ፈልግ

ዓርብ ጥቅምት 9/2016 ዓ. ም. የቀረበ የጠቅላላ ሲኖዶስ ጉባኤ ማብራሪያ ዓርብ ጥቅምት 9/2016 ዓ. ም. የቀረበ የጠቅላላ ሲኖዶስ ጉባኤ ማብራሪያ  

ቅዱስ ሲኖዶስ፥ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪዎች የሰው ልጅ ክብር እንደገና እንዲገነዘቡት ተማጸነ

በቫቲካን በመካሄድ ላይ የሚገኘው 16ኛ የሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ፥ ውይይት የተካሄደባቸውን ርዕሠ ጉዳዮችን በመጥቀስ ማብራሪያ ሰጥቷል። ዓርብ ጥቅምት 9/2016 ዓ. ም. በቀረበው የሲኖዶሱ ዕለታዊ መግለጫ ላይ የብጹዓን ጳጳሳት ሥልጣንን ጨምሮ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያላቸውን የጋራ ሃላፊነትን በማካተት ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ሎዘርቫቶረ ሮማኖ” የተሰኘ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ በእትሙ እንዳስነበበው፥ በሂደት ላይ የሚገኘው 16ኛው የሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቅምት 8 እና 9/2016 ዓ. ም. ውይይት ባካሄደቸው አሥራ ሦስተኛ እና አሥራ አራተኛ ጠቅላላ ጉባኤዎች ላይ ማብራሪያዎችን ሰጥቶባቸዋል። በጠቅላላ ጉባኤዎች ላይ የቀረቡት ሁለት ርዕሠ ጉዳዮችም፥ ወሲባዊ ጥቃት እና ስልጣን የሚሉ እንደነበር ታውቋል። ሁለቱን ጉባኤዎች 341 እና 343 ዓባላት የተሳተፉት ሲሆን፣ አባላቱ ለንዑሥ ቡድኖች በተዘጋጀው ነጻ የውይይት መድረክም ተገኝተው ሃሳባቸውን እና አስተያየታቸውን ማካፈላቸውን፥በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ለጋዘጤኞች በሰጡት ማብራሪያ አስረድተዋል።

ዓርብ ጥቅምት 9/2016 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በተግባር ሠነዱ ምዕራፍ “B ቁ. 3” ላይ የተገለጹትን፥ ተሳትፎ፣ ሃላፊነት እና ሥልጣን በሚሉት ላይ ውይይቶች መካሄዳቸውን የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በመግለጽ ማብራሪያን ሰጥተዋል። ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በማብራሪያቸው፥ አንዳንድ ጊዜ በቤተ ክርሲቲያን ውስጥ የሚንጸባረቅ የሥልጣን አምባ ገነንነትን በማስታወስ፥ ቤተ ክርስቲያን አምባገነንነትን ለማስወገድ ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ በማረጋግጥ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥልጣን የበላይነትን የሚያንጸባርቁበት ሳይሆን አገልግሎት መሆኑን አስረድተዋል። ሥልጣንን በተመለከተ የጉባኤው ተካፋዮች ሰፋ ያለ ውይይት ማካሄዳቸውን የገለጹት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ የቤተ ክርስቲያን ስልጣን ሁሉን የመወሰን እና የመቆጣጠር አደራ ሳይሆን ነገር ግን ውክልና እንደሆነ ገልጸው፥ ጳጳስ የውሳኔ ቃል ያለው ቢሆንም ነገር ግን የግሉ ብቻ መሆን የለበትም በማለት አስረድተዋል።

ለውይይት ከቀረቡት ርዕሦች መካከል አንዱ፥ “ለድሆች በሚሰጥ አገልግሎት ውስጥ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ያላቸው ሚና” የሚል እንደነበር  ያስታወሱት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ለድሆች እና ችግር ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች የሚሰጥ አገልግሎት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐሙስ ጥቅምት 8/2016 ዓ. ም.  ምሽት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ያቀረቡትን የጸሎት ስልት የተከተለ ሊሆን እንደሚገባ የተናገሩ ሲሆን፥ የጉባኤው ተካፋዮችም በበኩላቸው በየጎዳናው ላይ በስቃይ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ጩኸት ሊደመጥ እንደሚገባ አሳስበዋል። ሰብዓዊነት በተለይም ለሦስተኛው የዓለም ጦርነት የበኩሉን እገዛን በማድረግ ላይ የሚገኘው እና በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች የስቃይ ምክንያት የሆነው የጦር መሣሪያ ዝውውር ቆሞ  የሰብዓዊነት ስሜት እንዲያንሰራራ ጳጳሳት ልብን የሚለወጥ መልዕክት ማሰማት እንዳለባቸው የጉባኤው ተሳታፊዎቹ አክለው ተናግረዋል።

