ፈልግ

16ኛ የጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ 16ኛ የጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ  

በሲኖዶሳዊነት ላይ የሚከናወነው ሲኖዶስ የሐሙስ እለት ጋዜጣዊ መግለጫ!

ሐሙስ ጥቅምት 15/2016 በሲኖዶሳዊነት ላይ የሚከናወነው 16ኛው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጳጳሳት መደበኛ ሲኖዶስ የእለቱን ወሎ የሚያመልከት መግለጫ ይፋ ማደረጉ የተገለጸ ሲሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ጉልህ የሆነ “ምሁራዊ” ባህሪ ነበረው፣ የክርስቲያናዊ አንድነትን የሚያበረታታ ነው ሲሉ የክርስቲያናዊ ሕብረትን የሚያስተዋውቀው ጳጳሳዊ ጽህፈት ቤት ዋና አስተዳዳሪ እና ሁለት የካቶሊክ እምነት ተከታይ ያልሆኑ “የወንድማማችነት ተወካዮች” በውይይቱ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የእዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

ሐሙስ ዕለት በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የቫቲካን ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ፕሬዚደንት እና የኢንፎርሜሽን ኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ እና የዚሁ ኮሚሽን ፀሃፊ የሆኑት ሺላ ፒሬስ አጠቃላይ ጉባኤው በአሁኑ ጊዜ በተቀናጀው ሰነድ ላይ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ትላንትና ከሰአት ለእግዚአብሔር ሕዝብ የተላከው መልእክት ከፀደቀ በኋላ ቅዳሜ የመጨረሻ ሰነድ ይፋ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ወይዘሮ ሺላ ፒሬስ የነጻ ንግግር ንዝረት

"ትላንት ከሰአት በኋላ የ16ኛው የጳጳሳት ጉባኤ ሲኖዶስ አካል የሆነ የአስራ ስምንተኛው ቀን እለታዊ ጠቅላላ ጉባኤ 348 አባላት በተገኙበት ተካሂዶ በመጀመሪያ ለእግዚአብሔር ህዝብ የተላከውን መልእክት ላይ ድምጽ ሰጥተናል" ሲሉ የተናገሩ ሲሆን “እያንዳንዱ አባል የቀረቡትን የኮፒውተር ታብሌቶች በመጠቀም ድምጽ ሰጥተዋል። ጥያቄው ‘የሲኖዶሱን መልእክት እጸድቃለሁ ወይ?’ የሚል ነበር በድምጽ ብልጫ 336 የድጋፍ እና 12 ተቃውሞዎች ድምጽ የተሰጠበት ጉዳይ እንደ ነበረ አክለው ገልጸዋል። እንደምታውቁት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ግልጽ በሆኑ ውይይቶች ውስጥ ተሳትፈዋል ”ሲሉ ወይዘሮ ሺላ ፒረስ ተናግሯል።

“በነጻነት በተደርገው ነጻ ውይይት ቤተክርስቲያን ሚስዮናዊ ድፍረት እንደሚያስፈልጋት ጎላ አድርገው ገልጸዋል፣ እና ከኢየሱስ ጋር የተደረገው ግንኙነት የእምነት እና የሚስዮናዊነት ግለት ማዕከል እንደሆነም ተጠቅሷል። ቤተክርስቲያን በወንጌል አዋጅ ላይ የተመሰረተች ናት፣ እናም አንድ ሰው ከተልእኮው ተነጥሎ ስለ ቤተክርስቲያን ማሰብ አይችልም ሲሉ አክለው ገለጸዋል።

