ፈልግ

የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሲሰጡ  

ቅዱስ ሲኖዶስ ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ አስታወቀ

በቫቲካን እየተካሄደ ያለው 16ኛ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 12/2016 ዓ. ም. በሰጠው ማብራሪያ፥ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥቅምት 14/2016 ዓ. ም. ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ መልዕክት እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል። ሲኖዶሱ በተጨማሪም የጉባኤውን ጠቅላላ ሠነድ ጥንቅርንም ቅዳሜ ጥቅምት 17/2016 ዓ. ም. ማታ ይፋ እንደሚያደርግ የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል። በሥነ-ሥርዓት ላይ የቪየና ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ፣ የሜክሲኮ ሲቲ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ካርሎስ አጊየር፣ የማርሴይ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ማርክ አቬሊን እና በሮም የጎርጎሮሳዊያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እህት ሳሙኤላ ሪጎን የቀረቡ ማብራሪያዎችን ጋዘጤኞች አድምጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለመላው ምዕመናን ይፋ የሚሆነው መልዕክት ረቂቅ ለጉባኤው ተሳታፊዎች በተነበበ ጊዜ አባላቱ ደስታቸውን በጭብጨባ ገልጸዋል። በዚህ ወቅት የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች ለጉባኤው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ “በረቂቅ ጽሑፉ ላይ ማስተካከያዎች እና ጥቂት ተጨማሪ ሃሳቦች ታክሎበት ተቀባይነት ያገኘ መሆኑን፥ በተለይም ወደ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሲተረጎም ግልጽነት እንዲኖረው ጥንቃቄ መደረጉን ገልጸዋል። ሰኞ ጥቅምት 12/2016 ዓ. ም. ማምሻውን ተጨማሪ የማሻሻያ ሃሳቦች ለሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የቀረበ ሲሆን፥ ይህም ታክሎበት ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ ረቡዕ ጥቅምት 14/2016 ዓ. ም. ጸድቆ እንደሚታተም፥ በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ገልጸዋል።

የሰኞ ጠዋት መስዋዕተ ቅዳሴ እና የሥራ ሂደት

የጉባኤው ተሳትያፊዎች የዕለቱን ተግባር ከመጀመራቸው አስቀድሞ ሰኞ ጥቅምት 12/2016 ዓ. ም. ጠዋት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በምያንማር የያንጎን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ቻርለስ ማውንግ ቦ መርተዋል። ቀጥሎም አሥራ ስድስተኛው ጠቅላላ ጉባኤ - በአባ ጁሴፔ ቦንፍራቴ አስተባባሪነት የተካሄደ ሲሆን በጉባኤው ላይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ጋር 350 አባላት ተሳታፊ ሆነዋል። በዕለቱ ከማር. 4:26-34 ተወስዶ በተነበበው ምንባብ ላይ በማስተንተን ለጉባኤ ተሳታፊዎች መንፈሳዊ ድጋፍ የሰጡት፥ የቅዱስ ዶሜኒክ ማኅበር አባል አባ ቲሞቲ ራድክሊፍ ፣ የቅዱስ ቤኔዲክቶስ ደናግል ማኅበር አባል እህት ማርያ ኢግናሲያ አንጄሊኒ እና ከአውስትራሊያ የመጡት የነገረ መለኮት ምሁር አባ ኦርሞንድ ራሽ እንደነበሩ ታውቋል። ቀጥሎም ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ የተጻፈው መልዕክት ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት መደረጉን ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ለጋዜጠኞች አስታውቀዋል።

