ፈልግ

የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ  (Vatican Media)

አባ ዳሪዮ ቪታሊ፥ ሲኖዶሱ ለመንፈስ ቅዱስ ሥራ ቅድሚያን እንደሚሰጥ ገለጹ

የነገረ መለኮት ሊቃውንት ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ በሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘት ሠነዶችን በማንበብ እና የውሳኔ ሃሳቦችን በማብራራት ድጋፍ እንደሚሰጥ ታውቋል። ጉባኤን ከሚያጋጥሙት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ ማዳመጥ እና መግባባት የሚገኝበት መድረክ ማወቅ እንደሆነ አባ ዳሪዮ ቪታሊ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ ቅድሚያን የሚሰጠው ለመንፈስ ቅዱስ እና የእርሱን ተግባር መረዳት እንደሆነ ደጋግመው መናገራቸው ይታወሳል። ሲኖስዶን ከፓርላማ የሚለየው ነበር ቢኖር፥ ከሥራው ጎን ለጎን የሊቃውንት ቡድን ለሚሰጠው አገልግሎት ምስጋና ይግባውና፥ ሲኖዶስ በመንፈሳዊ ልኬት ላይ የተመሠረተ የቤተ ክርስቲያን ዝግጅት መሆኑ ተነግሯል።

ማዳመጥ

16ኛው የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ካለፈው ልምድ ጋር ሲነጻጸር በተለየ መልኩ ምድቡ በሁለት የተከፈለ እንደሆነ ሲታወቅ፥ በውይይት ወቅት ትናንሽ ቡድኖችን እንዲያግዝ የተጠራ የአስተባባሪዎች ቡድን እና የነገር-መለኮት ሊቃውንት ያለው እንደሆነ ታውቋል። የነገር-መለኮት ሊቃውንቱ በጉባኤው መካከል ጽሑፎችን ማንበብ፣ ማቅረብ እና ማዳመጥ እንደሆነ፣ የነገረ መልኮት ቡድን አስተባባሪ የሆኑት አባ ዳሪዮ ቪታሊ ቴሌፓቼ ለተሰኘ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የቴሌቪዥን ጣቢያ ገልፀዋል። የነገረ-መለኮት ሊቃውንትን ከሚያጋጥማቸው ተግዳሮቶች መካከል አንዱ በጉባኤው የሚቀርቡ ንግግሮችን ማዳመጥ እና ባዳበሯቸው ክህሎቶች መሠረት መግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ እውቅና መስጠት እንደሆነ አባ ዳሪዮ አስረድተዋል።

በመንፈስ ቅዱስ በመመራት መወያየት

“በመንፈስ ቅዱስ በመመራት መወያየት” የሚለው ነጥብ መሠረታዊ እንደሆነ የገለጹት አባ ዳሪዮ፥ መንፈስ ቅዱስ የሚሠራው በቃላት እና በመደማመጥ በሚፈጠር የጋራ እውነታ ውስጥ እንደሆነ ተናግረው፥ መንፈስ ቅዱስ ብርሃን በመሆን መንገድን እንደሚመራ፥ እንደሚጠቁም እና በወንድሞች እና እህቶች መካከል ሊፈጠር የሚችል አለመግባባት እንደሚቀንስ አስረድተዋል። “ሲኖዶስ ወንጌልን እንዴት መኖር እንደሚገባ ወደ መግባባት የሚደረስበት ቦታ ነው” ያሉት አባ ዳሪዮ፥ የሲኖዶሱ የተግባር ሠነድም ይህንን ዘዴ “በመንፈስ ቅዱስ የሚደረግ ውይይት” ብሎ እንደሚጠራው አስታውሰዋል።

በኅብረት መጓዝ

በሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሠነድ ውስጥ በተጨባጭ እንደተመለከተው፥ በመንፈስ ቅዱስ ውስጥ ያለው የጋራ ውይይት ከማስተዋል ጋራ በጸሎት ሊገለጽ እንደሚችል አባ ዳሪዮ ተናግረዋል። በኅብረት መጓዝ ሁሉንም የሚወክል እና የተገለሉ ድምፆችን ጭምር በማካተት ወደ ስምምነት የሚመራ ትንቢታዊ እና ገንቢ መንገድ እንደሆነ አባ ዳሪዮ ገልጸው፥ በኅብረት ለመራመድ ወደ ስምምነት ሊያደርሱ የሚችሉ ነጥቦችን በሚገባ መመልከት አለብን” በማለት የጋዜጠኞችን ሚና በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጉባኤው መካከል የሚቀርቡ ጥያቄዎችን እና በዝግ የሚካሄዱ ውይይቶችን ማሳወቅ እንደሚገባ አሳስበዋል። የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ በጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. እንደማይዘጋ ነገር ግን በጥቅምት ወር 2017 ዓ. ም. ልዩ ከአብያተ ክርስቲያናት የቀረቡት መንገዶች ለማወቅ የሚያስችል ሌላ ምዕራፍ እንደሚኖር አባ ዳሪዮ አስታውቀዋል።

ቤተ ክርስቲያን ወዴት እንደምትሄድ ጥያቄዎችን ማቅረብ

የኅብረት ጉዞው እንደሚቀጥል እና በጉባኤው ወቅት አለመግባባትን በሚያመጡ ነጥቦች ላይ ማተኮር አለማስፈለጉን ግምት ውስጥ ማስገባት ጥሩ ነው ያሉት አባ ዳሪዮ፥ ይህም የሦስተኛው ሺህ ዓመት ቤተ ክርስቲያን ቅርጾችን ለመለየት እና በተግባር ለመተርጎም ያለመ እንደሆነ ገልጸው፥ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ምርጫ ወቅት ጋዜጠኞች እንዲገኙ የማይፈቀድላቸው እና በዚያ ሁኔታ ውስጥ

ማንም ሰው የመንፈስ ቅዱስ ሥራን በመቃወም ቅሬታን እንደማያቀርብ አስረድተዋል። በሲኖዶስ ጉባኤ ውስጥ ግን የቤተ ክርስቲያን ኅብረት እንዴት እንደሚገነባ፣ የወንጌል መልዕክተኛ መሆን እና ሁሉም እንዲሳተፍ መፍቀድ” የሚሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ተገቢ እንደሆነ አባ ዳሪዮ ተናግረው፥ ጋዜጠኞች የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው፥ ጉባኤውን እንደሚያዳምጡ እና መንፈስ ቅዱስ የሚያሳያቸውን እንደሚናግሩ፥ ወይም ደግም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዳሉት፣ መንፈስ ቅዱስ ከሂደቱ አንፃር ምን እያከናወነ እንደሚገኝ እንደሚመሠክሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

03 October 2023, 17:05