ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን 

ካርዲናል ፓሮሊን፥ እስራኤል ራሷን ለመከላከል በምትወስደው እርምጃ ሲቪሎች እንዳይጎዱ አሳሰቡ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ በቅድስት አገር የሚካሄደውን ጦርነት በማስመልከት ከቫቲካን መገናኛ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ብጹዕነታቸው በዚህ ቃለ ምልልሳቸው፥ የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን በእስራኤል ላይ የፈጸመው ጥቃት ኢ-ሰብዓዊ እንደሆነ ገለጸው፥ ራስን ለመከላከል በሚወሰድ ሕጋዊ እርምጃ ሲቪሎች መጎዳት የለባቸውም በማለት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን መገናኛ ጋር ዓርብ ጥቅምት 2/2016 ዓ. ም. ባደረጉት ቃለ ምልልስ በቅድስት ሀገር በተከሰተው ጦርነት ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው ጉዳይ ታጋቾችን መፍታት እንደሆነ እና ይህን ጥረት ለማሳካት ቅድስት መንበር ለሽምግልናው ፈቃደኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

"ቅድስት መንበር እንደ ሁልጊዜው ለማንኛውም አስፈላጊ የሽምግልና ጥረት ዝግጁ ናት" ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ እስራኤል ላይ ጥቃት በተፈጸመ በስድስተኛው ቀን በሰጡት አስተያየት፥ የተፈፀመውን ጥቃት “ኢ-ሰብዓዊ ነው” ሲሉ ገልጸውታል። ብጹዕነታቸው ከቫቲካን መገናኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሃማስ ታጣቂ ቡድን የተያዙ ታጋቾች በሙሉ እንዲፈቱ ያቀረቡትን አቤቱታ በመድገም፥ የእስራኤል ራስን የመከላከል  ሕጋዊ እርምጃ ተመጣጣኝነት እንዲረው ጠይቀዋል።

በጋዛ በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት በሲቪል ዜጎች ላይ የደረሰው ጉዳት እንደሚያሳስባቸው ገልጸው፣ ምንም እንኳን የጦርነት እና የጥፋት ክስተቶች ቢታዩም እውነተኛ እና ፍትሃዊ መፍትሄ ሊገኝ የሚችለው “ሁለት መንግሥታት” የሚለው ሃሳብ ተግባራዊ ሲሆን እና ይህ የመፍትሄ ሃሳብ ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን በሰላም አብረው እንዲኖሩ ያስችላል" ብለዋል።

ጥያቄ፡ ብጹዕነትዎ ግጭቶች ሁሉ አስከፊ ናቸው፤ ነገር ግን ባለፈው ቅዳሜ የተከሰተው ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ የጭካኔ ተግባር እንደነበር ተመልክተናል። የሰው ልጅ ሕይወት በከንቱ እየጠፋ መሆኑን እናያለን። ከዚህ የከፋ እንዳይመጣ ለማድረግ ዕድሉ አሁንም አለ ብለው ያስባሉ? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፥

መልስ፥ ባለፈው ሳምንት ማጠናቀቂያ ማለትም መስከረም 26/2016 ዓ. ም. ሃይማኖታዊ በዓላቸውን ለማክበር በተሰበሰቡት በሺህዎች በሚቆጠሩ እስራኤላውያን ላይ የሃማስ ታጣቂ ቡድን እና ሌሎች ሚሊሻዎች ተባብረው የፈጸሙት የሽብር ጥቃት ኢ-ሰብአዊ መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ገልጸው፥ ጥቃቱን ቅድስት መንበር በጽኑ እንደምታወግዘው ተናግረዋል። ከዚህም በላይ በጋዛ ታግተው የሚገኙት ወንዶች፣ ሴቶች፣ ሕፃናት እና አረጋውያን ጉዳይ ያሳስበናል። በዚህ ጥቃት ለተጎዱት ቤተሰቦች አጋርነታችንን እንገልፃለን። አብዛኞቹ አይሁዳውያን እንደሆኑ እና አሁንም ድንጋጤ ውስጥ የሚገኙትን እና የቆሰሉትን በጸሎታችን እናስታውሳቸዋለን ብለዋል።