ጉባኤው ላይ በቀረቡት ንግግሮች መካከል የጋራ ሃላፊነት የሚለው ሃሳብ በተደጋጋሚ ይሰማ እንደነበር የተናገሩት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ የጋራ ሃላፊነት እንደ ተሳትፎ እና እንደ ውስጣዊ ተነሳሽነት ቅንጅት መታየቱን ገልጸዋል። በዚህም መሠረት ሃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች ብዛት፣ ብቃት እና በተለይም ለምእመናን ቁርጠኝነት አስፈላጊነት አጽንኦት ተሰጥቷል። የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት የሆኑት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ሐሙስ እና ዓርብ የተካሄዱ ሁለት ጉባኤዎችን የተሳታፉ አባላት ቁጥር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስን ጨምሮ 365 እንደነበሩ ገልጸው፥ በሌሎች የተለያዩ መንገዶች ጉባኤውን ከተሳተፉት ሌሎች መቶ አባላት ጋር ጠቅላላ ድምሩ 464 እንደ ነበር፥ በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽ/ቤት ሃላፊ እና የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ለጋዘጤኞች በሰጡት ማብራሪያ አስታውሰዋል።

የሲኖዶሱ የመረጃ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ወ/ሮ ፒሬስ ርፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፥ በሕዝቡ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ደንቦችን ለመዘርጋት ለሞከሩት ምዕመናን ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው እና በዚህ ተግባራቸው ሥልጣን ያለአግባብ በመጠቅም የሕሊና ወቀሳን፣ ኤኮኖሚያዊ እና ጾታዊ በደሎች መፈጸማቸውን ገልጸው፥ ይህም ቤተ ክርስቲያን ተአማኒነቷን እንድታጣ ማድረጉን ወይዘሮ ፒሬስ አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት ጥብቅ የቁጥጥር ዘዴ መኖሩ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ “ይህም ከመደማመጥ እና ከውይይት ጋር የተያያዘ ሂደት በመሆኑ በደልን ለመከላከል ያግዛል” ብለዋል። ተግባራዊ ሊሆኑ የሚገቡ ለውጦች መኖራቸውን የገለጹት ወይዘሮ ፒሬስ፥ በፋይናንስ እና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሮች ላይ የበለጠ ግልጽነት ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል። አንዳንድ የቀኖና ሕጎች እና ማዕረጎች የጥንት በመሆናቸው ከጊዜው ጋር ስለሚጋጩ ክለሳ ሊደረግባቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

ወደ ሲኖዶሳዊነት ስንመለስ፥ ቀደም ሲል የነበሩ እንደ ሐዋርያዊ ምክር ቤቶች እና ሌሎች የቤተ ክርስቲያን መዋቅሮችን የማጠናከር አስፈላጊነት መኖሩን ተናግረዋል። ወይዘሮ ፒሬስ በመጨረሻም፥ ወጣቶችን አስመልክቶ በቀረበው ሃሳብ ላይ፥ ዲጂታሉ ዓለም ከቤተ ክርስቲያን የራቁትን በወንጌል አገልግሎት ለመቅረብ እውነተኛ መንገድ እንደሆነ በማስገንዘብ፥ እና ይህም ወጣቶችን በሚገኙበት የተለያዩ ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የማግኘት ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