ወይዘሮ ፒሬስ በመቀጠል “ስለ ጸሎት እና የጸሎት ቡድኖች አስፈላጊነትም ተነግሯል። የምስጢረ ቁርባን እና የእርቅ ምስጢር የሆነው የምስጢረ ንስሐ መሰረታዊ ጠቀሜታ በድጋሚ ተረጋግጧል ያሉ ሲሆን የሲኖዶሳዊው ሥርዓተ አምልኮ፣ ሲኖዶሳዊነት እንደ ሥርዓተ አምልኮ፣ ሲኖዶስ ደግሞ በስርዓተ አምልኮ የእናትነት ሚና የሚጫወት ቦታ መሆኑ አጽንዖት ተሰጥቶበታል ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ወይዘሮ ፒረስ በላቲን ቋንቋ “ሴንሱስ ፊዴይ [የእምነት ስሜት] አስፈላጊነት ጎላ ተደርጎ መገለጹን ዘግበዋል። ስለሴቶች አድናቆት እና ከኢየሱስ ጋር ስለነበሩት ብዙ ሴቶች የመጥቀስ እድል እንደ ነበረ የተናገሩት ሺላ ፒረስ ቤተክርስቲያንን ማዳመጥ በተመለከተ የሴቶችን የተለመደ የማዳመጥ፣ የማጽናናት፣ የመምከር ችሎታም ትኩረት ተሰጥቶበታል። ሴቶች የቤተክርስቲያን ተገዥ ሳይሆኑ የቤተክርስቲያን አካል መሆን አለባቸው ተብሎም ተነግሯል ሲሊ አክለው ገልጸዋል።

ወይዘሮ ፒሬስ "ጥቃቶች አካላዊ ብቻ አይደሉም” የሚለው ጉዳይ እንደተነሳም ጠቅሷል። ከዚያም “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽንሰ-ሐሳብ አስፈላጊነት አጽንዖት ተሰጥቶት ነበር፡ ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥቱ እንጂ ለራሷ አይደለችም። በዚህ ምክንያት ቤተክርስቲያን ሁሉንም መቀበል አለባት የሚል ሐሳብ እንደ ተነሳም አክለው ገልጸዋል።

በጉባኤው ላይ በተደረገው ውይይት “ሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ አስተምህሮ እና የትርጓሜ ትምህርት ዋቢ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል። ስለ ክርስቲያናዊ አንድነት ታላቅ ተልዕኮ፣ ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ስለመነጋገር እና ከማያምኑ ሰዎች ጋር ስላለው ግንኙነት ተነግሮ ነበር ሲሉ አስታውሰዋል።

"የዓለም አቀፉ ሰሜናዊ ወደ ዓለም አቀፋዊው ደቡብ የባህል ቅኝ ግዛት ዓይነቶች" በጉባኤው ውስጥ የተነሱት ሌላው ጉዳይ እንደ ነበረ የገለጹት ሺላ ፒሬስ እንዲሁም "ቤተክርስትያን በአለም ቀውሶች ውስጥ መገኘቷን ማጉላት አስፈላጊ ነው፣ ቤተክርስቲያን ከዓለም ውጭ አይደለችም እና እየሆነ ያለውን ነገር ችላ ማለት እንደማትችል ይነገር ነበር-ጦርነት እና የሰላም ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ በእዚህ የሲኖዶሳዊነት ላይ የተካሄደው ሲኖዶስ ጉባሄ በከፍተኛ ደረጃ የተነጋገረበት አርእስት ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ አንፃር አሉ ሺላ ፒረስ “ልጆቻቸውን እንዴት ማሳደግ እና ማስተማር እንዳለባቸው አሁንም መረዳት ያለባቸው ሰዎች በግጭቶች እና በከፋ ልዩነት ሁኔታዎች ውስጥ ህጻናት በየእለቱ በሚሞቱበት እውነታ ላይ የሚደርስባቸው ስቃይ ሁኔታም ተጠቅሷል ያሉ ሲሆን በተጨማሪም “ድሆችን በቤተክርስቲያኗ የጉዞ ማእከል እንዲያደርጉ የቀረበው የወንጌል ጥያቄ አጽንዖት ተሰጥቶት ነበር፡ የክርስቲያናዊ ገጽታ እንጂ ማህበራዊ ጉዳይ አይደለም ያሉት ፒረስ በመጨረሻ መጪው የውህደት ሰነድ የታሰበለትን የእግዚአብሔርን ህዝብ ለማበረታታት ታቅዶ የተዘጋጀ ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ሩፊኒ፡ የ"ውህደት ሰነድ" ይዘቶች እና አላማ

