ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ክርስቶፍ ሾንቦርን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ክርስቶፍ ሾንቦርን  

ካርዲናል ክርስቶፍ፥ ሲኖዶሳዊነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በኅብረት የሚኖሩበት መንገድ እንደሆነ ገለጹ

በአውስትሪያ የቪዬና ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ክርስቶፍ ሾንቦርን መጭውን የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤን አስመልክተው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ሲኖዳዊነት በቤተ ክርስርቲያን ውስጥ በኅብረት ለመኖር የሚያግዝ መንገድ አንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሲኖዶሳዊነት የቤተ ክርስቲያንን ልዩ የአኗኗር ዘይቤ እና ተግባር የሚመለከት፥ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች በመሳተፍ መላው የእግዚአሔር ሕዝብ በአንድነት የወንጌል ሕይወት እንዲኖሩ መንገድ የሚያሳይ መሆኑን የቪየና ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ክርስቶፍ ገልጸዋል። ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ በቃለ ምልልሳቸው፥ የመጪው ሲኖዶስ የትኩረት አቅጣጫን በማስመልከት በሰጡት ጠቅላላ ጭብጥ፥ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጊዜ እያካሄደች ያለችውን ሲኖዶሳዊ ሂደት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1985 ዓ. ም. አጽንዖት ሰጥታ ከጀመረችው ጉዞ ጋር ኅብረት እንዲኖረው ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል።

በዚህ ሲኖዶስ ውስጥ ብዙ ነገሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ የተናገሩት ብፁዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የማዳመጥ እና የማስተዋል ልዩ መንገድን እንድንለማመድ አድርገዋል ብለዋል። “የማዳመጥ እና የማስተዋል መንገድን መጓዝ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዘወትር አስፈላጊ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማስተዋል ለሚለው ቃል የሰጡትን ትኩረት  በማስታወስ፥ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ ምን እንደሚያሳይ እና ምን ማድረግ እንደሚፈልግ መረዳት አስፈላጊ እንደሆነ መናገራቸውን በመጥቀስ፥ ሲኖዶስም ይህን የማስተዋል መንገድ በጥልቀት ለመማር እና ለመለማመድ የሚደረግ ሙከራ እንደሆነ አስረድተዋል።

የሀገረ ስብከት ሲኖዶስ በሕግ ቀኖና የተደነገጉ ደንቦች አሉት ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፥ ሃሳባቸውን ለብዙ ምዕመናን ማካፈላቸውን እና የሀገረ ስብከታቸው ምክር ቤት ሌሎች የተሻሉ መንገዶችን መከተል እንዳለበት አስተያየት ማቅረባቸውን ገልጸው፥ ከቁምስናዎች፣ ከተቋማት፣ ከገዳማት እና ከሀገረ ስብከቱ ነባራዊ ሁኔታ ከተወጣጡ ወደ 1,500 ከሚደርሱ ልዑካን ጋር መሰብሰባቸውን ገልጸዋል።

የስብሰባቸው መሪ ሃሳብ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደጋግመው የሚጠቅሱት እና በሐዋርያት ሥራ ላይ የምናነበው የሐዋርያት ጉባኤ እንደሆነ ገልጸው፥ ከእግዚአብሔር ጋር በሚደርጉት ጉዞ ወቅት ስላጋጠማቸው፥ እግዚአብሔር በሕይወታቸው እና በቁምስናቸው ውስጥ የሚሆነውን እንዲያስታውሱት ያደረጋቸውን ነገሮች እርስ በርስ መነጋገር እንደሚገባ ለሀገረ ስብከታቸው ሐሳብ ማቅረባቸውን አስረድተዋል።

በውይይታቸው ወቅት የተጠቀሙት ዘዴ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የተጻፈ እንደነበር ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፥ በሐዋርያት ዘመን ወደ ክርስትና ሕይወት የመጡ አረማውያን ጉዳይ ችግር ይፈጥር እንደነበር አስታውሰው፥ አረማውያኑ መጠመቅ አለባቸው ወይስ የለባቸው? ከተጠመቁ የአይሁድን ሕግ መከተል ነበረባቸው ወይንስ በክርስቶስ ማመናቸው በቂ ነበር? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ የአንዳንድ ሰዎች ልምድ በማስተዋል ምላሽ መስጠታቸውን አስታውሰዋል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ከተናገረ በኋላ ጳውሎስ እና በርናባስ ተናግረው በመጨረሻም መላው ጉባኤ ካዳመጣቸው በኋላ ጸሎት በማድረግ በመጨረሻ “መንፈስ ቅዱስ እና እኛ በጋራ ወስነናል” ወደሚለው መደምደሚያ መድረሳቸውን አስታውሰዋል።