ሊቀ ጳጳስ ግሩሻስ ስልጠና እና ተሃድሶ አስመልክተው ተናግረዋል

የአውሮፓ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት እና የሊጧኒያ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጊንታራስ ግሩሻስ፣ ባለፈው የካቲት ወር በቼክ ሪፓብሊክ መዲና ፕራግ ላይ የተካሄደውን አህጉራዊ የሲኖዶሳዊነት ስብሰባ አስታውሰዋል። ሊቀ ጳጳሱ ስብሰባው ለጋራ ውይይት እና ለመንፈሳዊ መጋራት እጅግ መልካም አጋጣሚ እንደ ነበር፥ ስብሰባው ላይም ከ45 አገራት የተወጣጡ ተወካዮች ሃሳባቸውን በተለያዩ አቅጣጫዎች ማቅረብ መቻላቸውን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጊንታራስ በመቀጠልም፥ የሲኖዶሱን ሥራ በመጥቀስ የስልጠናን ማዕከላዊነት አስመልክተው በሰጡት ሃሳብ፥ ሲኖዶሳዊነት ማለት ቤተ ክርስቲያን መሆን፣ አብሮ መኖር፣ በኅብረት የሚለማመዱት መንገድ ማለት እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተው፥ የሲኖዶሱ ልምድ ራሱ ይህንን ሁሉ በተጨባጭ ይገነዘባል ሲሉም ጠቁመዋል። "በእነዚህ ቀናት ውስጥ ድካም ቢኖርብንም፥ አሁንም ከፍተኛ ጉልበት አለን” ብለው፥ የሲኖዶሱ ተካፋዮች ከተለያዩ አገራት የመጡ ቢሆንም በመካከላቸው ብዙ የሚያመሳስላቸው ነገሮች እንዳሉ፥ ከሁሉ አስቀድሞ የጋራ እምነት፥ ሌላው አስፈላጊ ገጽታ የልብ መለወጥ፣ አስተሳሰብን ለመለወጥ ካለው ፍላጎት ጀምሮ እንደ ቤተ ክርስቲያን ለማደግ ፍላጎት መኖሩን እንገነዘባለን ብለዋል።

እህት ፋዱል፥ “በመከራ እና በተስፋ መካከል መገኘት”

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1993 በአባ ፓውሎ ዳሎሊዮ የተመሠረተ እና በሶርያ ካቶሊካዊ ሥርዓት ዲር ማር ሙሳ ገዳም የመጡት ሶርያዊት መነኩሴ እህት ሁዳ ፋዶል ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት እና ለመካከለኛው ምሥራቅ ሲኖዶስ ሂደት ምስክር በመሆን ባሰሙት ንግግር፥ አካባቢው እንደ ጦርነት፣ ወረርሽኝ እና የመሬት መንቀጥቀጥ በመሳሰሉ አደጋዎች መጎዳቱን ገልጸው፥ ሀገረ ስብከታቸው ላለፉት ሦስት ዓመታት ያለ ጳጳስ መቆየቱን ተናግረዋል። በቅርብ ከሊባኖስ የመጡት ጳጳስ በተለይ ወጣቶችን በማሳተፍ ከልዩ ልዩ የምዕመናን ማኅበረሰብ ጋር ለመገናኘት ጥረት ማድረጋቸውን አስረድተዋል። በሂደት ላይ የሚገኘውን ሲኖዶስ በማስመልከት በሰጡት አስተያየትም፥ በአንድነት እና በጸሎት የሚደረግ የሃሳብ ልውውጥ ያለበት በመሆኑ እጅግ ጠቃሚ ወቅት እንደሆነ ተናግረው፥ “እያንዳንዱ የውይይቱ ጭብጥ ‘በኅብረት መጓዝ’ በሚለው ዘይቤ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ መነሻ ነጥብ፣ የጉዞ ጎዳና እና ሊደረስበት የሚገባ ግብ ያለው ነው” ብለዋል።

የቶኪዮ ሊቀ ጳጳስ የፍቅር ሥራ ዕይታ

ቀጥለው ንግግር ያደረጉት፥ በጃፓን የቶኪዮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ታርሲስዮ ኢሳኦ ኪኩቺ ሲሆኑ፥ሊቀ ጳጳስ አቡነ ታርሲስዮ በዚህ ወቅት “ካሪታስ ኢንተርናሽናልስ” የተሰኘ ካቶሊካዊ የፍቅር ሥራ ድርጅት፣ የጃፓን ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የእስያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ እንደ ነበሩ ታውቋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ታርሲስዮ በንግግራቸው፥ ጃፓኖች ውይይቱን በራሳቸው ዘይቤ ማካሄድ እንደሚመርጡ ገልጸው፥ በቡድን መናገር ለጃፓኖች ምን ያህል ከባድ እንደሆነም አስምረውበታል።