ዶ/ር ሩፊኒ በበኩላቸው እንደ ገለጹት ከሆነ ዛሬ ጥዋት የረቂቁን የወህደት መገለጫ በመመርመር በትናንሽ ክብ ጠረጴዛዎች ዙሪያ የጀመረው የጋራ 'modi' [ማሻሻያ] በውህደት ሰነዱ ማሻሻያዎች ተደርገው እንደ ነበረ የገለጹ ሲሆን በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ 349 ተሳታፊዎች በጉባኤው ተገኝተዋል ብለዋል።

ዛሬ ጠዋት "በክብ ጠሬጴዛ ዙሪያ ሥራ ከመጀመሩ በፊት ከጸሎቱ በኋላ አጠቃላይ ሰነድ አርቃቂ ኮሚሽኑ ቅዳሜ ለድምጽ የሚቀርበውን ሰነድ መሰረት የሆኑትን መስፈርቶች ለጉባኤው አካፍሏል  ያሉ ሲሆን አሁን እየመረመርን ነው” ሲሉ ዶክተር ሩፊን አክለው አስረድተዋል። “የሲኖዶሱ ውጤት ሆኖ ለሊቀ ጳጳሱ የሚቀርበው ሰነድ በሚቀጥለው ጉባኤ እ.አ.አ በጥቅምት 2024 የሚጸድቅ ይሆናል” ሲሉ አብራርተዋል።

ሩፊኒ እንዳሉት ዋና አላማው ያለንበትን እንድንረዳ፣ በእነዚህ የማስተዋል ሳምንታት የተነገረውን እንድናስታውስ እና በስርጭቱ ሂደት በዚህ ሲኖዶስ መጀመሪያ ላይ የጀመረውን እና የሚያበቃውን ጉዞ እንደገና ለመጀመር ነው። እ.አ.አ በጥቅምት 2024 በተለይም “ሰነዱ የላቀ ማስተዋል የምያስፈልጋቸውን እና ተጨማሪ ጥናት የሚሹ ነጥቦችን መያዝ አለበት። ሁሉንም ነገር በታማኝነት መወከል አለበት። በክብ ጠረጴዛ ሂደት ላይ ነን። ጉባኤው የእግዚአብሔር ሕዝብ ሲደመጥ የራሳቸውን ማስተዋል ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ ይመለሳሉ የሚል እንድምታ የያዘ ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ዶክተር ሩፊኒ "ይህ ጉዞ ነው እና በእርግጠኝነት በሰነዱ ተፈጥሮ እና አጭርነት ምክንያት - 40 ገጾች ብቻ ነው ያሉት፣  የ100 ወይም 200 ገፆች አላፊ ጽሑፍ መኖሩ ትርጉም የለውም - ሁሉንም ዝርዝሮች ሊይዝ አይችልም። ቋንቋው የውይይት መሆን አለበት ሲሉ የተናገሩ ሲሆን አክሎም “ሰነዱ በጉዞ ላይ ያሉትን ለማበረታታት ይጠቅማል ሁሉም የተጠመቁ፣ ምእመናን እና ዲያቆናት፣ ካህናት፣ ጳጳሳት፣ ገዳማዊያትን ይወክላል ሲሉ ተናግሯል። ጉዞውን ስለጀመሩ ወይም ስለቀጠሉ ሁሉም ሰው ሊበረታታ እና ሊመሰገን ይገባል። ብዙዎች ቀድሞውንም ጉዞዋቸውን ቀጥለዋል ሲሉ ተናግሯል።

