ፈልግ

4ኛው ጠቅላላ ጉባኤ 4ኛው ጠቅላላ ጉባኤ  (Vatican Media)

ቅዱስ ሲኖዶስ፥ አንድነት በሚታይበት የኅብረት መንፈስ በተግባር ሠነድ ላይ ማሰላሰል መጀመሩ ተገለጸ

በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘው 16ኛ የሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በተግባር ሠነድ ሞዴል “B-1” ላይ ማሰላሰል መጀመሩን ከጉባኤው ሥፍራ የደረሰን መረጃ አመልክቷል። ሰኞ መስከረም 28/2016 ዓ. ም. ጠዋት የተጀመረውን አራተኛ ጠቅላላ የሲኖዶስ ጉባኤን በጸሎት ሥነ-ሥርዓት ያስጀመሩት፥ የ16ኛ ጠቅላላ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሰብሳቢ እና የአውሮፓ አገራት ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

16ኛው የጳጳሳት ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉ ባኤ “ለሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን፡ ኅብረት፣ ተሳትፎ እና ተልዕኮ” በሚል መሪ ቃል ቫቲካን ውስጥ ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ሲሆን፥ የጉባኤው ተሳታፊዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ መስከረም 28/2016 ዓ. ም. የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በማቅረብ በሲኖዶሱ የተግባር ሠነድ ሞዴል B-1 ላይ ማሰላሰል ጀምረዋል።

በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ በአንጾኪያ ማሮናዊ ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ቤቻራ ቡትሮስ ራኢ ቃለ መዕዳናቸውን ያካፈሉ ሲሆን፥ በዚህም “ሲኖዶሳዊው ጉዞ ለዓለም አቀፍ ቀውሶች ምላሽ ለመስጠት ይረዳናል” በማለት ተናግረዋል። ከመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በኋላ ለውይይት ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ የገቡት የጉባኤው ተካፋዮች ትኩረታቸውን በሲኖዶሱ የተግባር ሠነድ ላይ በማድረግ ባለፈው ሳምንት የጀመሩት የሞዴል “A” ቀጣይ በሆነ ሞዴል “B1” ላይ በኅብረት አሰላስለዋል።

ለሁሉ የሚደርስ የአንድነት ብርሃን

የ16ኛው ቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች  ሞዴል Bን ለጉባኤው ተካፋዮች ሲያስተዋውቁ ባደረጉት ንግግር፥ የመጀመሪያውን ሞዴል በማስታወስ፥ "ባለፉት ሁለት ዓመታት የእግዚአብሔር ሕዝብ ያደረገውን የኅብረት ጉዞ ልምድ በድጋሚ በመመልከት ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ሁለንተናዊ ራዕይ እንዲሆን ጥረት አድርገናል" በማለት ተናግረዋል።

በሁለተኛው ሞዴልም “የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከመስማት ከተገኙ ሦስት ጥያቄዎች መካከል በመጀመሪያው ላይ ጉባኤው እንዲያሰላስልበት መጋበዙን ገልጸዋል። የሞዴሉ ርዕሥም፥ “በጉልህ የሚታይ የኅብረት መንፈስ” የሚል መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች  ለጉባኤው ተካፋዮች ገልጸው፥ ይህን መሪ ሃሳብ መሠረት በማድረግ የጉባኤው ተካፋዮች ቅድሚያን በመስጠት የሚያሰላስሉበት አርዕስትም፥  “ከእግዚአብሔር እና ከሰው ልጆች ሁሉ ጋር የበለጠ የአንድነት መሣሪያ ምልክት መሆን የምንችለው እንዴት ነው?” የሚል መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ሆለሪች ለጉባኤው ተናግረዋል።

ሰኞ ከሰዓት በኋላ እና ማክሰኞ ጠዋት ትናንሽ ቡድኖች ውይይቶ እንደሚካሄዱ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ዣን ክሎድ ሆለሪች፥ ቀደም ሲል በተለማመዱት እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በሚደርጉት የጋራ መግባቢያ ዘዴ መሠረት መንፈስ ቅዱስን በማዳመጥ እርስ በርስ እንደሚወያዩ ገልጸው፥ በጉባኤው መካከል የሚነበቡ የቡድን ሪፖርቶች ተዘጋጅተው እና ለጉባኤው እንዲቀርቡ በሚፈለጉ ነጥቦች ላይ በማተኮር ወደ ጋራ ግንዛቤ ውስጥ በጥልቀት መግባት እንደሚጀመር አስረድተዋል።

4ኛ ጠቅላላ ጉባኤ

ከብፁዕ ካርዲናል ሆለሪች የመግቢያ ንግግር ቀጥሎ በሞዴል B-1 ላይ የቀረቡት መሪ ሃሳቦችን መሠረት በማድረግ በርካታ ባለሙያዎች ያቀረቡትን ንግግር የሲኖዶሱ አባላት አድምጠዋል። ለጉባኤው ንግግር ካደረጉት መካከል ክቡር አባ ቲሞቲ ራድክሊፍ፥ በዮሐ. 4፡7–30 ላይ የተጻፈውን በመጥቀስ፥ በውሃ ጉድጓዱ አጠገብ በነበረች ሳምራዊት ሴት ታሪክ ላይ የጉባኤው ተካፋዮች እንዲያሰላስሉበት ጋብዘዋል።

በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኝ ዱራም ዩኒቨርሲቲ የነገረ መለኮት እና የሃይማኖት ጥናት እና የካቶሊክ ማኅበራዊ አስተምህሮ እና ልምምድ ጥናቶች ማዕከል ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አና ሮውላንድስ፥ አንድነትን መሠረት ያደረገ “የበጉ የሠርግ በዓል” በሚለው ጭብጥ ላይ ሥነ-መለኮታዊ አስተንትኖን አቅርበዋል።በደቡብ ቱርክ ጥንታዊ ክልል፣ በፒሲዲያ ከተማ በሚገኝ የካቶሊክ እና የኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የጋራ ዓለም አቀፍ የሥነ-መለኮት ውይይቶች ኮሚሽን ተባባሪ ፕሬዝዳንት አቶ ኢዮብ፥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሲኖዶሳዊነት ላይ ያላትን ልምድ ለጉባኤው ተካፋዮች አካፍለዋል።

በተጨማሪም ከማሌዥያው ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የመጡት ክቡር አባ ክላሬንስ ዴቬዳሳን “ከእግዚአብሔር እና ከሰው ልጆች ሁሉ ጋር የበለጠ የአንድነት መሣሪያ ምልክት መሆን እንዴት እንችላለን?” በሚለው ርዕሥ ላይ የጉባኤው ተሳታፊዎች እንዲያሰላስሉበት ጋብዘዋል።

ቀጥሎም ከሆንግ ኮንግ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የተጋበዙት የጉባኤው ተካፋይ ወ/ሮ ሲዩ ዋይ ቫኔሳ ቼንግ ስለ “ሲኖዶሳዊነት እና ባሕል” በሚል ርዕሥ፣ በተለይም “ሲኖዶሳዊነት እና የእስያ ባሕሎች” በሚለው ርዕሥ ላይ በማሰላሰል ምስክርነታቸውን ለጉባኤው ተካፋዮች አካፍለዋል። ሰኞ መስከረም 28/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በነበራቸው ክፍለ ጊዜ የውይይት ቡድኖቹ በአዲሱ ሞዴል ለመወያየት መሰብሰባቸው ታውቋል።

10 October 2023, 17:21