በእነዚህ ቀናት ውስጥ ውይይት እያደረጉበት ያለው ርዕሥ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ እስያ ውስጥ የተዘጋጀውን አህጉራዊ ጉባኤ በንዑሥ ቡድኖች አማካይነት በተሻለ ሁኔታ ማካሄዳቸውን ጠቅሰዋል። በአምስቱም የንዑሣን ቡድኖች ውይይት ላይ በመሳተፍ በቤተ ክርስቲያን አንድነት ውስጥ ያለውን ልዩነት ሙሉ በሙሉ ለመለማመድ በድጋሚ ዕድል ማግኘታቸውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ታርሲስዮ አስረድተዋል። እስያ ውስጥ ብዙ ቋንቋዎች እና ብዙ እውነታዎች መኖራቸውን የተናገሩት የቶኪዮ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ታርሲስዮ፥ ከሁሉም ሰዎች ጋር በአንድ መንገድ ብቻ መጓዝ እንደማይቻል እና ሲኖዶሳዊነት ማለት ሁሉ አንድ ዓይነትነት ማለት እንዳልሆነ፥ ነገር ግን ግለሰቦችን እና ባሕሎችን በተገቢው መንገድ ማክበርን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል

ሊቀ ጳጳሱ ቀጥለውም፥ የካሪታስ ኢንተርናሽናልስ ፕሬዝዳንት በመሆን ስላበረከቱት አገልግሎት ሲናገሩ፥ "እያንዳንዱ የካሪታስ ድርጅት በቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ጉዞ ውስጥ መሠረታዊ እንደሆነ፥ ሁሉም ድርጅቶች ካቶሊካዊ ማንነት እንዳላቸው፥ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋርም በንቃት እንደሚተባበሩ እና በተጨማሪም የክርስቲያኖች እና የሌሎች እምነቶች እሴቶች ያሏቸው መሆኑን በመግለጽ፥ ሲኖዶሳዊነት ድርጅቱን በሚመሩበት አገር እና በሁሉም የዓለም ክፍሎች ከሚሠሩት ድርጅቶች ጋር ሊታይ እንደሚችል አስረድተዋል።

እህት ተሬዛ ባሮን፥ ስለ ተፈጥሯዊ የአፍሪካ ሲኖዶሳዊነት

የሐዋርያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እህቶች ማኅበር የበላይ አለቃ እና ዓለም አቀፍ የበላይ አለቆች ኅብረት ፕሬዚደንት አይርላናዳዊ እህት ሜሪ ቴሬዛ ባሮን በንግግራቸው፥ “አንድን መጽሐፍ አንድ ላይ ሆነው የሚያነቡ ሁለት ሰዎች የሉም” የሚለውን አባባል በመጥቀስ፥ በምስራቅ አፍሪካ የገጠር ሰበካ ውስጥ በመጀመሪያ የምንኩስና ሕይወት ወቅት የኖሩትን የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊት ልምድ በማስታወስ ባደረጉት ንግግር፥ የትውልድ አገራቸው የአይርላንድ ግማሽ በሚያክል አካባቢ ውስጥ በሚገኙ 35 መንደሮች ውስጥ ሁለት ካኅናት እና አንድ የትምህርተ ክርስቶስ መምህር ሐዋርያዊ አገልግሎት በማበርከት ላይ እንደሚገኙ በማስታወስ ሲኖዶሳዊነት ነገሮችን ከዚህ ልምድ በመነሳት እንድመለከት አድርጎኛል በማለት ተናግረዋል። 