በኅብረት ውስጥ የሚገኝ እምነት፣ ተስፋ እና በጎ አድራጎት

የቅዱስ ዶሜኒክ ማኅበር አባል፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አባል እና በአውስትሪያ የቪየና ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ ሾንቦርን፥ ከዚህ በፊት የተካሄዱ ጉባኤዎች ልምdocን በጥልቀት በመመርመር እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1965 ዓ. ም ተካሂዶ የነበረውን ሁለተኛውን የቫቲካን ጉባኤ አስታውሰዋል። በወቅቱ ካርል ራህነር የተባሉ ምሑር ለጉባኤው ባደረጉት የመጨረሻ ንግግራቸው፥ “ጉባኤው የእምነት፣ የተስፋ እና የበጎ አድራጎት ዕድገት ካላመጣ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው” ማለታቸውን ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ ሾንቦርን አስታውሰዋል። ተመሳሳይ መልዕክት አሁኑ እየተካሄደ ላለው የሲኖዶስ ጉባኤ እንደሚያስተላልፉ ካርዲናሉ ተናግረዋል።

የነገረ መለኮት ምሁር እንደመሆናቸው መጠን፥ ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ከተካሄደ ከሃያ ዓመታት በኋላ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1985 ዓ. ም. በቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ የተጠራውን ልዩ የሲኖዶስ ጉባኤ መካፈላችውንም ገልጸዋል። የኅብረት መሠረታዊ ፅንሰ ሐሳብን በተመለከተ፣ ከ50 ዓመታት በኋላ ዛሬ በማክበር ላይ የምንገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምሥረታ በዓል፥ “ከቅድስት ሥላሴ ጋር አንድነት ያለውን የእምነት ኅብረት፥ በምዕመናን መካከል ያለውን ኅብረት እና ለሁሉም ሰዎች ክፍት የሆነን ኅብረት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዴት መኖር ይቻላል?” የሚል አመለካከት ያለው እንደሆነ ተናግረዋል። “ሲኖዶሳዊነት ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ምስጢር የሚናገረውን “የሕዝቦች ብርሃን” የሚለውን ሐዋርያዊ ሠነድ ራዕይ እንደገና ማጤን ነው ብለው፥ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢርነት፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆኗን እና ስለ አባሎቿ ተዋረዳዊ ሕጎችን የያዘ ቃለ ምዕዳን እንደሆነ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ ቀጥለውም፥ “ከእንግዲህ ወዲህ አውሮፓ የቤተ ክርስቲያን ዋና ማዕከል አይደለችም” በማለት ተችተዋል። “በቅዱስ ሲኖዶሱ መካከል ዕለት ዕለት እንደሚታየው፥ ላቲን አሜሪካ፣ እስያ፣ አፍሪካ እና አህጉራዊ ጉባኤዎቻቸው ዋና ተዋናዮች ሲሆኑ የአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤ ግን የዳበረ አቅም ሊኖረው አልቻለም” ብለዋል። “አሮጌው የአውሮፓ አህጉር በተግባር ከሚገጽ ሲኖዶሳዊነት ወደ ኋላ የቀረ በመሆኑ ማነቃቂያ ያስፈልገዋል” ብለዋል። የአውሮጳ ጳጳሳት ጉባኤዎች በስደተኞች ጉዳይ ላይ አንድም ጊዜ ቃል አለማሰማቱን ለአብነት አቅርበዋል። ብጹዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ በመጨረሻም ሲኖዶሳዊነት ያለ ሥርዓተ አምልኮ እንደማይኖር ዘወትር የሚያውቁትን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናትን ዋቢ አድርገው፥ በኅብረት የሚከበረውን የጋራ እምነት መንከባከብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሲኖዶሳዊ ቀጣይነት

ከጉባኤው ሊቃነ መናብርት መካከል አንዱ እና የሜክሲኮ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ካርሎስ አጉያር ሬቴስ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2012 ዓ. ም. በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ አዲሱን የስብከተ ወንጌል ሥራ ለማስጀመር የተቋቋመውን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታውሰው፥ "ቤተሰቦች አዲሱን ትውልድ በቅዱስ ቃሉ ማነጽ ባለመቻላቸው እምነትን ወደ ሌሎች ዘንድ ማሠራጨቱ ተደናቅፏል” በማለት ንግግራቸውን ደምድመዋል።