“የምክንያታዊነት ስሜትን መልሶ ማግኘት አስፈላጊ ነው፤ ጭፍን ጥላቻን በማስወገድ ሁከትን እንደ መፍትሄ መውሰድን መተው ያስፈልጋል። ጥቃት ሚደርስባቸው ሰዎች ራሳቸውን መከላከል መብታቸው ነው፤ ነገር ግን እራስን ከጥቃት መከላከል ሕጋዊ እና መብት ቢሆንም መጠንን ያከበረ መሆን አለበት” ብለዋል።በእስራኤል እና በሃማስ ታጣቂዎች መካከል ለውይይት ምን ያህል ቦታ እንዳለ የማውቀው የለም ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ለውይይት ዕድል እንዳለ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ በሁለቱ ወገኖች መካከል ሳይዘገይ ውይይት ሊካሄድ ይገባል” ብለዋል። ይህም በጋዛ እንደታየው ተጨማሪ ደም እንዳይፈስ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸው፥ የእስራኤል ጦር ጋዛ ውስጥ በፈጸመው ጥቃት የብዙ ንፁሃን ዜጎች ሕይወት መጥፋቱን አስታውሰዋል።

አንድ የእስራኤል ወታደር 270 እስራኤላውያን በሀማስ የተገደሉበትን አካባቢ ሲቃኝ
አንድ የእስራኤል ወታደር 270 እስራኤላውያን በሀማስ የተገደሉበትን አካባቢ ሲቃኝ

ጥያቄ፡ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰላም በፍትህ ላይ እንደሚገነባ ደጋግመው ተናግረዋል። ፍትሃዊ ያልሆነ ሰላም የለም። ይህ ዛሬ ለሁለቱም ወገኖች የቀረበ የፍትህ ጥሪ እንዴት ይገለጻል?” ተብለው የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ 

መልስ፥ “ሰላም ሊመሠረት የሚችለው ፍትህ ላይ ብቻ ነው። ያለ ፍትህ በሰዎች መካከል ሰላም ሊኖር አይችልም። በቅድስት ሀገር ፍትህ ሊኖር የሚችለው፥ ፍልስጤማውያን እና እስራኤላውያን የብዙሃኑን ፍላጎት በማሟላት በሰላም እና በጸጥታ አብረው ሊኖሩ የሚችሉት፥ “ሁለት አገራት” የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ ተግባራዊ ሲሆን ነው” ብለዋል። “በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተደገፈው ይህ የመፍትሄ ሃሳብ በሁለቱም ወገኖች ተግባራዊ ሊሆን የማይችል እንደሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙዎች ቢያስቡም፥ ነገር ግን ቅድስት መንበር በተቃራኒው መንገድ ድጋፏን ቀጥላለች” ብለዋል።

“አሁን ፍትሃዊ የሚሆነው፥ ከቀደሙት ግጭቶች ወዲህ በሃማስ ታጣቂዎች የተያዙት ታጋቾች በአስቸኳይ እንዲመለሱ ማድረግ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ከዚህ አንጻር በቅርብ ቀናት ውስጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡትን ልባዊ ጥሪ በድጋሚ አድሰው፥ እስራኤል እራስን ለመከላከል በምትወስደው ሕጋዊ እርምጃ ጋዛ ውስጥ የሚኖሩ የፍልስጤም ሲቪሎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቅ የለበትም” ብለዋል። እንደማንኛውም ሌሎች ግጭቶች ወቅት በተግባር የሚገለጽ የሰብዓዊነት ሕግ በዚህ ግጭት ውስጥም ሙሉ በሙሉ ሊከበር ይገባል” ብለዋል።

ፍልስጤማውያን የእስራኤልን የአየር ጥቃት ሲሸሹ
ፍልስጤማውያን የእስራኤልን የአየር ጥቃት ሲሸሹ

ጥያቄ፡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ መስከረም 30/2016 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባቀረቡት ሳምንታዊ ጠቅላላ አስተምህሮ ማጠቃለያ ላይ ታጋቾቹ እንዲፈቱ አቤቱታቸውን አቅርበው የንጹሐን ሕይወት እንዲታደግ ጠይቀዋል። ቅድስት መንበር በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ዓይነት በፍልስጤም እና በእስራኤል ጦርነት መካከልም ለማድረግ የምትችልበት ዕድል አለ ወይ? ተብለው የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥

