ፈልግ

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ የጉባኤውን የውይይት ርዕሦች በማስመልከት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ የጉባኤውን የውይይት ርዕሦች በማስመልከት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ  (Vatican Media)

የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ በስደተኞች፣ በሴቶች እና በድሆች ጉዳይ ላይ ትኩረት አድርጎ መዋሉ ተገለጸ

በቫቲካን ውስጥ እየተካሄደ ያለው 16ኛው የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ዓርብ መስከረም 25/2016 ዓ. ም. ባደረገው ውይይት ስደተኞችን፣ ሴቶችን እና ድሆችን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረጉ ታውቋል። ይህን ለጋዜጠኞች የተናገሩት የሲኖዶሱ ጉባኤ መረጃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አቶ ፓውሎ ሩፊኒ ሲሆኑ፥ በትናንሽ የውይይት ቡድኖች የተከፈሉ የጉባኤው ተሳታፊዎች ለውይይት በቀረቡት፣ መንፈሳዊ ስልጠና፣ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቤተሰብ እና ጾታዊ ጥቃትን በማስመልከት ለውይይት በቀረቡት ርዕሠ ጉዳዮች ላይ ነፃ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓርብ መስከረም 25/2016 ዓ. ም. በሲኖዶሱ መካከል ትኩረት ከተሰጣቸው መሪ ሃሳቦች መካከል፥ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎችን ለክኅነት አገልግሎት ከማዘጋጀት ጥረት ጀምሮ ካኅናትን፣ ምእመናን እና የትምህርተ ክርስቶስ መምህራንን ማሰልጠን፥ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቤተሰብ ሆና ሁሉም ሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቦታ እንዳለው፥ ጸሎት፣ ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚጫወቱት ሚና፥ የምእመናን፥ ለሐዋርያዊ አገልግሎት የተቀቡ እና ያልተቀቡ አገልጋዮች ሚና፥ የቅዱስ ቁርባን እና የእግዚአብሔር ቃል ማዕከላዊነት፣ ድሆች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላላቸውን ተፈላጊነት በተመለከተ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። ስደትን በተመለከተ ስቃይ ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች ግንባር ቀደም እንደነበር የገለጹት የሲኖዶሱ ጉባኤ መረጃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፥ በጦርነት ወቅት የማያባራ መከራን በመቀበል ላይ የሚገኙ የዩክሬናውያንን ታሪክ በማዳመጥ የጉባኤው ተሳታፊዎች ማጨብጨባቸውን ገልጸዋል።

በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ዓርብ መስከረም 25/2016 ዓ. ም. ለጋዜጠኞች ዕለታዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ ከላይ የተጠቀሱ ርዕሠ ጉዳዮችን በማስመልከት ዝርዝር መረጃዎችን ለጋዜጠኞች አጋርተዋል። ዓርብ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ከሰዓት ድረስ ባለው ጊዜ በተካሄደው ውይይት ላይ 351 የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ተሳታፊ እንደሆኑ እና በ35 አነስተኛ ቡድኖች ተከፋፍለው ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ ከጉባኤው መካከል በየቀኑ የሚመነጩ ዋና ዋና የውይይት ውጤቶችን ይፋ ለማድረግ ከጋዜጠኞች ጋር የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

18 ሪፖርቶች ቀርበው 22 ግለሰቦች ንግግር አድርገዋል

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ዓርብ መስከረም 25/2016 ዓ. ም. ሰዓት በኋላ እንደገለጹት፥ ውይይቱ በትናንሽ ቡድኖች ሲካሄድ ቆይቶ የመጀመሪያ ክፍልን ወደ ምሽት ማጠናቀቁን አስረድተዋል። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተገኙበት ለሁለት ጊዜያት ተከፍሎ ውይይት እንደተደረገ እና በመጀመሪያው ውይይት ማጠቃለያ 18 የተለያዩ ቡድኖች ተወካዮች ሮፖርታቸውን አቅርበው እንደነበር ገልጸው፥ በሁለተኛው ክፍለ ጊዜ 22 አባላት ንግግር ማድረጋቸውን ዶ/ር ፓዎሎ ሩፊኒ ገልጸዋል። በጉባኤው ተካፋዮች በኩል በቀረቡት ንግግሮች መካከል አራት ደቂቃን የወሰደ የዝምታ ጸሎት ተደርጎ እንደነበር አስረድተዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግር የያዘ መጽሐፍ

ከሰዓት በኋላ በተደረገው የሦስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ፥ የቫቲካን አሳታሚ ድርጅት በሦስት ቋንቋዎች እንደርሱም በጣሊያንኛ፣ በእንግሊዘኛ እና በስፓኒሽ ቋንቋዎች ያሳተማቸው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሁለት ንግግሮችን የያዘ አዲስ መጽሐፍ ለእያንዳንዱ የጉባኤው አባላት መታደሉን ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ተናግረዋል። አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1991 ዓ. ም. “የእግዚአብሔር ጸጋ ከውስጣዊ ሙስና ያድነናል” በሚል አርዕስት የጻፉትን የመጀመሪያን ርዕስ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በነሐሴ 2023 ዓ. ም. ለሮም ሀገረ ስብከት ካኅናት ያስተላለፉትን መልዕክቶች ያካተተ እንደሆነ ተመልክቷል።

