ፈልግ

የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ  (Vatican Media)

ሲኖዶስ እና ማኅበራዊ መገናኛ በሚል ርዕሥ የአንድ ቀን ስልጠና መካሄዱ ተገለጸ

መስከረም 23/2016 ዓ. ም. የሚጀመረውን 16ኛ የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤን በማስመልከት ለጋዜጠኞች የተዘጋጀ የአንድ ቀን ስልጠና በሮም መካሄዱ ታውቋል። ሮም ውስጥ በሚገኝ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 8/2016 ዓ. ም. የተካሄደውን የአንድ ቀን ስልጠና ያስተባበረው “ግሪንአኮርድ” የተሰኘ ክርስቲያናዊ የባሕል ድርጅት ሲሆን፥ በጋራ ያዘጋጁትም በቅድስት መንበር የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እና የመገናኛ ጽሕፈት ቤት መሆናቸው ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ለሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን፡ አንድነት፣ ተሳትፎ እና ተልዕኮ” በሚል ርዕሥ መስከረም 23/2016 ዓ. ም. እንደሚጀምር ለሚጠበቀው 16ኛ የሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ጥቂት ሳምንታት ብቻ እንደቀሩት ያታወቃል። የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከመስከረም 23 እስከ ጥቅምት 18/ 2016 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፥ የዚህ ጉባኤ ሁለተኛው እና መጨረሻው ክፍለ በጥቅምት ወር 2017/ ዓ. ም. እንደሚካሄድ ታውቋል።

የጉባኤውን ዝግጅት እና ሂደት ለመላው ምዕመናን እንዲዘግቡ የተጠሩትን ሚዲያዎች ለማዘጋጀት በሚል ዓላማ፥ “ግሪንአኮርድ” የተሰኘ ክርስቲያናዊ ድርጅት፥ የብጹዓን ጳጳሳት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እና በቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት በጋራ ያዘጋጁትን የአንድ ቀን ሥልጠና ማስተባበሩ ታውቋል። “ሲኖዶሱ ከመገናኛ ብዙሃን የሚጠብቀው እና መገናኛ ብዙሃኑ ከሲኖዶሱ የሚጠይቀው” በሚሉ ሁለት ርዕሦች ላይ ከሚቀርቡ የሁለት ዙር ስልጠናዎች መካከል የመጀመሪያው ዙር፥ ዛሬ ማክሰኞ መስከረም 8/2016 ዓ. ም. ሮም በሚገኝ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት እስከ ማታ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ መካሄዱ ታውቋል።  

"ሲኖዳሳዊነት የእግዚአብሔር ሕዝቦች የወንጌልን መልካም ዜና ለማብሰር አብረው እንደሚጓዙ እና የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት እና ተልዕኮ ብቁ የሚያደርግ ልዩ ዘይቤ መሆኑን ያመለክታል” ያሉት የ “ግሪንአኮርድ” ክርስቲያናዊ ድርጅት ፕሬዘደንት አቶ አልፎንሶ ካውቴሩቾ፥ ይህም ቀላል የሆኑ የአስተዳደር ጥያቄዎችን   ወይም የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች አንድነትን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ይልቁንም የቤተ ክርስቲያንን ልዩ የአኗኗር ዘይቤ እና ተግባር የሚመለከት ነው” በማለት አስረድተዋል።

የሲኖዶሱ ሁለት ዙር ጉባኤዎች

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1965 ዓ. ም. ማቋቋማቸው ይታወሳል። እርሳቸው የተናገሩትን በመድገም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቅዱስ ሲኖዶስ የማማከር ሚና እንዳለው ገልጸው፥ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮችን በተመለከተ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መረጃ እና አስተያየት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው ላይ እንደገለጹት፥ ዓላማው የውይይት ርዕሠ ጉዳዮች በተለያዩ ደረጃዎች እና ዘዴዎች መደምደሚያቸው ለእግዚአብሔር ሕዝብ በተሻለ መንገድ የሚገለጽበት መንገድ እንደሆነ ያስረዱት አቶ አልፎንሶ ካውቴሩቾ፥በጉባኤው ላይ የሚነሱ ርዕሠ ጉዳዮች ባለሙያዎች ዘንድ ብቻ እንዳይቀሩ በጋዜጠኞች መተርጎም አለባቸው” ብለዋል።