መልስ፥ የሃማስ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ምክንያት የእስራኤል ጦር የሚሰጠው ምላሽ፣ የእስራኤል ታጋቾችን ማስለቀቅ እና በጋዛ የንጹሃን ሕይወትን ከሞት ማትረፍ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እና መላውን የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን የሚያሳስብ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል። ቅድስት መንበር እንደ ሁልጊዜው ማንኛውንም አስፈላጊ የሽምግልና ጥረቶችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገልጸው፥ እስከዚያው ድረስ ክፍት የሆኑ መንገዶችን ለመጠቀም እንደሚሞክሩ ተናግረዋል። ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አክለውም፥ “ግጭቱን ለማስቆም የሚደረግ ማንኛውም የሽምግልና ጥረት፥ ጉዳዩን ውስብስብ  የሚያደርጉ ተከታታይ ርዕሦችን ማለትም የእስራኤል የሠፈራ ዕቅዶችን፣ የጸጥታ ሁኔታ እና የኢየሩሳሌም ከተማ ጉዳይን ግምት ውስጥ ማስገባት አለበት” ብለዋል። ምንም እንኳን ችግሩ ከባድ ቢሆንም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብርታት እና ድጋፍ በፍልስጤማውያን እና በእስራኤላውያን መካከል ቀጥተኛ ውይይት በመታገዝ መፍትሄ ማግኘት እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ጥያቄ፡- የፍልስጤም ፕሬዝደንት ማህሙድ አባስ እና የእስራኤሉ ፕሬዝደንት አይዛክ ሄርዞግ በቅርቡ በተደረጉ ሁለት ቃለ ምልልሶች፥ ሁለቱም ከቅድስት ሀገር አናሳ የክርስትና እምነት ተከታዮች ሳያቋርጡ ለሚመጡት የሰላም ጥያቄዎች አድናቆታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች በግጭቱ ምክንያት መከራ ውስጥ ገብተዋል። የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት በቁጥር ዝቅተኛ የሆነው የጋዛ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ሁኔታ አሳሳቢ ነው። የቅድስት ሀገር ክርስቲያኖች አሁን በተጨባጭ ሊታገዙ የሚችሉት እንዴት ነው?” ተብለው የተጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥

መልስ፥ በመጀመሪያ ደረጃ በጸሎት፣ መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው፥ እነዚህ ቃሎችም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እና የቅድስት መንበርን የፍቅር አቀራረብ እንደገና የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተናግረው፥ “ክርስቲያኖች ኢየሱስ የተወለደበት፣ የኖረበት፣ የሞተበት እና ከሞት የተነሣበት ምድር ወሳኝ አካል ናቸው” ብለዋል።

ከጥንትም ጀምሮ ወደ ፊትም ፍልስጤምን ወይም እስራኤልን እንደ ክርስትና እምነት መገኛ ሥፍራነት የማያስብ ሰው ሊኖር አይችልም” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ጋዛ ውስጥ የሚገኙ በቁጥር ወደ 150 የሚደርሱ ካቶሊክ ምዕመናን በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ መገኘታቸው እውነት እንደሆነ ገልጸው፥ አንድ አባል ሲሰቃይባት ቤተ ክርስቲያንም እንደምትሰቃይ አስረድተው፥ ባሁኑ ወቅት የጋዛ ምዕመናን በቁምስና ውስጥ መጠለላቸውን እንደሚያውቁ ተናግረዋል። የቁምስናው መሪ ካኅን ከምዕመናን ጋር በቤተልሔም ውስጥ ምንም ዓይነት ዕርዳታን ማግኘት በማይችሉበት ሁኔታ በፍርሃት ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

“ለእስራኤላውያን፣ ለፍልስጤማውያን ለክርስቲያኖች፣ ለአይሁዶች እና ለሙስሊሞች እንጸልይ፥ ሰላም ከእናንተ ጋር ይሁን! ለኢየሩሳሌም ሰላም ይሁን፣ ለወንድሞች እና እህቶች፥ ለወዳጆቼ በሙሉ ሰላም እንዲሆን፥ እግዚአብሔርንም ለበጎነቱ እጸልያለሁ” (መዝ. 122:6-9) በማለት፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በቅድስት አገር የተነሳውን ጦርነት በማስመልከት ከቫቲካን መገናኛ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።

14 October 2023, 17:33