ፈልግ

የብሔራዊ ጦር ወታደሮች በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዕቃዎችን የሚያጓጉዙ ሲቪል ተሽከርካሪዎችን ሲያጅቡ የብሔራዊ ጦር ወታደሮች በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዕቃዎችን የሚያጓጉዙ ሲቪል ተሽከርካሪዎችን ሲያጅቡ  (AFP or licensors)

ቅድስት መንበር በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚፈፀመውን ጥቃት አወገዘች

በጄኔቫ ለተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ተልዕኮ ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሞንሲኞር ጆን “በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው አሳሳቢ የሰብአዊ መብት ሁኔታ በጣም ያሳስበናል” ብለዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ሞንሲኞር ጆን ፑዘር በ54ኛው የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ እንዳሉት ቅድስት መንበር “በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ስላለው አስደንጋጭ የሰብአዊ መብት ሁኔታ በጥልቅ አሳስቧታል” ብለዋል። ቅድስት መንበርን በመወከል ሞንሲኞር ፑዘር እንደተናገሩት ቅድስት መንበር “ሁሉንም የዓመፅ ድርጊቶች እንደምታወግዝ ፥ በተለይም ለሕይወት መጥፋት ወይም ለፆታዊ ጥቃት የሚዳርጉትን ድርጊቶች እንደምትኮንን” ገልፀዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን በጎበኙበት ወቅት የታጣቂ ቡድን ጥቃቶችን፣ እልቂቶችን፣ አስገድዶ መድፈርን፣ የመንደሮች መውደምና መወረርን፣ የእርሻና የቀንድ ከብቶችን ዘረፋን አውግዘው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው በማለት አስታውሰዋል።

አሳሳቢ ጉዳዮች

በጄኔቫ ለተባበሩት መንግስታት የቅድስት መንበር ተልዕኮ ቋሚ ታዛቢ የሆኑት ሞንሲኞር ፑዘር ሲናገሩ ፥ ህፃናትን ለወታደርነት መመልመልን ጨምሮ በታጣቂ ቡድኖች የሚሰነዘረው ጥቃት እየጨመረ መሄዱን እንዲሁም በብሄራዊ ጦር ሰራዊቱ የሚፈፀሙ ጥቃቶችም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ገልጸዋል።
የዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ቡድን ያቀረበው ምክረ ሀሳብ የሆነውን የናይሮቢ እና የሉዋንዳ የሰላም ስምምነት ትግበራን ሁሉም ባለድርሻ አካላት እና የታጠቁ ቡድኖች ውጤታማ የሆነ ትጥቅ መፍታትን እንዲያረጋግጡ እና 'በፍጥነት እንዲተገብሩ’ ቅድስት መንበር እንደምትደግፍ ተናግረዋል።
ሞንሲኞር ፑዘር አክለውም ቅድስት መንበር በክርስቲያን ማህበረሰቦች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በማሳየት “የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተለይ የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች (ADF) ተደጋጋሚ ጥቃቶች እና እያደገ የመጣውን አክራሪነት የሚያደርሰውን ከባድ ስጋት አቅልሎ እንዳይመለከት አሳስባለች” ብለዋል።
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቀጠለውን “አጠቃላይ ወንጀለኛን ነፃ የማውጣት” ሁኔታ አጉልተው በመግለጽ ፥ “ብዙ የሰብአዊ መብት ረገጣ ሰለባዎች ፍትሃዊ ወይም ፈጣን የፍርድ ሂደት አያገኙም” በማለት የሃገሪቱን የፍርድ ሂደት ተችተዋል።

መጪው ምርጫዎች

ሞንሲኞር እንዳሉት የመጪውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በመጠባበቅ ላይ ላለችዋ ሃገር ቅድስት መንበር “ሁሉም የኮንጐ ዜጎች የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በአስተማማኝ፣ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ ሁኔታ የመግለጽ መብት እንዲኖራቸው የማረጋገጥ አስፈላጊነትን በድጋሚ ገልጻለች” ብለዋል።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጳጳሳት ኮንፈረንስ እና ሌሎች ድርጅቶች ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢዎችን በማሰልጠን ላይ ያከናወኗቸውን ተግባራት ገልጸው “መጪው ምርጫ ተዓማኒነት ያለው፣ ግልጽ እና ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሆን እንዲህ አይነት ተዋናዮች ወሳኝ ይሆናሉ” ብለዋል። በተጨማሪም የኮንጎ ባለስልጣናት “በዚህ ወሳኝ ወቅት የሁሉንም ሰው ደህንነት እና የፖለቲካ ነፃነት እንዲያረጋግጡ” ጠይቀዋል።
ሞንሲኞር ፑዘር ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ይህችን አገር ለብዙ አሥርተ ዓመታት የእርስ በርስ ግጭቶች ያስከተሉትን ደም መፋሰስ ልንለምድ አንችልም፤ ይህም በሌሎች ቦታዎች በአብዛኛው የማይታወቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕይወቶች መጥፋትን አስከትሏል። እዚህ እየሆነ ያለው ነገር መታወቅ አለበት። እኔ በጣም የማበረታታውን አሁን ያለውን የሰላም ሂደት በተጨባጭ ተግባራት ሊታዩ ይገባል ፥ ቃል ኪዳኖችም ሊጠበቁ ይገባል” ብለው ያሰሙትን ንግግር በማስታወስ ነው።
 

12 October 2023, 15:20