ፈልግ

የሲኖዶስ ጉባኤ ተሳታፊዎች በንዑስ የቡድን ውይይት ወቅት  የሲኖዶስ ጉባኤ ተሳታፊዎች በንዑስ የቡድን ውይይት ወቅት   (Vatican Media)

ብጹዕ አቡነ ሬይመንድ የሲኖዶሳዊነት ተጨባጭ ልምድን በማስመልከት አስተያየታቸውን ገለጹ

በካናዳ የቅዱስ ጄሮም ሞንት ላውሪ ሀገረ ስብከት መሪ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሬይመንድ ፖይሰን፥ የሲኖዶሳዊነትን ተጨባጭ ልምድ በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። በቫቲካን ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18/2016 ዓ. ም. ድረስ የተካሄደውን 16ኛ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤን የተካፈሉት ብጹዕ አቡነ ሬይመንድ፥ የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ ባካሄደው የመጀመሪያ ስብሰባ ወቅት የታየው መግባባት የሚያድግበትን መንገድ ማየት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በካናዳ ኪቤክ የቅዱስ ጄሮም ሞንት ላውሪ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሬይመንድ ፖይሰን፥ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “በጉባኤው ወቅት በመካከላችን የነበረው መግባባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንደሚያድግ መመልከት ያስደስታል” ሲሉ ተናግረው፥ የሲኖዶስ ጉባኤው ጳጳሳትን፣ ካኅናትን፣ ገዳማውያንን እና ገዳማውያትን፣ ወጣት እና ጎልማሳ ምዕመናንን ከዓለም ክፍል ያሰባሰበ ዓለም አቀፍ ልምድ እንደ ነበር አስታውሰዋል።

የሲኖዶስ ጉባኤው የቤተ ክርስቲያን ልምድ ነው

ከጉባኤው አስቀድሞ ከነበረው የሱባኤ ዝግጅት ጀምሮ የነበረው ልምድ ልዩ እንደ ነበር ጠቁመው፥ “የሲኖዶሱን ዓላማ ይፋ ለማድረግ መልካም እና አስፈላጊ መንገድ ነበር" በማለት ብጹዕ አቡነ ሬይመንድ ፖይሰን ተናግረዋል።

ጥልቅ አስተንትኖ እና ጸሎት የተደረገበት ሲኖዶሳዊ ጉባኤ እንደ ነበር የተናገሩት ብጹዕ አቡነ ሬይመንድ ፖይሰን፥ ቤተ ክርስቲያን  የአንድ ትልቅ ድርጅት ምክር ቤት እና የቦርድ አባላት የሚገኙባት እንዳልሆነች ወይም በዓለም ዙሪያ የተሻለ ተልዕኮን ለመፈጸም እና እራሱን ለማደራጀት በሮም ስብሰባን ያካሄደ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽን አይደችም በማለት ተናግረው፥ ነገር ግን በተቃራኒው፥ በጸሎት እና በሱባኤ አብረው የተጓዙበት ሌሎች የሚናገሩትን ለማዳመጥ ያለመ የቤተ ክርስቲያን ልምድ ነው” በማለት ገልጸውታል።

አስፈላጊው ልምድን ማግኘት ነው

ብጹዕ አቡነ ሬይመንድ ለውይይት አስፈላጊነት አጽንኦት በመስጠት፥ ዘዴው ከጠቅላላ ጉባኤው ሂደት አልፎ በሌሎች አጋጣሚዎችም ተግባራዊ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ የጉባኤው ረቂቅ ቢዘጋጅም ትልቁ እና አስፈላጊው ከዓለም ዙሪያ ከመጡት የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች ጋር በመሆን ያገኙት ልምድ እንደ ነበር ተናግረዋል።

በጉባዔው ላይ የተገኙት የካናዳ ልዑካንን ሊያጋጥማቸው የሚችል ፈተና፥ ልምዳቸውን ወደ መጡበት ቤተ ክርስቲያን ማምጣት ነው ብለዋል። ትልቁ ሥራቸው የጉባኤውን ብርሃን ከሌሎች ወንድሞች እና የአገሪቱ ጳጳሳት ጋር በመካፈል እያንዳንዱን የቤተ ክርስቲያን አባል እንዲደርስ ማድረግ፣ የጥምቀት ጸጋን የተቀበለ እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል በተልዕኮ የመሳተፍ ክብርን ጠንቅቆ እንዲያውቅ ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።

ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የመሳተፍ ተልእኮ ማደስ

ብጹዕ አቡነ ሬይመንድ ለዜና አገልግሎቱ እንዳስረዱት፥ ሲኖዶሱ ሁሉም ሰው በቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ውስጥ እንዲሳተፍ የሚያደርገውን ሃሳብ እንደሚያነቃቃ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ምንም እንኳን የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ኃላፊነት ቢኖራቸውም ሁሉም እንደየራሱ ስጦታ እና ቸርነት በቤተ ክርስቲያን ሥራ ላይ ጉልበታቸውን እውቀታቸውን እና ሃብታቸውን ማፍሰስ ይችላሉ ብለዋል።

ብጹዕ አቡነ ሬይመንድ ፓይሰን ከሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ የመጀመሪያው ዙር ያገኙትን ልምድ ሲያጠቃልሉ እንደተናገሩት፥ የጉባኤው ተሳታፊዎች ከእግዚአብሔር ሕዝብ የሚነሳውን፣ የሚያስቡትን እና ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው ያላቸውን ስሜት እንዲገልጹ የሚያስችላቸው የመጀመሪያ ረቂቅ መዘጋጀቱን ገልጸው፥ የተዘጋጀው ረቂቂ በዓለም ውስጥ ስለምትገኝ ቤተ ክርስቲያን እና ዓለምም ስለ ቤተ ክርስቲያን አወቃቀር እና ተልእኮዋ በሚገባ እንዲረዳ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚቀጥለው ዓመት ለሚካሄደው ሁለተኛ ዙር 16ኛው ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ አቡነ ሬይመንድ ፓይሰን፥ በመጀመሪያው ዙር የኖሩትን ልምድ ለሌሎች መመስከር ሥራቸው እንደሚሆን ተናግረው፥ በጊዜ ሂደት በሀገረ ስብከቶች እና በቁምስናዎች ውስጥ ተመሳሳይ መነሳሳት እንደሚኖር ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ወደፊት ስለ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር የበለጠ ሲወያዩ አንዳንድ አዳዲስ ሃሳቦች እንደሚመነጩ ተናግረዋል።

31 October 2023, 16:39