በዚህም ምክንያት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጀመሪያው ሲኖዶስ ትኩረታቸውን ለቤተሰብ መስጠታቸው መሠረታዊ ነው” ብለው፥ ቀጥሎም እንደ ጎርጎሮሳውያን በ 2018 ዓ. ም. የተካሄደው የሲኖዶስ ጉባኤ ወደ ወጣቶች በመድረስ፣ ከእነርሱ ጋርም አብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ መወሰኑን አስረድተዋል። የሜክሲኮ ዋና ከተማ ሊቀ ጳጳሳ ከመሆናቸው ቀደም ብለው፥ በትላልኔፓንትላ ሀገረ ስብከት ከአዲሱ ትውልድ ጋር የነበራቸውን ልምድ ሲናገሩ፣ ጓደኝነታቸውን ለማጎልበት በማሰብ ከተለያዩ የማኅበሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ ወጣቶች ጋር መሰብሰባቸውን ገልጸው፥ የእምነት ጥማት በእምነት ውስጥ በሚኖሩ ወጣቶች አማካይነት ወደ ሌሎች ዘንድ መተላለፍ አለበት ብለዋል።

በአማዞን አካባቢ አገራት መካከል የተካሄደውን የሲኖዶስ ጉባኤን እንዲካፈሉ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጋበዛቸውን የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ካርሎስ አጉያር፣ በዚህ የሲኖዶስ ጉባኤ ላይ የአየር ንብረት ለውጥን እና የፍጥረት ጥበቃ አስፈላጊነትን በማጤን ሕጻናትን እና ወጣቶችን በሥነ-ምህዳር ላይ ማካተት መቻል አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘባቸውን ተናግረው፥ በዚህም ሕጻናት እና ወጣቶች የእግዚአብሔርን ቃል እንዲረዱ መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ብፁዕ ካርዲናል ካርሎስ አጉያር በመጨረሻም፥ በሜክሲኮ ሲቲ የነበረውን የሲኖዶሳዊነት ሂደት በማስታወስ፥ በወረርሽኙ ምክንያት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 2021 እንዲጀምር መራዘሙን ገልጸው፥ ሂደቱ  የልዩ ልዩ አካባቢዎች እውነታዎችን በቅርብ የተመለከቱበት፣ የኅብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት በጋራ ውይይት ወደ መግባባት የደረሱበት እና በመደማመጥ ላይ የተመሠረተ ዘዴ በመሆኑ “የቤተ ክርስቲያን መንገድ ሲኖዶሳዊ ነው” በማለት ደምድመዋል።

ማዳመጥ፣ ዝምታ፣ ጸሎት እና ነፃነት

በፈረንሳይ የማርሴይ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ማርክ አቬሊን፥ በቅዱስ ሲኖዶስ አባልነት  የጉባኤውን ጠቅላላ ሠነድ ጥንቅርን እንዲያቀርብ የተሰየመ ምክር ቤት አባል ሲሆኑ፥ በሲኖዶስ የመጀመሪያ ልምዳቸው የተሰማቸውን ስሜት ሲገልጹ፥ አዲስ ልምድ ለማግኘት ዕድል ያገኙበት፣ ከመላው ዓለም ከመጡ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ የጓጉበት፥ የልምድ ልውውጥ የተደረገበት በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸው፥ ጉባኤው ከተጀመረ ከቀናት በኋላ የተሰማው የጦርነት ዜና አሳሳቢነትን ተናግረዋል።