ልዩነት እና አብሮ የመጓዝ ፍላጎት

የሲኖዶሱ መረጃ ኮሚሽን ጸሐፊ ወ/ሮ ሼላ ፒሬስ፥ ሲኖዶሳዊ ውይይት በማለት በገለጹት ድባብ ውስጥ ለመገኘት የተለያዩ አነስተኛ የውይይት ቡድኖች እርስ በርስ መተዋወቅ እንደጀመሩ ተናግረው፥ በእርግጥ አብረን እየተራመድን እንገኛለን ብለዋል። የውይይት ድባቡ ምንም እንኳን ውጥረት ቢታይበትም ከሁሉም በላይ ደስታ ያለበት ነበር በማለት ተናግረዋል። በደቡብ አፍሪካ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ረጅም የማኅበርዊ ግንኙነት ልምድ ያላቸው ሞዛምቢካዊ ሼላ ፒሬስ፥ በጣም አስገራሚው ገጽታ ከተለያዩ አኅጉራት የተውጣጡ አባላትን በእያንዳንዱ ቡድን ውስጥ በመሰብሰባቸው፥ ልዩነት ቢኖርም የወንድማማችነት መንፈስ እና አብሮ የመጓዝ ፍላጎት የነበረበት ውይይት እንደነበር አስረድተዋል።

አብሮነት እና የጓደኝነት ትስስር

ወ/ሮ ፒሬስ እንደ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ሁሉ፥ በእነዚህ ሁለት ክፍለ ጊዜያት ውስጥ የተነሱትን አንዳንድ ጭብጦች ዘርዝረው፥ በተለይም “ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም የምትቀበል ቤተሰብ ናት” ለሚለው ሃሳብ አፅንዖት ሰጥተዋል። ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በተደጋጋሚ ካቀረቧቸው ጭብጦች መካከል አንዱ ነበር ያሉት ወ/ሮ ፒሬስ፥ የክርስቲያኖች አንድነት እና ሃይማኖቶች የጋራ ውይይቶች፥ እንዲሁም ለወጣቶች እውቅና መስጠት እና የሴቶች ተሳትፎ አስፈላጊነትን በማስመልከት ጠዋት በተካሄደው የውይይት መድረክ በተቻለ መጠን ሁሉን ለማሳተፍ ጥረት ያደረገ እንደነበር አበክረው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት፥ ሁሉም ነገር የዚህ ሂደት አካል እንደሆነ ተናግረው፥ በዚህ የሲኖዶስ ጉባኤ ቅድሚያ የሚሰጠው ማዳመጥ እንደሆነ እና ማዳመጥ ሲባል ማዳመጥን መማር እንደሆነ በማስረዳት፥ የሲኖዶሱ የመጀመሪያ ቀናት መሪ መርሆች ከብዙ የጸሎት ጊዜያት ጋር የተገናኙ እና ቆም ብሎ ለማሰላሰል እና ለማስተዋል የሚረዱ ቀናት እንደነበሩ ወ/ሮ ፒሬስ አስረድተው፥ የጓደኝነት ትስስርን ማጠናከር ያስፈልጋል በማለት ዶክተር ፓውሎ ሩፊኒ ያቀረቡትን ሃሳብ አጠናክረዋል።ከትናንሽ የውይይት ቡድኖች ውስጥ የተገኙ ጓደኝነቶች መኖራቸውን የገለጹት ወ/ሮ ፒሬስ፥ እርስ በርስ ተገናኝተን ቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋትን ለመረዳት ራሳችንን መስጠት ይገባል ብለዋል። በእርግጥ ችግሮች እንደነበሩ እና ሁልጊዜም እንደሚኖሮ የተናገሩት ወ/ሮ ፒሬስ፥ ነገር ግን ብዙ መሰናክሎች እንደሚወገዱ የማመሳከሪያው ነጥብም መከራን የተቀበለው የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋ ይሆናል” ሲሉ አክለዋል።

ውይይት የተደረገባቸው ርዕሶች

የሲኖዶሱ ጉባኤ መረጃ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አቶ ፓውሎ ሩፊኒ በዝርዝር እንደተናገሩት፥ በትንንሽ የውይይት ቡድኖች ውስጥ ትኩረት የተደረገው እንደ ቀኖና ሕግ፣ የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች እና እንደገናም ስልጠና በመሳሰሉት የቤተ ክርስቲያን አወቃቀሮችን በሚመለከቱ ጭብጦች ላይ ውይይቶች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።

የቀወድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊን በመጥቀስ፥ ቤተ ክርስቲያን "በሁለት ሳንባዎች" መተንፈስ እንዳለባት የተናገሩትን ታሪካዊ ሐረግ በመጥቀስ፥ በምሥራቅ-ምዕራብ ቤተ ክርስቲያናት ግንኙነት ጭብጥ ላይ ትኩረት እንደተሰጠ ገልጸዋል። የስደት ክስተትን በተመለከተ፥ ስደተኞችን በመደገፍ አስፈላጊነት እና የብጹዓን ጳጳሳት እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለስደተኞች የሚያደርጉት ድጋፍ መሠረታዊ መሆኑ በድጋሚ ጠቅሰዋል። ሴቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን ሚና በተመለከተ የሴቶችን ሚና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚለው፣ ወጣቶችን እና ድሆችን በተመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ውይይት ተደጎ ይህን በተመለከተ በተወሰነ ደረጃ የሚታየው መቀዛቀዝ እንዲወገድ ማሳሰቢያ ተሰጥቶበታል።

 

07 October 2023, 17:41