኛለች” በማለት ብሩህ ተስፋቸውን በመግለጽ ማብራሪያቸውን ደምድመዋል።

ንስሐ እና መታደስ

በጀርመን የኤሰን ሀገረ ስብከት ጳጳስ እና የሠራዊቱ ሐዋርያዊ አገልግሎት አተባባሪ ጳጳስ አቡነ ፍራንዝ ጆሴፍ በጀርመን የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2018 ዓ. ም. ጀምሮ ስታደርግ የቆየችውን ሲኖዶሳዊ ጉዞን በማስታወስ፥ ያገኙትንም ልምድ ለጋዜጠኞች አብራርተው፥ ሂደቱን የጀመሩበት ምክንያት በሀገሪቱ ውስጥ የተፈጸሙ በርካታ ወሲባዊ ጥቃቶችን ለመለየት በማሰብ እንደነበር አስረድተዋል።

ሥራው የተካሄደው ከጀርመን ካቶሊኮች ማዕከላዊ ኮሚቴ ጋር በመተባበር መሆኑ ተናግረው፥ ይህም በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የሙያ ቡድኖች ተወካዮችን ያካተተ እንደነበር ገልጸዋል። የንስሐ እና የመታደስ መንገድ ነበር” በማለት የገለጹት አቡነ ፍራንዝ፥ “የቤተ ክርስቲያንን ድርጊት ራስን በመተቸት እና ለቤተ ክርስቲያን ሕይወት መታደስ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን በማጤን ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል” በማለት ተናግረዋል። “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃልን እና ካቶሊካዊ ትውፊቶችን ምስክር ማድረግ ወደ ነገረ-መለኮት እውቀት መመለስን ይጠይቃል” ያሉት አቡነ ፍራንዝ ጆሴፍ፥ በነገረ-መለኮት ግኝቶች የምእመናንን እምነት እና የዘመኑን ምልክቶች በብርሃን መተርጎም የወንጌል አገልግሎትን ተአማኒ ለማድረግ ያግዛል” ብለዋል።

“ነገረ-መለኮት፣ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ወይም ትውፊት እና በዘመኑ ምልክቶች መካከል የማይታረቁ ቅራኔዎች ካሉ ማንንም ቢሆን ወደ እምነት እንዲደርስ የማይረዳ እና ለካቶሊኮች መመሪያ ሊሰጥ አይችልም” በማለት ገልጸው፥ ጀርመን ውስጥ የካቶሊክ ምዕመናን ቁጥር 30 በመቶው ብቻ እንደሆኑ እና ሌላው 30 ከመቶ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች እንደሆኑ፣ 40 በመቶው የሚሆኑት ደግሞ አማኞች ያልሆኑ መሆናቸውን አስረድተዋል። “በጀርመን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አራት የአስተሳሰብ ዘርፎች አሉ” ያሉት አቡነ ፍራንዝ ጆሴፍ እነርሱም ፡- በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለ የሥልጣን ተዋረድ፣ የክህነት አገልግሎት፣ የሴት ምዕመናን ሚና እና የፆታ ሥነ ምግባር መሆናቸውን ተናግረዋል። እነዚህን ጉዳዮች ለማጥናት እና የሚወሰዱ እርምጃዎችን ዝርዝር ለማቅረብ በፍራንክፈርት አምስት ዋና ዋና ጉባኤዎች ተዘጋጅተው እንደነበረ ገልጸው፥ ውጤቶቹም በጀርመን ጳጳሳት ጉባኤ አማካይነት በተከታታይ በተዘጋጁት ሠነዶች መታተማቸውን ገልጸዋል።

"በዚህ መንገድ በጀርመን ቤተ ክርስቲያን ልምድ ውስጥ ሲኖዶስ የሚባል አዲስ የመሰብሰቢያ መንገድ የሥራ ዓይነትን መርጠናል" ብለዋል። እነዚህ ቀኖናዊ የሲኖዶስ ውሳኔዎች እንዳልሆኑ ገልጸው፥ ነገር ግን የበለጠ ክብደት እንዲኖራቸው ለማድረግ ቢያንስ በሁለት ሦስተኛው የጳጳሳት ድምጽ ዕውቅና የተሰጣቸውን ብቻ ለመቀበል መወሰኑን ተናግረው፥ ሦሶስት አመታት ውስጥ 15 ውሳኔዎች መጽደቃቸውን አስረድተዋል.