“እንደዚህ ዓይነት አስደንጋጭ ክስተቶች በሚከሰቱበት ወቅት ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔርን የፍቅር መልዕክት በዓለም ላይ በብርቱ የማሰራጨት ሃላፊነት መውሰድ አለባት” በማለት ብፁዕ ካርዲናል አቬሊን አጽንኦት ሰጥተዋል። በአገራቸው ውስጥ በጋራ የሲኖዶሱ ጉዞ ላይ ያልተሳተፉ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ማርክ አቬሊን፥ በሲኖዶሳዊነት ጉዞ ላይ የመሳተፍ ዕድል አሁንም መኖሩን ገልጸዋል። “የጋራ ኃላፊነታችንን በሚያንፀባርቁ የመጨረሻ ውሳኔዎቻችን በኩል ብዙ ተስፋዎችን እያሳደግን እንገኛለን” ብለው፥ የመጨረሻው ሳምንት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለመስማማት የሚሞክሩበት እና ልዩነቶችን የሚፈቱበት ወሳኝ ጊዜ እንደሆነ ገልጸው፥ የሚቀጥሉት ወራት የዘራነውን ፍሬ የምናጭድበት ወራት ይሆናል” ሲል ገልጸዋል።

ዓለምን ለሰው ልጅ በሙሉ የተሻለች ቦታ ለማድረግ ምን ማድረግ እችላለሁ?

በሮም የጎርጎሮሳዊያን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር እና የሐዘንተኛይቱ ማርያም የደናግል ማኅበር የበላይ አለቃ የሆኑት እህት ሳሙኤላ ሪጎን በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ፥ “በሲኖዶሱ ጉባኤ ላይ እንድገኝ ከእግዚአብሔር የመጣልኝን ጥሪ፣ ጥምቀትን እንደተቀበለ ክርስቲያን እና እንደ ገዳማዊት በጸሎት ተቀብያለሁ” ብለው፥ “ሲኖዶሱ እጅግ በሚያበለጽግ ልምድ እና በቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊነት የተነካሁ መሆኔን እያሳየ ነው” በማለት፣ የሲኖዶሱ ተሞክሮ ለትህትና የሚጋብዝ እና ዕይታውም ብዙ የሚያምሩ አገልግሎቶችን ለመጀመር የሚረዳ ኃይል ነው” በማለት ተናግረዋል።

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በእምነት ስለ መትጋት፣ በትጋት ስለ መሥራት እና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለውን የተስፋ ጽኑነት፥ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ ከተነበበው ቅዱስ ቃል የያዟቸው ሦስት ሃሳቦች እንደሆኑ የተናግሩት እህት ሳሙኤላ ሪጎን፥ “እነዚህ ሃሳቦች ከሲኖዶሱ የሚወጡ ሃሳቦች ከሆኑ በአዎንታዊ መልኩ እውነተኛ ለውጥ እናደርጋለን” ብለዋል። ይህ የሆነበት ምክንያት "እኛ ወይም ከእኛ ጋር ሆነው እግዚአብሔር የሚያሳድገውን ጠቃሚ ዘር ተቀብለናል" በማለት አክለዋል። በዚህ መርህ ላይ እህት ሳሙኤላ ሪጎን፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ፥ “ዛሬ እንደገና የተለየ ክርስቲያን መሆን ጀምሬአለሁ” ያለውን በመጥቀስ፥ “ሁሉም ሰው ይህን ቢያደርግ እውነተኛ ለውጥ እናመጣለን ነበር” በማለት አስረድተዋል።

ቅዳሜ ማታ ይፋ የሚደረገው የጉባኤው ጠቅላላ ሠነድ ጥንቅር

ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ምላሽ ሲሰጡ፥ ውጤቱ እስካሁን ሊገለጽ ባለመቻሉ የሠነዱ ጥንቅር ቅዳሜ ምሽት ይፋ ሊሆን ቀጠሮ መያዙን ገልጸዋል። ሁለተኛውን ጥያቄ በተመለከተ፥ ወደፊት በሚደረገው የሲኖዶስ ጉባኤ አሁን ያለው ሲኖዶስ በይዘትም ሆነ በቅርጽ ግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ብፁዕ ካርዲናል አጊላር ሬተስ ተናግረው፥ እስካሁን ውይይት የተደረገበት እና ልምድ የተወሰደበት ርዕሥ ወደ ተግባር ከገባ ወደፊት ለመጓዝ መንገዱ ክፍት እንደሚሆን አስረድተዋል። ሁሉም ነገር የሚወሰነው ሰዎች ወደ ሀገረ ስብከታቸው ሲመለሱ በሚደረገው ጥረት ላይ እንደሆነም አክለዋል።