ይህን ሃሳብ ማዕከል በማድረግ በሁለት የተከፈለው ሥልጠናው በጠዋት ዝግጅቱ ለሲኖዶሱ ጭብጦች እና ዘዴዎች ጊዜን በመስጠት የሚወያይ እና ከሰዓት በኋላ የሚኖረውን ክፍለ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ለቫቲካን መገናኛ ጽሕፈት ቤት በመስጠት፥ ከጉባኤው በፊት፣ በጉባኤው ወቅት እና ከጉባኤው በኋላ የከናወነውን ማወቅ ለሚፈልጉ ጋዜጠኞች ድጋፍ መስጠትን የሚመለከት እንደሆነ አስታውቀዋል። ስልጠናው በተጨማሪም “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የሚለውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን መመሪያዎችን በማክበር የቤተ ክርስቲያን በዓላት ሊኖራቸው የሚገባቸውን ባህሪያት ግምት ውስጥ በማስገባት፥ የካርበን ሊቀትን በማካካስ ረገድ ሲኖዶሱ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ላይ እንደሚወያይ ታውቋል።

በስልጠናው ንግግር የሚያደርጉት አባላት

በስልጠናው መጀመሪያ ላይ ንግግር ያደረግጉት የሲኖዶሱ ጠቅላይ ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች፥ የሲኖዶሱ ልዩ ጸሐፊዎች ክቡር አባ ጃኮሞ ኮስታ እና ክቡር አባ ሪካርዶ ባቶኪዮ፣ ሮም ከሚገኝ ጎርጎሮሳዊ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ ክቡር አባ ዳሪዮ ቪታሊ፣ በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የክርስቲያኖች አንድነት ማስፋፊያ ጽሕፈት ሞንሲኞር ሃይቺንቴ ዴስቲቬል፣ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን የገዳምውያት አንድነት የቀድሞ ፕሬዚዳንት እህት ናዲያ ኮፓ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ እህት ናታሊ ቤካርት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ  አባ ሉዊስ ማሪን ደ ሳን ማርቲን፣ በጳጳሳዊ ምክር ቤት ውስጥ ሕግ አውጭ ክፍል የቀድሞ ፕሬዝደንት ብፁዕ ካርዲናል ፍራንችስኮ ኮኮፓልሜሪዮ፣

በቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ አማካሪ ሮሚልዳ ፌራውቶ፣ የቫቲካን መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ፣ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ዳይሬክተር አቶ አንድሪያ ሞንዳ፣ ከጎርጎሮሳዊ ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ አባ ዋልተር ኢንሴሮ፣ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ጸሐፊ ክቡር አባ ሉሲዮ አድሪያን ሩዪዝ እና ክቡር አባ ዳሪዮ ቪታሊ፣ የጳጳሳዊ ግሪጎሪያን ዩኒቨርሲቲ; ኣብ ዳይካስተር ፎር ኮሙኒኬሽን ጸሓፊ፡ የቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ዘላቂ ፕሮጀክት ሳይንሳዊ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ዋልተር ጋናፒኒ፣ የላይፍ ጌት መገናኛ እና ሳይንስ ዳይሬክተር ዳይሬክተር ወ/ሮ ሲሞና ሮቬዳ እና አቶ ሲሞኔ ሞልቴኒ መሆናቸው ታውቋል።

በስልጠናው ወቅት የቀረቡ ንግግሮችን የመሩት፥ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ አቶ ፓኦሎ ሩፊኒ፣ “ሎዜርቫቶሬ ሮማኖ” የተሰኘ የቅድት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ክፍል ጋዜጠኛ ሲልቪያ ጉይዲ፣ በጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የብሔራዊ ማኅበራዊ መገናኛ ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ቪንቼንሶ ኮራዶ እና የጣሊያን ቴሌቪዥን “TG2” ጋዜጠኛ ክርስቲና ሩጄሪ መሆናቸው ታውቋል።  

 

19 September 2023, 16:26