“በቤተክርስቲያኗ ውስጥ በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንድ ጊዜ የማይታዩ ብዙ የሚያምሩ ነገሮች አሉ” ሲሉ የቫቲካን የኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ኃላፊ ዶክተር ሩፊን የተናገሩ ሲሆን "ሰነዱ ለዚህ የሲኖዶስ ልምድ ጉልበት እና ደስታን ለማምጣት ማገልገል አለበት" በዚህ ረገድ “የሰነዱ አነሳሽነት ግልጽ መሆን አለበት፡- በጋራ እንዴት እንደምንራመድ ለመረዳት እና እንድንማር ይረዳናል፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሁሉንም በማካተት መፍትሄ መፈለግ አለብን” በማለት ደምድሟል። “የእግዚአብሔር ሕዝብ በእውነቱ ከነርሱ ጋር የሚጓዙ ካህናትና ምእመናን ያስፈልጓቸዋል፣ ለቀሳዊስታዊነት ሳይገዙ ማለት ነው” ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ሙሬይ፡ የወንድማማችነት ተወካዮች መገኘት አስፈላጊነት

መግለጫውን የመሩት የቅድስት መንበር የዜና ማሰራጫ ጽ/ቤት ባልደረባ ክሪስቲኔ ሙሬይ “ድርጊቱን ተከትሎ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እና ምዕመናን የተውጣጡ ወንድሞች በ16ኛው የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። ሰፋ ያለ ውክልና ለማግኘት ከአራቱ ዋና ዋና የክርስቲያን እምነቶች የተውጣጡ 12 ወንድማማች ልዑካን ተጋብዘዋል፡- ሦስቱ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ ሦስቱ ከምሥራቃውያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት፣ ሦስቱ ታሪካዊ የፕሮቴስታንት ኅብረት እና ሦስት የጴንጤቆስጤ-ወንጌላውያን ማኅበረሰቦች ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።

“በሲኖዶሱ ባህል” መሠረት፣ የወንድማማችነት ተወካዮች ተራ ታዛቢ ሳይሆኑ በተለይም በትናንሽ ክብ ጥረጴዛዎች ዙሪያ እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል። እ.አ.አ ከጥቅምት 1 እስከ 3 በተካሄደው የሲኖዶስ ዝግጅት ላይም በመንፈሳዊ ሱባሄ ላይ ተሳትፈዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ኮች፡ ክርስቲያናዊ ሕበረት ሲኖዶሳዊነት እና ተልእኮ

በዚህ ዐውደ-ጽሑፍ የክርስቲያናዊ አንድነትን የሚያበረታታ የቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሊቀ መንበር ብፁዕ ካርዲናል ኩርት ኮች ስለ ሲኖዶሱ ሥነ ምግባራዊ ገጽታ የተናገሩ ሲሆን የወንድማማች ልዑካን መገኘት የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እና የቤተ ክህነት ማኅበረሰቦች ተሳትፎ የክርስቲያን ሕብረት ልምድ ማዕከል መሆኑን እንደሚያሳይ ጠቁመው፣ “ጥምቀት አንድ የሚያደርገን፣ የክርስቲያን ማኅበረሰብ መሠረት እና የሲኖዶሳዊነት መሠረት ነው” በማለት ተናግሯል። “የጋራ ጸሎት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አብረን እንጸልያለን አብረን እንራመዳለን” በማለት የተናገሩ ሲሆን ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህ ሲኖዶሳዊ ሂደት ሁለንተናዊ መሆን እንዳለበት እና የክርስቲያን ሕበረት ጉዞው ሲኖዶሳዊ መሆን አለበት ምክንያቱም “በክርስቲያናዊ ሕበረት እና በሲኖዶሳዊነት መካከል መስማማት ስላለ” እርግጠኛ መሆናቸውን ደጋግመው ተናግረዋል። ክርስቲያናዊ የሆነ ሕብረት እንደ ሚሲዮናዊነት እንቅስቃሴ መጀመሩ መታወስ አለበት ሲሉ አክለው አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