ለጉባዔው የተመረጠውን ዘዴና በቤተ ክርስቲያን በየደረጃው ተግባራዊ ማድረግ የሚቻልበትን ሁኔታ በመጥቀስ የምእመናን እና የሴቶችን ተሳትፎ እንደሚያሰፋ ተገልጿል። የቪየና ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2015 ዓ. ም. በሲኖዶሳዊ ርዕሠ ጉዳይ ላይ ያደረጉትን ንግግር በማስታወስ ሲናገሩ፥ የኢየሩሳሌም ጉባኤ መሠረታዊ ውሳኔዎችን ማድረጉን እና በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ እንደምናነበው ወደ ውሳኔ ለመድረስ ያገዛቸው ዋናው ዘዴ ማዳመጥ እንደሆነ አስታውሰዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ ተመሳሳይ ዘዴን ሲለማመዱ እንደቆዩ ተናግረው፥ በዚህ ረገድም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2015 ዓ. ም. ጀምሮ እስከ ዛሬ 1400 የሚደርሱ አባላት የተሳተፉባቸውን አምስት የሀገረ ስብከት ጉባኤዎች ማካሄዳቸውን በማስታወስ ይህም የመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ መግለጫ እንደሆነ አስረድተዋል። ድምጽ ባይሰጥበም የመደማመጥ እና የመግባባት ልምድ እንደነበረው ተናግረው፥ ዋናው ነገር በመጨረሻ ውሳኔዎች ላይ መድረስ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። የኢየሩሳሌም ጉባኤ ለቤተ ክርስቲያን ታሪክ መሠረታዊ ውሳኔ እንዳደረገ እና በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደተገለጸው ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ የሚያግዙ ሦስት ዜዴዎች እንዳሉ እነርሱም፥ ማዳመጥ፣ ጸጥታ እና ውይይት መሆናቸውን ገልጸዋል።

የእህት ሪጎን  ንግግር በመድገም፥ በሲኖዶሱ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውለው ዘዴ ቢሆንም ዋናው ነገር መደማመጥ መሆኑን ካርዲናል ክሪስቶፍ ተናግረዋል። ሁሉም ሰው፣ በሥራ ቦታ፣ በቤተሰብ ውስጥ፣ በሃይማኖታዊ ማኅበረሰቦች ውስጥ ይህንን ልኬት እንደገና ማግኘት እንዳለበት እህት ሪጎን ተናግረው፥ ሁሉም ሰው ሃሳብን የማካፈል እና የመደመጥ ዕድል ሊኖረው ይገባል ብለዋል። ሲኖዶስ ምዕመናንን በልዑካንነት ማካተቱን በተመለከተ ለቀረበው ትችት ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ አስተያየታቸውን ሲገልጹ፥ ይህ ችግር እንዳልሆነ ጠቁመው የብጹዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ እውነተኛ ተሳትፎ ቢኖርም ሲኖዶስ ሆኖ መቀጠሉን አስረድተዋል። በሌላ በኩል ብፁዕ ካርዲናል ክሪስቶፍ በጉባኤው መካከል ዘወትር ምእመናን እንደ ነበሩ እና አንዳንድ ጠቃሚ ሃሳቦችን ሲያካፍሉ እንደነበር አስረድተዋል።

ሲኖዶሳዊነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ልዩነት እንዳስከተለ እና ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ምን ያህል ወደ አንድነት ጎዳና ሊጋበዙ እንደሚችሉ ያለውን ጥርጣሬን በተመለከተ ካርዲናሉ ሲያስረዱ፥ የክርስቲያኖችን ልዩነት መመሥከር አስቸጋሪ መሆኑን ጠቁመው፥ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መነኩሴ የተናገሩትን በመጥቀስ፥ ምናልባት እግዚአብሔር ይህ ውርደት እንዲደር የሚፈቅደው፥ አንድ ሰው አንድነት ለሰው ልጅ መልካም መሆኑን ገና መገንዘብ ስላልቻለ ነው ብለዋል።

