ፈልግ

የሲኖዶሱን ጠቅላላ ጉባኤ በማስመልከት መግለጫ ሲሰጥ የሲኖዶሱን ጠቅላላ ጉባኤ በማስመልከት መግለጫ ሲሰጥ  

በሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የጸሎትን ማዕከላዊነት የሚገልጽ ሥነ-ሥርዓት እንደሚፈጸም ተገለጸ

የሲኖዶስ መሪዎች፥ በቫቲካን ሊካሄድ በታቀደው የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ዋዜማ፥ ማለትም ቅዳሜ መስከረም 19/2016 ዓ. ም. ታላቅ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንደሚካፈጸም አስታወቁ። ይህም በሲኖዶሳዊ ሂደት ውስጥ የጸሎት ማዕከላዊነት እንደሚያጎላ እና በሲኖዶስ እና በቅዱስ ቁርባን መካከል ያለውን ግንኙነት ግልጽ ያደርገዋል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚሳተፉበት እና ቅዳሜ መስከረም 19/2016 ዓ. ም. እንደሚካሄድ የሚጠበቀው ታላቅ የጸሎት ሥነ-ሥነ ሥርዓቱ፥ በሮም የሚካሄደው የሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ መከፈቻ ሲሆን፥ በእግዚአብሔርን ሕዝቦች መካከል ሁለት መሠረታዊ ገጽታዎችን፥ ማለትም በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን ወንድማማችነት እና በአንድነት ጎዳና ወደፊት ለመራመድ በሚደረግ ጥረት የጸሎትን ማዕከላዊነት እና የውይይት አስፈላጊነትን የሚያጎላ እንደሚሆን ተነግሯል።

የጸሎት እና የክርስቲያኖች አንድነት አስፈላጊነት

በቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል በኩል ጠቅላላ መርሃ ግብሩን ያስተዋወቁት የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ፥ እህት ናታሊ ቤክርት እንደገለጹት፥ በሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ ዋዜማ ላይ የሚፈጸመው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት፥ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ “አንድነት” እና “ሰላም” የሚሉት መሪ ቃላት እንደሆኑ ገልጸው፥ ጸሎት ለክርስቲያኖች አንድነት እጅግ አስፈላጊነት መሆኑን በማሳየት፥ የሲኖዶሱን ጉባኤ ለመንፈስ ቅዱስ በአደራ አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የቁስጥንጥንያውን የክርስቲያኖች ውኅደት ፓትርያርክ ብጹ ዕ ወቅዱስ በርተሎሜዎስ ቀዳማዊን ጨምሮ አሥራ ሁለት የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮችን እንደሚቀላቀሉ የገለጹት እህት ናታሊ ቤክርት፥ በእንግሊዝ የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጀስቲን ዌልቢ እና ሌሎች በርካታ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ያልሆኑ ወንድሞችም በሲኖዶሱ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

አስቀድሞ የነበረውን አንድነት በኅብረት ማክበር

የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በኅብረት ሆነው በሮም በሚቀርብ የጸሎት ምሥክርነት ላይ ወጣቶች ትልቅ ሚና የሚኖራቸው ሲሆን፥ ተነሳሽነቱ በታይዘው የቀድሞው ወንድም አሎይስ አስተባባሪነት የተጀመረ እና በሲኖዶሳዊ ሂደት ወቅት በኢየሱስ ክርስቶስ የተገኘውን አንድነት በማክበር አብያተ ክርስቲያናት ያሳዩት ተጨባጭ ተነሳሽነት እንደሆነ ተገለጿል።

በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ከ40 የሚበልጡ አገራትን የሚወክሉ 3,000 የሚሆኑ ወጣቶች ቅዳሜ መስከረም 19 እና እሑድ መስከረም 20/2016 ዓ. ም. በሮም ተገኝተው በመገኘት  ዎርክሾፖችን፣ ምስክርነቶችን፣ የውዳሴ እና የአምልኮ ዝግጅቶች እንደሚካፈሉ መርሃ ግብሩ አመልክቷል።

ዓርብ ጳጉሜ 3/2015 ዓ. ም. በተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የታይዘው ወንድም ማቲው እንደተናገሩት፥ የጋራ ስብሰባው በተለይ ወጣቶችን በማሳተፍ የሲኖዶሱን ተጨባጭነት ለመግለፅ ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል።