በሲኖዶስ የወንድማማችነት ልዑክ ተገኝቶ የነበረው የምዕራብ እና ደቡብ አውሮፓ ኦርቶዶክስ የመጀመሪያ ሀገረ ስብከት ተወካይ አቶ ኢኦሲፍ በመቀጠል ተናግሯል። "የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባል እንደመሆናችን መጠን የዚህ ሂደት አካል በመሆናችን በጣም ደስ ብሎናል" በማለት ሲኖዶሳዊነት እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ላይ ማሰላሰሉ በዓለም አቀፍ የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ ውይይት የጋራ ኮሚሽን ውስጥ ለአሥር ዓመታት እንደቀጠለ አስታውሰዋል። “በዓለም ክርስቲያኖች መካከል፣ በውጥረት እና በመከፋፈል ከታወቁ ዘመናት በኋላ እውነተኛ ‘ወንድማማችነት’ እየተገነባ ነው። አንድ የሚያደርገንን አብረን እንሻለን” ሲል አረጋግጧል። አክሎም የትብብር ምሳሌ በጣሊያን ውስጥ “የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ከ300 በላይ አብያተ ክርስቲያናትን ለሮማኒያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በውሰ እንዲገለገሉበት ሰጥታለች” ብሏል። ከዚህም በላይ በአውሮፓ እና በአለም ዙሪያ በተፈጠሩት የብዙ ቅይጥ ቤተሰቦች ምስክርነት “የክርስቲያናዊ ሕብረት ሥር መሰረት ነው” ሲል አክሎ ገልጿል።

ኦንዪና፡ በጳጳሱ እና በቤተክርስቲያን የተደረገ የትሕትና ተግባር

የዓለም ጴንጤቆስጤ ፌዴሬሽን ተወካይ እና የጋና የጴንጤቆስጤ ቤተክርስትያን ፕሬዝዳንት የነበሩት ኦፑኩ ኦኒናህ በሲኖዶሱ ላይ የወንድማማችነት ልዑካን ሆነው የተገኙ ሲሆን የአለም አቀፍ የካቶሊክ እና የጴንጤቆስጤ የጋራ ኮሚሽን አባል ናቸው። “ለክርስቲያናዊ ሕበርት አካላትና ለሌሎች አብያተ ክርስቲያናት የቀረበው ግብዣ በጳጳሱ በኩል ያለውን ትሕትና የሚያሳይ ነው፤ በመሆኑም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የጳጳሱንና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የትሕትና ድርጊት የሚያመለክት ነው” ስሉ በአድናቆት ተናግረዋል። የሲኖዶሱ ሂደት፣ “በጣም አካታች፣ ግልጽ እና ሰዎች ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ እኩል እድል የሚሰጥ ነው” ሲሉም አክለለው የገለጹት  የዓለም ጴንጤቆስጤ ፌዴሬሽን ተወካይ እና የጋና የጴንጤቆስጤ ቤተክርስትያን ፕሬዝዳንት የነበሩት ኦፑኩ ኦኒናህ በተጨማሪም “የእያንዳንዱ ሰው አስተያየት በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይቆጠራል ይህ “በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የታየ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ የብስለት ምልክት ነው” ስሉ በሲኖድሱ ላይ በመሳተፋቸው የተሰማቸውን እርካታ እና ደስታ በስሜት ታጅበው ገልጸዋል።