በመጨረሻም በላቲን አሜሪካ የአድቬኒያት ፕሬዝዳንት የሆኑት አቡነ ኦቨርቤክ፥ ጳጳሳት፣ ቀሳውስት፣ ገዳማውያት እና ገዳማውያን እንዲሁም ምእመናን ፍጥረትን በተመለከተ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በጋራ የሚሰሩበት የአማዞን አካባቢ አገራት የጳጳሳት ጉባኤዎች ልምዶች ያላቸውን ጠቀሜታ አጽንኦት ሰጥተዋል። “ኢየሱስ ክርስቶስን ሁል ጊዜ የእምነት ማዕከል በማድረግ፣ ልማዶችን እና ልማዳዊ ድርጊቶች በእውነት የስልጣን ተዋረድ ውስጥ ቅድሚያ የማይሰጣቸው መሆኑን በማስገንዘብ ማብራሪያቸውን ደምድመዋል።

በፈረንሳይ የግሬንቦል ቪዬን ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ዣን ማርክ አይቸን፥ የደቡባዊ ቱሉዝ አካባቢ “የፈረንሳይ አማዞን” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ያለውን ልምድ ሲናገሩ፥ ክልሉ በድህነት የሚታወቅ ቢሆንም የኢየሱስ ክርስቶስን እና የወንጌልን መንፈሳዊ ፍለጋን የሚያበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል። 150,000 ነዋሪዎች ከሚገኙበት አካባቢ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ሁኔታዎች ወደሚገኙበት እና አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች ወደሚገኙበት ሀገረ ስብከት እንደተዛወሩ ተናግረው፥ ሁለቱን ሀገረ ስብከቶችን ብዙ የሚያመሳስሏቸው ተመሳሳይ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ገልጸው፥ ዋናው ተግዳሮት የጋራ ሃላፊነት መጓደል እንደሆነ ተናግረው፥ ሲኖዶሳዊነት ማለት አንድ ላይ በማሰላሰል እና ቤተ ክርስቲያን ይህን ጽንሰ-ሐሳብ እንዴት እንደምትቀበለው መመልከት እና ቤተ ክርስቲያን ኃላፊነት ከሚሰማቸው ጥቂት ሰዎች  ወደ የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል በኅብረት የማወጅ የጋራ ሃላፊነት ካለባት ቤተ ክርስቲያን ጋር በኅብረት መጓዝ ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

ዘላቂነት ያለው ጉዞ

በሕንድ ሐዋርያዊ የቄርሎሳውያን እህቶች ማኅበር ጠቅላይ አለቃ እና በሕንድ የገዳማውያት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እህት ማሪያ ኒርማሊኒ፣ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ በፕሬዝደንትነት የሚመሩት ጉባኤ ከ130,000 በላይ አባላት ያሉት እና በዓለም ውስጥ ትልቁ የካቶሊክ ገዳማውያት ማኅበራትን የሚወክል ጉባኤ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም አቀፉ የጠቅላይ አለቆች ኅብረት ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው እህት ኒርማሊኒ አስደሳች ልምድ እና አስደናቂ ጉዞ በሆነው የሲኖዶስ ጉባኤ ወቅት የሕንድ ገዳማውያት ለሚያደርጉት የጸሎት ድጋፍ አጽንኦት ሰጥተዋል።  በእያንዳንዱ የጉባኤው ተሳታፊ መካከል የባሕል እና የአስተዳደግ ልዩነት ቢኖርም ልምዳቸውን እና ሃሳባቸውን በነፃነት ለካርዲናሎች፣ ለብጹዓን ጳጳሳት፣ ለነገረ መልኮት ሊቃውንት፣ ለወጣት ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ ለምእመናን እና እንደ እርሳቸው ላሉ ግለሰቦች በነፃነት እንደሚያካፍሉ ተናግረዋል።

