ፈልግ

በጄኔቭ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽ/ቤት በጄኔቭ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽ/ቤት  (BENEDETTA BARBANTI)

ቅድስት መንበር፥ ሰብዓዊ መብቶችን በሰው ልጅ ክብር ውስጥ ማስፈን እንደሚያስፈልግ አሳሰበች

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ አዲስ የተሰየሙት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ፥ መስከረም 2/2016 ዓ. ም. በጄኔቫ በተካሄደው 54ኛው የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ባሌስትሬሮ ለጉባኤው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፥ አብዛኛዎቹ መንግሥታት ስላረጋገጡት ብቻ ፅንስን ማስወረድ ሰብዓዊ መብት ሊሆን እንደማይችል ምክር ቤቱን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

 የቅድስት መንበርን አቋም በማንጸባረቅ፥ “ሰብዓዊ መብቶችን በሰው ልጅ የጋራ እና የማይገረሰስ ክብር ውስጥ ማካተቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለለበት” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ፥ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር፥ "ከራስ ወዳድነት፣ ከግለሰባዊነት እና የመከፋፈል ሰለባ ከመሆን ይልቅ ወደ አንድነት ይመራል” ብለዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ከዚህ ጋር አያይዘው እንደተናገሩት፥ የቀድሞው ር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሚያዝያ 18/2008 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ በላኩት መልዕክት፥ የስምምነቱ ውስጣዊ ይዘት የሰውን ልጅ ክብር ከመጠበቅ ይልቅ የጥቂቶችን ፍላጎት ለማርካት ያለመ በመሆኑ የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ውሳኔ መሠረቶች እንደገና ሊጤኑ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን አስታውሰዋል።

75 ዓመታትን ያስቆጠረው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ውሳኔ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሰባዓዊ መብቶች ድንጋጌ የፀደቀበት 75ኛ ዓመት ዘንድሮ መከበሩን ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ፥ "ሰብዓዊ መብት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስምምነት ለግለሰቦች የሚሰጠው መብት ብቻ ሳይሆን ይልቁንም ለሰው ልጅ ዕድገት አስፈላጊ የሆኑትን ተጨባጭ እና ጊዜ የማይሽራቸው እሴቶችን የያዘ ነው” ብለዋል።

“አዲሶቹ መብቶች ለአብላጫ ድምጽ ሕጋዊነትን አይሰጡም”

“አዲሶቹ መብቶች ለአብላጫ ድምጽ ሕጋዊነትን አይሰጡም” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ፥ ይህ ማለት አንድ ድርጅት ወይም ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በድንጋጌው ውስጥ የተካተቱትን አንድ ወይም ብዙ መብቶችን ለመቀበል ፍቃደኛ ባይሆንም የመብቱን ትክክለኛነት ከማክበር ነፃ አያደርጋቸውም" ብለው፥ ነገር ግን ደግሞ "አዲስ መብቶች" የሚባሉት ሕጋዊነትን እንዳያገኙ በቁጥር ብዙ ግለሰቦች ወይም ክልሎች ስላረጋገጡ ብቻ ሕጋዊነትን አያገኙም” ብለዋል። ለዚህ የተሳሳተ የመብቶች ጽንሰ-ሀሳብ አብይ ምሳሌ የሚሆነው፥ “ፅንስ የማቋረጥ መብት” በሚል ሰበብ በየዓመቱ የ 73 ሚሊዮን ንፁሃን ሰው ሕይወት መጥፋት እንደሆነ ሊቀ ጳጳሱ አስረድተዋል።

አሁንም በርካታ አቅመ ደካሞች ይገለላሉ

ታሪካዊውን የሰባዓዊ መብቶች ድንጋጌን ያስታወሱት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ፥ የምሥረታውን 75ኛ በዓል በማስመልከት እንደተናገሩት፥ “ከ75 ዓመታት በኋላ ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አሁንም በጦርነት፣ በግጭት፣ በረሃብ እና በአድልዎ እየተሰቃዩ መሆናቸው ምን ያህል አሳዛኝ ነው” በማለት አስምረውበታል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማያሻማ መልኩ የወንድማማችነት መንፈስ ካለመኖሩ የተነሳ ዛሬ ብዙ ሰዎች አቅመ ደካማ፣ ድሃ ወይም ዋጋ የሌለው በመባል ውግዘት እንደሚደርስባቸው ገልጸው፥ አንዳንድ ባሕላዊ ደንቦች ችላ በመባላቸው፥ በማኅበረሰቡ ውስጥ የተገለሉትን እንዲያውም የማስወገድ ስጋት መኖሩን ተናግረው፥ በዚህ ምክንያት የምሥረታ በዓሉ "የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃን መሠረት በማድረግ በእነዚያ መሠረታዊ መርሆች ላይ ለማሰላሰል ጠቃሚ ዕድልን ይሰጣል" ብለዋል።

የድሆችን ሁለንተናዊ መብቶች መደገፍ

ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርስ መድልኦ እና የመገለል ዝንባሌን ለመዋጋት፥ ለድሆች እና በማኅበረሰቡ ለተገለሉት ወገኖች ቅድሚያ በመስጠት ዓለም አቀፋዊ መብቶቻቸውን መደገፍ እና ማሳደግ፥ እንዲሁም ለጋራ ጥቅም የበኩላቸውን እንዲወጡ ማድረግ አስፈላጊ ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተደጋጋሚ ያቀረቡትን ጥሪ ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ፥ የመናቅ ባሕልን መዋጋት እንደሚገባ፥ ለድሆች እና በማኅበረሰቡ ለተገለሉ ሰዎች የሚሆኑ አማራጭን መቀበል፥ ዓለማቀፋዊ መብቶቻቸውን ማስከበር፥ በልጽገው ለጋራ ጥቅም እንዲውሉ ማስቻል አስፈላጊ" እንደሆነ ማሳሰባቸውንም ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰኔ 14/2015 ዓ. ም. ጀምሮ ጄኔቫ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዲስ የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ አድርገው የሰየሟቸው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ኤቶሬ ባሌስትሬሮ፥ ለ54ኛው የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ያደረጉትን ንግግር ሲደመድሙ እንደተናገሩት፥ ቅዱስነታቸው “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፥ "ሌሎችን የማክበር ባሕል ተግባራዊ በማድረግ እና በማስተማር፥ ልዩነቶችን መቀበል በሚችል ፍቅር በመታገዝ ለእያንዳንዱ ሰው ሃሳብ፣ አስተያየት እና ተግባር ክብር በመስጠት፥ ሌላው ቀርቶ ስሕተቱንም ጭምር እንድንቀበል መጋበዛቸውን አስታውሰዋል።

 

14 September 2023, 17:02