ሊቀ ጳጳስ ጋዳሲኪ፣ የውይይት ዘዴ

የፖዝናን ሊቀ ጳጳስ እና የፖላንድ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ስታኒስላው ጋዳሲኪ ስለ ተሞክሯቸው ተናግረው ምንም እንኳን ሌሎች ክርስቲያኖችን፣ አይሁዶችን እና ኢአማኒያን በሲኖዶሱ ላይ ቢጋብዙም አለመግባባት መወገዱን በማየታቸውመደነቃቸውን ገልጸው አለመግባባቶች በሲኖዶሱ ላይ የታዩት “ከስንት አንዴ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። ለእዚህ ስኬት በዋነኝነት የሚተቀሰው በሲኖዶሳዊነት ላይ የተካሄደው 16ኛው የካቶሊክ ጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጉባሄ የተጠቀሙበት ዘዴ አወንታዊ በመሆኑ የተነሳ ነበር ያሉ ሲሆን ይህም ዘዴ “በመጀመሪያ ሃሳባችሁን ግለፁ፣ ከእዚያን በኋላ ሌሎችን አዳምጡ እና በመጨረሻም በዝምታም ቢሆን በውይይት ተሳተፉ። ስለዚህም በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የውይይት ዘዴ እንዳለ አሳይተናል ይህም በዚህ ዓለም ከቤተክርስቲያን ውጭም ቢሆን ሰላማዊ ውይይቶችን የሚያመጣ እንደ ጦርነቶች እና ዓለም አቀፍ ግጭቶች ባሉ ጉዳዮች ላይ መሻሻል ለማድረግ የምያስችል ዘዴ ነው ሲሉ አክለው ገልጸዋል።

ሥነ-ምህዳራዊ ገጽታን በተመለከተ የፖላንድ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ይህ ሲኖዶሳዊ ሂደት የተለያዩ የሐይማኖት ተቋማት እምነቶችን፣ መንፈሶችን እና የባህል ልዩነቶችን በማክበር ወደ አንድነት እየገሰገሰ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

ዶ/ር ክሊፎርድ፡- ከቀጣይ እና ግልጽ የውይይት ዘይቤ ጋር

ዶ/ር ካትሪን ክሊፎርድ ካናዳዊ እና በኦታዋ በሚገኘው የቅዱስ ጳውሎስ ዩኒቨርስቲ የስልታዊ እና የታሪክ ስነ-መለኮት መምህር እና የአለም አቀፍ የካቶሊክ-ሜቶዲስት የጋራ ኮሚሽን አባል በሲኖዶሱ ውስጥ የሰሜን አሜሪካ የሲኖዶስ ሂደት ተወካይ በመሆን በመሳተፍ ላይ ናቸው። በዓለም ላይ ያሉ እያንዳንዱ ጳጳሳት ለአሁኑ ሲኖዶሳዊ ሂደት ቅድሚያ የሚሰጠው የሲኖዶሳዊ መሪ ሃሳብ እንዲወስዱት ያላቸው ፍላጎት የረዥም ጊዜ የብስለት ሂደት ውስጥ የተንፀባረቁበት እና የተመጣጠነ የብስለት ሂደት መሆኑን አጉልተው የተናገሩ ሲሆን ከክርስቲያናዊ ሕበረት አጋሮች ጋር በየጊዜው የሚደረጉ ውይይቶች ጠቃሚ እና ገንቢ እንደ ሆኑ አክለው ገልጸዋል።

በካናዳ አገር ዐውደ የቅድመ-ሲኖዶስ ጉዞን በተመለከተ፣ “በሌሎች የክርስቲያን አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች መካከል ስለ ሲኖዶሳዊ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አሠራራቸውን በተመለከተ የራሳቸውን ልምድ ባካፈሉልን መካከል ጠቃሚ ውይይት ተካሂዷል። ይህ ተቀባባይ ወይም አንዱ አንዱን የሚቀበልበት ክርስቲያናዊ ሕብረት የምንለው ጠቃሚ ምሳሌ ነው፣ አንዱ ከሌላው ጥሩ ልምድ እየተማረ፣ እያንዳንዳችን ቤተ ክርስቲያን የመታደስ እና የማደግ አስፈላጊነትን ተገንዝበን ሁላችንም በተሻለ ሁኔታ በቅዱስ ወንጌል መንገድ እንድንኖር ይረዳናል ብለዋል። በመጨረሻም ሲኖዶሳዊነት ሙሉ በሙሉ የታረቀ ቤተ ክርስቲያን ለመሆን ለምናደርገው የጋራ ጉዞ ተመራጭ ምስል ወይም ምሳሌ ሆኗል። የመላው የሰው ዘር የመዳን ምንጭ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ የምንካፈለው እምነት እኛን ከሚከፋፍሉን ጥያቄዎች እጅግ የላቀ ነው” ሲሉ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል።