ወንድም ማቲው፥ ወጣት ነጋዲያኑ በጸሎት ዝግጅቱ ዋዜማ ላይ ሮማ ውስጥ ከሚገኝ የቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ጀምረው በቫቲካን ወደሚገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ድረስ መንፈሳዊ ንግደት እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ በተመሳሳይ ዕለት በዓለም ዙሪያም ጭምር የሚቀርቡ በርካታ የጸሎት ዝግጅቶች መኖራቸው ተናግረዋል።

ወንድም ማቲው አክለውም፥ ቅዳሜና እሁድ የሚያካሄዱት ሰፊ ዝግጅቶች፥ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ስብሰባ እና የክርስቲያንኖች አንድነት የጋራ ጸሎት፥ ቀድሞውኑ በሂደት ላይ የሚገኝ ሲኖዶሳዊነት ምሳሌዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ስለ ሲኖዶስ ለሌሎች መናገር

በመጨረሻም፥ የሲኖዶሱን ጠቅላላ ጉባኤ የመረጃ ኮሚሽንን በፕሬዝዳንትነት እንዲመሩት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተመረጡት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ስለ መጪው የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ ዝርዝር መረጃን አካፍለዋል።

የሲኖዶሱ ጠቅላላ ጉባኤ መርሐ ግብር ዝርዝር ሁኔታ ገና ያልተጠናቀቀ ቢሆንም፥ የሲኖዶሱ ጉባኤ የሥራ ሂደት በሞዴሎች መከፈሉን የጠቀሱት ዶ/ር ሩፊኒ፥ አንድ ወር የፈጀው ስብሰባው፥ እስካሁን የተከናወኑ የሥራ ውህደቶችን በማዘጋጀት ላይ ያተኮረ እና የመጨረሻ ሞደሉ ዋና ዋና ነጥቦችን ማለትም፥ ሲኖዶሳዊነት፣ ኅብረት፣ ተልዕኮ እና ተሳትፎ የሚሉትን ርዕሠ ጉዳዮች ያካተተ እንደሆነ ተናግረዋል።

በሲኖዶሱ ጉባኤ ወቅት የሚነሱ ርዕሠ ጉዳዮችን ለሌሎች ማድረስን በተመለከተ የተናገሩት ዶ/ር ሩፊኒ፥ ስለ ሲኖዶሱ የሚያስተላልፉበት መንገድ በሲኖዶሱ እና በመላው ቤተ ክርስቲያን የማሰላሰል ሂደት ላይ  ጠቃሚ እንደሆነ አስረድተዋል።

ዶ/ር ሩፊኒ አክለውም፥ ምስጢራዊነትን፣ ግላዊነትን እና የአንዳንድ መድረኮች ቅዱስነት መጠበቅ፥ እነዚህ ጊዜያት ለማድመጥ፣ ለማስተዋል እና በኅብረት ላይ የተመሠረተ ጸሎትን ለማድረግ ካለው ፍላጎት ጋር ተዳምሮ እውነተኛ እና ጠቃሚ ዕድል መሆናቸውን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ የወሰደው አካሄድ፥ የሲኖዶስ አባላት አንድ አካል ሆነው እርስ በርስ እንዲተዋወቁ እና እንዲደማመጡ የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጸው፥ ጉባኤው የሲኖዶሱ አካል የሥራ ሂደቱን ጠቅለል አድርጎ የሚገልጽ የሲኖዶስ ሠነድ እንደሚያዘጋጅ ጠቁመው፣ ነገር ግን ሠነዱ የመጨረሻው እንደማይሆን እና ሲኖዶሱ በሚቀጥለው ዓመት ሁለተኛ ጉባኤውን እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል።

ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ንግግራቸውን ሲደመድሙ፥ እንዲህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የኅብረት ጥረት ታሪክ የሚሠራበት መንገድ እንደሆነ አጥብቀው ተናግረው፥ በጉባኤው ወቅት ጋዜጠኞችን ለማገዝ የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉላቸው በመግለጽ፥ ጋዜጠኞችም በዚህ እምነት እንዲኖራቸው ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

 

09 September 2023, 16:23