ብፁዕ ካርዲናል አጉያር ሬቴስ ቀጥለው፥ 180 ሚሊዮን ነዋሪዎች ባሉባት ሜክሲኮ 80% የካቶሊክ እምነት ተከታይ እንደሆነ በመግለጽ፥ የጓዳሉፔ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን መሠረት ያደረገ ሃይማኖታዊ ሥርዓት መሠረት ያደረገ የሜክሲኮ ጳጳሳት ጉባኤን ልምድ ጠቅሰዋል። በሰሜን፣ በደቡብ እና በመካከለኛው ግዛቶች የተለያዩ ሁኔታዎች እንዳሉ፥  ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 ዓ. ም. በሜክሲኮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ለማኅበራዊ እና ባሕላዊ ፍላጎቶች ምላሽ ለመስጠት ደህንነቱ የተጠበቀ ሂደት እንዲኖር በማለት መጠየቃቸውን አስታውሰዋል።

በፈረንሳይ የማርሴይ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ማርክ አቬሊን በበኩላቸው፥ ሲኖዶሱ ታላቅ የአንድነት መንፈስ የታየበት፥ በአንድነት የተካሄደ እና የክርስቲያኖች አንደነት የጸሎት ምሥክርነት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ሁሉም ሰው ከልብ በተሰቀለው በኢየሱስ ክርስቶስ ዙሪያ ከልብ በመገኘቱ ሲኖዶሳዊነት ብቸኛው እና አስተማማኝ የአንድነት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።

የተመሳሳይ ጾታ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች፥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ የሞራል 'ሥርዓትን' በመጥቀስ በተናገሩት ቃላት ሊጎዱ እንደሚችሉ ብፁዕ ካርዲናል ክርስቶፍ ተናግረው፥ የረቂቁ ጸሐፊ እንደነበሩም አስታውሰዋል። መጽሐፉ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የታወጀ የቤተ ክርስቲያን ተግባር እንደሆነ ተናግረው፥ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሞት ቅጣት ላይ ጣልቃ በመግባት አንድ ለውጥ ብቻ ማድረጋቸውን እና ሌሎች ለውጦች ካሉ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ውሳኔ ላይ ብቻ የሚመኩ መሆናቸውን ተናግረዋል። ካርዲናሉ የትምህርተ ክርስቶስ መጽሐፍን የሚያነቡት ሰዎች ጠቅላላ ይዘቱን እንዲያነቡ አሳስበው፥ እነዚህ ጉዳዮች የሞራል ሥነ-መለኮትን የሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች መሆናቸውን አስረድተው፥ “ሰዎች ኃጢአተኞች ቢሆኑም ዘወትር የመከበር እና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት መብት አላቸው” በማለት ተናግረዋል።

በመጨረሻም በቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አስተምህሮ፣ በነገረ መለኮት ሊቃውንት አስተዋጽዖ እና በምዕመናን ስሜት መካከል ስላለው ግንኙነት፣ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ መግቢያ ላይ የተናገሩትን መልዕክት እንደገና መመልከት እንደሚገባ ብፁዕ ካርዲናል ክርስቶፍ አስረድተዋል። እንደ እምነት ሁሉ ሐዋርያዊ አስተምህሮንም መለወጥ እንደማይቻል፥  አንድ ሰው ስለ ሥላሴ፣ ስለ ምስጢረ ሥጋዌ ወይም ስለ ቅዱስ ቁርባን የሚሰጠውን ትምህርት መለወጥ እንደማይችል አስረድተዋል። በዓለም ላይ በሁሉም ቦታ ተቀባይነት ያለው የሃይማኖት መግለጫ ባህሎች ቢለያዩም የእምነቱ ይዘት ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ብዙ የዳበረ ቢሆንም መለወጥ እንደማይቻል በፈረንሳይ የማርሴይ ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ዣን ማርክ አቬሊን ጠቁመዋል።

 

24 October 2023, 17:20