እህት ኒርማሊኒ ከጉባኤው መልስ ወደ ሕንድ ሲመለሱ ከዚህ በፊት በሮም ያልተደረገውን የሲኖዶሱ ልምድ ይዘው እንደሚመለሱ ተናግረዋል። የሲኖዶሱ ጉዞ ሁሉንም የማኅበራት አባላትን የሚያሳትፍ ቀጣይ ሂደት እንደሆነ አስረድተዋል። የመጣነው ከየትም ይሁን ከየት ሁላችንም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት በመሆናችን ሳናቋርጥ ለሰላም፣ ለስደተኞች እና ለጥገኝነት ጠያቂዎች የመጸለይ አስፈላጊነት አለ” በማለት አበክረው ተናግረዋል።

የጥሪ እውነታ

የሴት ዲያቆናት ጉዳይ እና ባለትዳር ዲያቆናት ሊኖራቸው ስለሚችል “የክኅነት” ሚናን በማስመልከት ለቀረበው ጥያቄ ብፁዕ ካርዲናል ባሬቶ ሲመልሱ፥ ይህ ሲኖዶስ በአማዞን አካባቢ አገራት ጉባኤ፥ በ7,500 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው ክልል የሚገኝ የ33 ሚሊዮን ነዋሪዎች የልምድ ውጤት እንደሆነ አስታውሰው፥ ዘጠኝ አገራትን በሚያካትት በዚህ ክልል ውስጥ 3 ሚሊዮን ቀደምት ተወላጆች ተሰራጭተው የሚኖሩበት ክልል እንደሆነ ገልጸው፥  የዚህ ክልል አስፈላጊ ገጽታ የተጠመቁትን ሁሉ የሚያካትት የአማዞን አካባቢ አገራት ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤን መምስረት እንደሆነ ተናግረውሳል። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው የሆነውን ይህንን ልምድ መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ብጹዕ አቡነ ኦቨርቤክ ይህን በመግለጽ፥ በጀርመን ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ሂደት ላይ የተነሱት ጥያቄዎች፥ ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ በድህረ ዓለማዊነት አስተሳሰብ ውስጥ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ የሌለበት እና ሃይማኖትም በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ምንም ዓይነት ትርጉም የሌለበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል። ጀርመን ውስጥ ከፕሮቴስታንት ፓስተሮች መካከል ግማሾቹ ሴቶች መሆናቸውን እና ቋሚ ዲያቆናት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1968 ዓ. ም ጀምሮ እንደነበሩ፥ ሴቶች በዲቁና አገልግሎት ውስጥ ስለሚኖራቸው ሚና እና ስለወደፊቱ ቆይታቸው ጥያቄዎች እየተነሱ መሆናቸውን በመግለጽ የቋሚ ዲያቆናት አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው፥ የድቁና ሕይወት ጥሪ ብቻ ሳይሆን መብትም ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል።

የጀርመን ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ አካሄድ አሁን ባለው ሲኖዶስ እና በጀርመን ሲኖዶስ ስላለው ተጽእኖ ተጠይቀው ሲመልሱ፥ በጀርመን ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ጉዞ ውስጥ የተደረገው ሁሉ በኅብረተሰቡ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ገልጸው፥ የወንጌል ባሕልን በማስረጽ ትምህርት ላይ ማሰላሰል እንደሚያስፈልግ እና የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ነገረ መለኮት ሚና ሊጫወት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ባለ ትዳር ወንዶችን ለክኅነት አገልግሎት መሾም የሚቻልበትን ሁኔታ በተመለከተ፥ ለብዙ ዓመታት እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን አስታውሰው፥ ለክኅነት አገልግሎት የሚዘጋጁ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎችን ማጣት የቤተ ክርስቲያን ምስጢራትን የማስቀጠል ተግዳሮት ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ የመኖር ፈተና ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።

 

 

23 October 2023, 18:34