በሀገረ ስብከታቸው ውስጥ ያለውን ግኑኝነት በማጠናከር የሐዋርያዊ ተግባር ጅምርን ማበረታታት የመጀመሪያው ተግባራቸው እንደነበር የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፥ የምክር ቤት ምርጫን ሳያካሂዱ፥ ደንቦችን ሳያወጡ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት የተካፈሉት ከልምዳቸው አንፃር ብቻ እንደነበር ገልጸው፥ በቤተ ክርስቲያን ታማኝነት ላይ ችግር ባጋጠመበት ወቅት የተደረገ አዎንታዊ ተሞክሮ እንደ ነበር በማስታወስ፥ ይህም በጠንካራ የእምነት እና የመተሳሰብ ልምድ በመታገዝ በእርግጠኝነት እና በተስፋ ወደፊት እንዲራመዱ እንደረዳቸው አስረድተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያን በ1985 ዓ. ም. የተካሄደውን የሲኖዶስ ጉባኤ እንደ ጳጳስ ሳይሆን እንደ ነገረ መለኮት ሊቅ መካፈላቸውን የሚያስታውሱት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፥ ጉባኤው ከተካሄደ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ቢሆን በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ይጠቀስ የነበረው መሪ ቃል አንድነት ወይም ኅብረት የሚል እንደሆነ

ገልጸው፥ አንድነት የቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ገጽታ እንደ ሆነና በሲኖዶስ ውስጥ የሚገኝ ሲኖዶሳዊነትም ተመሳሳይ እንደሆነ አስረድተዋል። ሲኖዶሳዊነት የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚገለጽበት፥ በአስተዳደር ጉዳዮች እና ውሳኔዎች ላይ መሳተፍ፣ በአጠቃላይ በቤተ ክርስቲያን የሕይወት ገፅታዎች ላይ መሳተፍ እንደሆነ ገልጸው፥ በሲኖዶስ ውስጥ የሚገኝ ሲኖዶሳስዊነት በቤተ ክርስቲያን አንድነት ውስጥ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በሕብረት በሚያደርጉት ጉዞ ወቅት የወንጌል ሕይወት እንዴት እንደሚኖሩ የሚገልጹበት መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው ሲኖዶሳዊነት ሁል ጊዜ የአንድነት ፍለጋ እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፥ ሲኖዶሳዊ ጉዞን ለማካሄድ ሁሉም ሰው ተመሳሳይ መንገድ መምረጥ እንደሚገባ ተናግረው፥ ይህ ጉዞ እውነትን ፍለጋ ወደ ፊት የሚራመደውን የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ ማዳመጥ እንደሆነ አስረድተው፥ ሲኖዶስ ምክክር የሚደረግበት እንጂ ሕግ አውጭ አካል አለመሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ በመግለጽ፥ ሲኖዶስ የመንፈስ ቅዱስን ድምጽ ለማዳመጥ የሚያገለግል እንደሆነ አስረድተዋል።

በዚህ ምክንያት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁለቱንም ማለትም የቤተሰብ ሲኖዶስ እና ይህ ሲኖዶስ በሁለት ወይም በርካታ ደረጃዎች ማለትም በአካባቢያዊ እና አኅጉራዊ ደረጃ በማካሄድ በመጨረሻም ሁለቱ የሲኖዶስ ጉባኤዎች ወደ አንድነት የሚወስደውን መንገድ መያዝ እንደሚገባ መፈለጋቸውን ገልጸው፥ ይህ ስምምነት የመንፈስ ቅዱስ ምልክት እንደሆነ ተናግረዋል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያልሆኑትን ወይም ከቤተ ክርስርቲያን ርቀው የሚገኙ ምዕመናን ድምፅ ማዳመጥም አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፥ የእነዚህን ምዕመናን ድምጽ ማዳመት ነገሮችን በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንደሚረዳ አስረድተዋል። ስናዳምጥ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ስሜት በሚገባ መረዳት እንደሚገባ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ክርስቶፍ፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የቤተ ክርስቲያን የእምነት ልብ እንደሆነ አስረድተዋል።

ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በተካሄዱት የሲኖዶስ ጉባኤዎችን እንደ አድማጭነት ወይም እንደ ሊቃውንት የተሳተፉት ወንድ እና ሴት ምእመናን እንደነበሩ ያሳወሱት ካርዲናል ክርስቶፍ፥ በዚህኛው ሲኖዶስ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሩ ቁጥር ያላቸው ምእመናን እንደሚሳተፉ ገልጸው፥ ይህም የሲኖዶሱን መሠረታዊ ዓላማ እንደማይለውጠው እና የሲኖዶስ ትውፊት ከሁሉም በፊት የአካባቢዎች እና የአኅጉራት እርስ በርስ መገናኘትን የሚፈልግ በመሆኑ የምእመናን ተሳትፎን ለማሻሻል አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።

የምዕመናን ሰፊ ተሳትፎ ውጤት ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲብራራባቸው በነበሩት ሲኖዶሳዊ የሙከራ ዘዴዎች ውስጥ መካተቱን የገለጹት ካርዲናል ክርስቶፍ፥ ሴት ምዕመናን  በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖራቸው፣ ከሞራል ሥነ መለኮት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን እንደገና ለማሰብ የተለየ የማሻሻያ ጥያቄዎችን ለማቅረብ እንደሚረዳ ገልጸዋል። ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ያላቸው ተሳትፎ አስቀድሞ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ውስጥ ዋና ጭብጥ እንደ ነበር ያስታወሱት ካርዲናል ክርስቶፍ፥ የምእመናን ተሳትፎ የጉባኤው ዓላማ ማዕከል ቢሆንም ገና ብዙ መማር እና መሥራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

የቀድሞው ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ሃያ ሦስተኛ ቀደም ሲል በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሴቶች ጭብጥ ከዘመናት ምልክቶች መካከል አንዱ እንደሆነ፥ በዓለም ዙሪያ ከሚነሱት ታላላቅ ጥያቄዎች መካከልም አንዱ እንደሆነ እና ይህ ጭብጥ በተለይም ከምዕራቡ ዓለም ርዕዮት ዓለም ጋር ተያይዞ  አከራካሪ ርዕሦችን የያዘ እንደሆነ ተናግረዋል። እምነትን በማስተላለፍ ረገድ ቤተሰብ የሚቻወተው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ የተናገሩት ካርዲናል ክርስቶፍ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2014-15 ዓ. ም. የተካሄደው ድርብ የቤተሰብ ሲኖዶስ፥ ቤተሰብ እምነትን ለልጆች ለማስተላለፍ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

እምነትን ለሌሎች ማስተላለፍ የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ፥ ሰዎችን ወደ እምነት የሚጠራው እና በልባቸው ውስጥ የሚሆነው እግዚአብሔር እርሱ እንደሆነ ገልጸው፥ ይህን የእግዚአብሔር ሥራ ሰዎች እንዲረዱት የሚያግዙ ሰዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል። “በዚህ ዘመን ዓለማዊነት ትልቁ ፈተና ነው” ያሉት ካርዲናል ክርስቶፍ፥ የቀድሞው ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ ስለ ዓለማዊ ማኅበረሰብ የተናገሩትን አስገራሚ ነገር አስታውሰዋል።

ዓለማዊነት ጉዳት ብቻ ሳይሆን አዎንታዊ ጎንም አለው ያሉት ካርዲናል ክርስቶፍ፥ ግለሰባዊ የህልውና ጥያቄዎችን የሚያነሱ ሰዎች ምናልባት የበለጠ ቀጥተኛ መንገድ የሚከተሉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ገልጸው፥ መንቃት እንደሚገባ፥ ቅዱስ ወንጌል የሕይወት ሃይል እንደሆነ እና ሕይወትን እንደሚያነሳሳ በማስረዳት ከዚህ አንጻር ይህ ሲኖዶስ ምንም ዓይነት ትችት ቢሰነዘርበትም የቤተ ክርስቲያንን ኅብረት ለማስቀጠል አንድ እርምጃ እንደሚሆን ሙሉ እምነት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

 

20 September 2023, 16:30