ፈልግ

የኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ግጭት የኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ግጭት   (AFP or licensors)

ቅድስት መንበር በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የሚፈጸመውን ጥቃት በጽኑ አወገዘች

ጄኔቫ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ እና መልዕክተኛ ብጹዕ አቡነ ጆን ፑዘር፥ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ያለው አሳሳቢ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ቅድስት መንበርን እጅግ ያሳሰባት መሆኑን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አቡነ ጆን ፑዘር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 54ኛ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፥  በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ያለው አስደንጋጭ የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ቅድስት መንበርን በጥልቅ እንዳሳሰባት ገልጸዋል።

አቡነ ጆን በንግግራቸው ቅድስት መንበር ሁሉንም ዓይነት የዓመፅ ድርጊቶችን እንደምታወግዝ፥ በተለይም ለሕይወት መጥፋት እና ለፆታዊ ጥቃት የሚዳርጉ ድርጊቶችን እንደምትኮንን ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በያዝነው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት መግቢያ ላይ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የመሣሪያ ጥቃቶችን፣ እልቂቶችን፣ አስገድዶ መድፈርን፣ መንደሮችን ማውደም እና መወረርን፣ የእርሻና የቀንድ ከብቶች ዘረፋን ማውግዛቸውን ጠቅሰዋል።

እጅግ አሳሳቢ ጉዳዮች

በጄኔቫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ እና መልዕክተኛ የሆኑት አቡነ ጆን ፑዘር ለጉባኤው ባሰሙት ንግግር፥ ሕፃናትን ለውትድርና አገልግሎት መመልመል እና በታጣቂ ቡድኖች የሚሰነዘሩ ጥቃቶች እየጨመሩ መሄዳቸው፥ እንዲሁም በብሔራዊ ጦር ሠራዊት በኩል የሚፈጸሙ ጥቃቶች ቅድስት መንበርን እንዳሳሰባት ገልጸው፥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የናይሮቢ እና የሉዋንዳ የመፍትሄ ሃሳቦችን በፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና ሁሉም የታጠቁ ቡድኖች ትጥቃቸውን መፍታታቸውን እንዲያረጋግጡ በማለት የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ቡድን ያቀረበውን ሃሳብ ቅድስት መንበር እንደምትደግፍ ተናግረዋል።

አቡነ ጆን ፑዘር አክለውም፥ ቅድስት መንበር በክርስቲያን ማኅበረሰቦች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በማስመልከት "የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ተከታታይ ጥቃቶች እና እያደገ የመጣው አክራሪነት የሚያደርሰውን ከባድ ስጋት አቅልሎ መመልከት እንደማይገባ ማሳሰቧን ተናግረዋል። በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የቀጠለውን አጠቃላይ የወንጀል ቅጣት ሁኔታ አጉልተው ገልጸው፥ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሰለባዎች ፍትሃዊ እና ፈጣን የፍርድ ሂደት እንደማያገኙ ተናግረዋል።

መጪዎቹ ምርጫዎች

ቅድስት መንበር፥ መጪዎቹ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ሁሉም የኮንጐ ዜጎች ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውን አስተማማኝ፣ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መንገድ የመግለጽ መብት እንዲኖራቸው የማረጋገጥ አስፈላጊነትን በድጋሚ መግለጿን አቡነ ጆን ፑዘር ተናግረዋል።

የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጳጳሳት ጉባኤ እና ሌሎች ድርጅቶች ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢዎችን በማሰልጠን ላይ ያከናወኗቸውን ተግባራት ገልጸው፥ "መጪው ምርጫ ተዓማኒነት ያለው፣ ግልጽ እና ሁሉንም ያሳተፈ እንዲሆን፣ እንደነዚህ ዓይነት ተዋናዮችን ማሳተፍ ወሳኝ ይሆናል" ብለዋል። በተጨማሪም የኮንጎ ባለስልጣናት “በዚህ ወሳኝ ወቅት የሁሉንም ሰው ደህንነት እና የፖለቲካ ነፃነት እንዲያረጋግጡ” በማለት ጠይቀዋል።

ብጹዕ አቡነ ጆን ፑዘር ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባሰሙት ንግግር፡- “ይህችን አገር ለአሥርተ ዓመታት የደረሰውን የደም መፍሰስ ልንለምድ አንችልም፤ ይህም በሌሎች አካባቢዎች እና በአብዛኛው የማይታወቁ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የሕይወት መጥፋትን አስከትሏል። እዚህ እየሆነ ያለው ነገር መታወቅ አለበት። በጣም የማበረታታው አሁን ያለው የሰላም ሂደት በተጨባጭ በተግባር ሊቀጥል ይገባል፤ ቃል ኪዳኖችም ሊጠበቁ ይገባል” ማለታቸውን፥ ጄኔቫ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ እና መልዕክተኛ ብጹዕ አቡነ ጆን ፑዘር ጠቅሰዋል።

 

10 October 2023, 17:33