እህት ሜሪ ቴሬዛ ባሮን በንዑሥ የውይይት ቡድኖች ውስጥ ያጋጠማቸውን ሲገልጹ፥ ሲኖዶሳዊነት አፍሪካ ውስጥ ከምእመናን ጋር በየእሑድ ከጭቃ በተሰራ ጎጆ ውስጥ ውሳኔዎችን በጋራ ለመውሰድ ከሚያደርጉት ስብሰባ ጋር ተመሳሳይ እንዳለው፥ ምዕመናኑ ትምህርት የቀሰሙ ባይሆኑም ከልብ የሚመነጭ እምነትን መካፈል መቻላቸውን እና የእያንዳንዱ ድምጽ ተመሳሳይ ክብደት ያለው እንደነበር አስታውሰዋል። ሲስተር ባሮን በመቀጠልም፥ "ከታች ጠንካራ ተሳትፎ ያላቸውን ወጣት ቤተ ክርስቲያናትን የበለጠ ማዳመጥን እንደሚገባ ተናግረው፥ በማኅበራቸው ውስጥ የምንኩስና ሕይወት በሲኖዶሳዊነት ላይ መመሥረቱን አረጋግጠዋል።

ሁሉም ሰው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የራሱ ድርሻ አለው

ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት እህት ፋዱል በበኩላቸው፥ የጋራ ሕይወት ምስክርነት  ሲኖዶሳዊነትን በተመለከተ ያበረከተውን አስተዋፅዖ ጠቅሰው፥ በተለይ የሶርያ ክርስቲያኖችን በጸሎት እየረዱ መሆናቸውን እና ኅብረት እንዲሰማቸው ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል። እህት ሜሪ ባሮን በሲኖዶሱ ሂደት ውስጥ የበላይ አለቆች ያላቸውን ተሳትፎ ጥቁመው፥ ሲኖዶሳዊነት የምንኩስናን ሕይወት እንዴት መኖር እንደሚቻል የሚያግዝ መሆኑ ተናግረው በማከልም፥ የአውታረ መረብ ላይ ስልጠና ምክረ ሃሳቦችን ለመጋራት እና ማኅበረሰብን ለመገንባት የሚሰጡትን ሦስት ጥቅሞች ተናግረዋል።

የሴቶችን የዲቁና አገልግሎት አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ እህት ሜሪ ባሮን ሲመልሱ፥ ጉዳዩን ሲኖዶሳዊ ሂደቱ እያሰላሰለበት እንደሚገኝ ገልጸዋል። የተለያዩ አስተያየቶች መኖራቸው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውበት ባህሪ ነው ብለው፥ ነገር ግን ውይይት እየተካሄደ ባለበት በዚህ ጊዜ ከዚህ በላይ መናገር ትክክል አይሆንም ብለዋል። በዚህ ረገድም እህት ፋዶል በምላሻቸው፥ ሁሉም ሰው የእግዚአብሔርን ስጦታዎች መጠቀም በመማር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወንድ እና ሴት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አፅንዖት ሰጥተዋል። ሊቀ ጳጳስ ግሩሻስም በማከል፥ በሲኖዶሱ ውስጥ በተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች ላይ የሚደረገው ክርክር የዚህ ሰፊ ውይይት አካል እንደሆነ ገልጸው፥ ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው አዎ ወይም አይደለም፣ ጥቁር ወይም ነጭ የሚል መልስ እንደሚፈልግ ተናግረዋል። በባህላዊ ዳራ ላይ የተመሰረቱ የሃሳብ ልዩነቶች እንዳሉ ግልጽ ነው ብለው፥ ስለዚህ በዚህ ደረጃ ላይ ውሳኔ መስጠት ያዳግታል ብለዋል።

በድጋሚ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሊቀ ጳጳስ ግሩሻስ ሲመልሱ፥ የጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝደንቶች በቀኖና ሕግ ውስጥ ሲኖዶሳዊ የሆኑ እና በውጤታማነት ሊተገበሩ በሚችሉ በርካታ መዋቅሮች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።  የቶኪዮ ሊቀ ጳጳስ እንደተናገሩት፥ በወረርሽኙ ወቅት ሰዎችን አንድ ላይ በመሰብሰብ በሲኖዶሳዊነት ላይ ለመወያየት ዕድል ባላመገኘቱ የአውታረ መረብ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው፥ ምእመናንን በሲኖዶሳዊነት ውይይት ማሳተፍ ከተፈለገ ተግባሮቻቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ አሳስበዋል።

 

 

 

21 October 2023, 17:20