ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ገብርኤሌ ካቺያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ንግግር ሲያደርጉ ሊቀ ጳጳስ ገብርኤሌ ካቺያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ንግግር ሲያደርጉ 

ቅድስት መንበር የአገር በቀል ቅርሶችን እና ባህሎችን አለመቀበል አንዱ ‘የጥቃት ዓይነት’ ነው አለች

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት የአካባቢ ተወላጆችን ክብር እና መብት እንዲጠብቁ እና ለአካባቢ ጥበቃ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ እንዲያደንቁ ቅድስት መንበር አሳስባለች።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ገብርኤሌ ካቺያ ሰኞ ዕለት በኒውዮርክ ለተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ የአገሬው ተወላጆች መብትን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
የጣሊያን ተወላጅ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ ገብርኤሌ የአገሬው ተወላጆች ባህሎች፣ ቋንቋዎች፣ ወጎች እና መንፈሳዊነት የመጠበቅን አስፈላጊነት አጉልተው አንስተዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት በአካባቢ ጥበቃ እና የባህል ቅርስ ጉዳዮች ላይ የአገሬው ተወላጆች ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና እንዲሰጡም ጋብዘዋል።

የአካባቢ ጥበቃ

ሊቀ ጳጳስ ካቺያ የአገሬው ተወላጆች ከአካባቢው ጋር ላሳዩት ተስማምቶ የመኖር ዝንባሌ እና የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ “የሥርዓተ-ምህዳርን የመቋቋም አቅም በማጎልበት” ያላቸውን ሚና አመስግነዋል።
የአገሬው ተወላጆች መሬቶች ከፍተኛውን የዓለም ብዝሃ ህይወት ክፍል በመጠበቅ ረገድ ያበረከቱት አስተዋጽኦ የስነ ምህዳር ጠባቂ እንዲሆኑ ማድረጉን ጠቁመዋል።
ሊቀ ጳጳሱ ከአገሬው ተወላጆች ምክክርና ፈቃድ ውጭ ጥበቃ የሚደረግላቸው ቦታዎች ስለመቋቋሙ ስጋታቸውን አንስተዋል። ይህንንም ሲያብራሩ “ይህ ለተጨማሪ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ለምሳሌ እንደ ህገወጥ ዝውውር፣ የግዳጅ ስራ እና ወሲባዊ ብዝበዛ ሊያጋልጣቸው ይችላል” ብለዋል።

ለአገሬው ተወላጆች ባህል አክብሮት

በተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ተወካይ በተጨማሪም እንደገለፁት “በባህላዊ ትርጉም ያለው እውቀትን፣ ልምዶችን፣ ተግባራትን፣ እቃዎች እና ቦታዎችን” የሚያጠቃልለውን የአገሬው ተወላጆች ባህላዊ ቅርሶችን ማክበር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የአገሬው ተወላጆች መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች ሲከበሩ ግልጽ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺኮስን ሐዋርያዊ መግለጫ የሆነውን ‘ኩዌሪዳ አማዞኒያ’ (Querida Amazonia) በመጥቀስ “ሙሉ በሙሉ ከውጪ ተጽዕኖ የተዘጋ፣ ታሪካዊ፣ የማይለዋወጥ ‘አገር በቀል’ ማንኛውንም ዓይነት ቅይጥ የማይቀበል የመግባቢያ ባህል ማራመድ አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

አለመቻቻልን ማሸነፍ

ወደ ዘላቂነት የለሽ ቱሪዝም ጉዳይ ስንመለስ ሊቀ ጳጳስ ካቺያ የሀገር በቀል ተወላጆችን ባህልን የሚጎዱ እንዲሁም መሬታቸውን እና ሀብታቸውን ለመቀራመት የሚዳርጉ ተግባራት ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
ተፈጥሯዊና ማህበራዊ ስነ-ምህዳሮችን የሚያከብር እና በአገር በቀል ህዝቦች ላይ ወጥ የሆነ የአኗኗር ዘይቤ የማይጭን ዘላቂ ቱሪዝም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ሊቀ ጳጳስ ገብርኤሌ ካቺያ በማጠቃለያቸው የአገሬው ተወላጆች መብት፣ ባህላዊ ቅርሶቻቸው እና የአካባቢ ጠባቂነት ሚናቸው እንዲጠበቅ በማሳሰብ ፥ “የአገሬው ተወላጆች ታዋቂ ባህሎችን አለመቀበል እና አለማክበር የጥቃት ዓይነት ነው ፥ ይህም ቀዝቀዝ ባለ ሁኔታ የሚፈፀም እና በፍርጃ ላይ የተመሠረተ ነው ፥ ይህ ደግሞ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።
 

12 October 2023, 16:45