ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥  

ብፁዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥ ለመጪው ሲኖዶሳዊ ጉባኤ ምዕመናን በጸሎት እንዲተባበሩ ጥሪ አቀርቡ

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥ መጭውን ሲኖዶሳዊ ጉባኤን ምዕመናን በጸሎት እንዲያስታውሱ ጥሪ አቅርበዋል። ጉባኤውን በማስመልከት ለመላው ካቶሊክ ብጹዓን ጳጳሳት በላኩት መልዕክት፥ በመስከረም 23/2016 ዓ. ም. የሚከፈተውን 16ኛው የሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በጸሎት እንዲያስታውሱ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች፥ ለመላው ካቶሊክ ብጹዓን  ጳጳሳት በላኩት መልዕክት፥ መስከረም 23/2016 ዓ. ለሚጀመረው 16ኛው የሲኖዶስ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዝግጅት ወቅት የሚደረግ ጸሎት አስፈላጊነት ላይ በማትኮር መልዕክት አስተላልፈዋል።

የሲኖዶሱ ጉባኤ በዋናነት በጸሎት እና በመንፈስ ቅዱስ ሥራ ላይ ያተኮረ መንፈሳዊ ዝግጅት መሆኑንም ያስረዱት ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች፥ ተሳትፎን ለማበረታታት እና ለጉባኤው አባላት የጸሎት ድጋፍ ለመጠየቅ በሲኖዶሱ ጠቅላይ ጽሕፈት የተዘጋጀ፥ በተለይም በየእሁዱ በሚቀርቡ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ማብቂያ ላይ የሚደገም የቡራኬ ጸሎት ይፋ መሆኑን አስታውቀዋል።

የካርዲናል ግሬች መልዕክት

ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች፥ “በብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ ለሚገኝይ ውድ ወንድሞች” ባሉት መልዕክታቸው ላይ እንደገለጹት፥ ሲኖዶሱ በዋናነት “የሲኖዶሱ ጉባኤ ተካፋዮችን ብቻ ሳይሆን በጥምቀት የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ የሆኑትን ምእመናን እና እያንዳንዱን ቤተ ክርስቲያን የሚያሳትፍ የጸሎት እና የመደማመጥ ዝግጅት ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ በየአካባቢያቸው በሚገኘው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚቀርበውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶችን እንዲመሩ ያሳሰቡት ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች፥ ጸሎት ብጹዓን ጳጳሳቱ ተሳትፎአቸውን የሚያረጋግቱበት እና ለዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን የሚደረግላትን እንክብካቤን የሚገልጽ መሆኑን አሳስበዋል።

አራት የጸሎት ገጽታዎች

በሲኖዶሱ ዐውድ ውስጥ የሚገኙ አራት የጸሎት ገጽታዎች በመጥቀስ ሃሳባቸውን ያካፈሉት ብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ግሬች፥ የመጀመሪያው ማዳመጥ እንደሆነ ገልጸው፥ ጸሎት የእግዚአብሔርን ቃል እና መንፈስ ቅዱስ የሚለውን በማዳመጥ የሚጀምር እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው፥ የመንፈስ ቅዱስ ድምፅ ለቤተ ክርስቲያን ማስተዋልን እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

ስግደት ከጸሎት ዓይነቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ግሬች፥ “እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ የሚናገረውን እና መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚፈጽመውን ድንቅ ሥራ ጽሞና በተመላበት በመንገድ በስግደት መረዳት አስፈላጊ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ምልጃ ሌላው የጸሎት ዓይነት እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች፥ ምዕመናን የምልጃ ጸሎት እንዲያቀርቡ አደራ ብለው፥ በምልጃ ጸሎታችን ከእኛ ፈቃድ ይልቅ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በማስቀደም፥ ይልቁንም ፈቃዱን እንፈጽም ዘንድ ሕይወትን የሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ልባችንን እንዲያበራልን መለመን እንደሆነ አስረድተዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ግሬች አራተኛውን የጸሎት ዓይነት በተመለከተ፥ ምስጋናን በማቅረብ ብርታትን ስለማግኘት ሲናገሩ፥ የምስጋና ጸሎት እኛ ከራሳችን ወጥተን እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ የሚያደርገውን ለማወቅ እና ወደ ግልጽነት የሚያሸጋግር እውነተኛ መንገድ መሆኑን አስረድተዋል።

የጸሎት አስፈላጊነት

ብፁዕ ካርዲናል ግሬች ምዕመናን በሙሉ የሲኖዶሱ ጉባኤን ማዕከል በማድረግ እሑድ መስከረም 20/2016 ዓ. ም. በሚቀርብ ዓለም አቀፍ ጸሎት፣ ስብከት፣ በቅዱስ ቁርባን ቡራኬ እና ስግደት ላይ እንዲሳተፉ ጋብዘዋል። 

ብጹዕ ካርዲናል ግሬች በመልዕክታቸው ማጠቃለያ ላይ፥ ሲኖዶሳዊው ጉዞን ለመሩት ብጹዓን ጳጳሳት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ አገልግሎታቸውንም በጸሎታቸው እንደሚደግፉት አረጋግጠው፥ የመንፈስ ቅዱስን መሪነት እና ከእግዚአብሔር ቃል የሚገኘውን ደስታ በጸሎታቸው ጠይቀዋል።

ለሁሉ እንዲደርስ የተላከ መልዕክት

ለመለኮታዊ አምልኳቸው ተመሳሳይ ቡራኬን እና ጸሎትን ለምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎችም ጭምር የላኩት ብፁዕ ካርዲናል ግሬች፥  መልዕክታቸው የሲኖዶሱን ጉባኤ መንፈሳዊነት ለማጉላት እና መላውን የእግዚአብሔር ሕዝብ በጸሎት ለማሳተፍ የሚደረገው ሰፊ ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ለሲኖዶሳዊ ጉባኤው ከሚደረጉ ቅድመ ዝግጅቶች መካከል አንዱ፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የጸሎት ጥሪ አውታረ መረብ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ጋር በመተባበር ለሲኖዶሱ ወርሃዊ የጸሎት መርሃ ግብር የሚያገለግል ድረ ገጽ የማዘጋጀት ውጥን፣ ጉባኤው ከመጀመሩ በፊት ማለትም መስከረም 19/2016 ዓ. ም. የጸሎት ሥነ-ሥርዓት እንደሚኖር እና የጉባኤው ተካፋዮችም ከመስከረም 20-22/2016 ዓ. ም. ድረስ ሱባኤን የሚገቡበት መርሃ ግብር መኖሩን፣ የጳጳሳት ሲኖዶስ ጠቅላይ ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ማርዮ ግሬች በመልዕክታቸው ላይ ገልጸዋል።

 

16 September 2023, 16:03