ለጋዜጠኞች ጥያቄዎች የተሰጠው ምልሽ

ለጥያቄው ምላሽ፣ ዶ/ር ክሊፎርድ ምላሽ ሰጥተዋል፣ ቤተክርስቲያን እንደ እግዚአብሔር ሰዎች ስብስብ እንድትወስድ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ አስፈላጊነት አጉልተዋል። ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ስለ ቤተክርስቲያን የጋራ ግንዛቤ በነገረ መለኮት ምሁራን መካከል ጠቃሚ ውይይቶች መደረጉን ጠቁመዋል። ይህም ቤተ ክርስቲያንን እንደ ኅብረት እና የእግዚአብሔር ሰዎች ምስጢር አድርጎ ከሚመለከተው የሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ትምህርት ጋር የሚመሳሰል መሆኑ የሚታወስ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የፖዝናን ሊቀ ጳጳስ እና የፖላንድ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ስታኒስላው ጋዳሲኪ አክለውም በፖላንድ የሚገኙ የወደፊት ካህናትን በሚመለከት በዘረዐ ክህነት የሚሰጠው የሥልጠና ጊዜ ወደ ሰባት ዓመታት የተራዘመ መሆኑን የገለጹ ሲሆን የዘረዐ ክህነት የቅድመ ዝግጅት ዓመትን ጨምሮ የተለያዩ ሳይንስ ትምህርቶች በመተግበራቸው እጩ ካህናት በብቃት እንዲሰለጥኑ በማድረግ የወደፊት ካህናት ከዓለም የተነጠሉ እንዳልሆኑ እንዲሰማቸው እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠነክር ለማስቻል የሥለጠና ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆኑን ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ኮች በአዲሱ የወንጌል አገልግሎት ውስጥ የክርስቲያን ሕበረት ሚና ምን እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ ይህ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን አስረድተዋል። የፖዝናን ሊቀ ጳጳስ እና የፖላንድ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ስታኒስላው ጋዳሲኪ ይህንን ሐሳብ እርሳቸው እንደሚጋሩት ገልጸው ሐሳቡን ስያስተጋቡ ተልእኮ የሁለቱም የአይሁድ እና የቤተ ክርስቲያን ማህበረሰቦችን ሕይወት እንደያዘ ገልጿል። የዘመኑን ምልክቶች የመለየት አስፈላጊነትን በተመለከተ ሊቀ ጳጳሱ የወጣቱ ብፁዕ ካርሎ አኩቲስ ምሳሌ የቅድስና ምስክር መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ዶ/ር ክሊፎርድ በበኩሏ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችኮስ በላቲን ቋንቋ ኢቫንጄሊ ጋውዲየም (የወንጌል ደስታ) በተሰኘው ጳጳሳዊ መልእክታቸው የሚስዮናዊ ለውጥ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ሲሉ አስታውሰዋል ።

ዶ/ር ሩፊኒ በሚቀጥለው አመት ተመሳሳይ አባላት ይገኙ እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ጉባኤው ባለበት ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።

የመጨረሻው ጥያቄ ስለ መንፈሳዊ ጥሪ እጦት እና ባለትዳር የሆኑ ወንዶችን ለክህነት አገልግሎት መሾም የሚቻልበትን ሁኔታ የነካ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን  ዶ/ር ሩፊኒ ለእዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ይህ ሐሳብ እንደ ተነሳ ገልጸው ነገር ግን ከተወያዩት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ እና ዋናው እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።

 

27 October 2023, 16:45