ፈልግ

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፤ በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፤ 

ቅድስት መንበር በዲጂታል ዘመን የሰላም ባሕልን በማሳደግ ላይ እንደምትገኝ ተገለጸ

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት፥ ዲጂታል ቴክኖሎጂ በትምህርት፣ በውይይት እና በሰላም ፍለጋ ላይ ያለውን ተፅእኖ በታማኝነት እንዲገመግሙት አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ፥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነሐሴ 25/2015 ዓ. ም. ባዘጋጀው ከፍተኛ የሰላም ባሕል መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን፥ የሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ንግግር ማዕከላዊ ጭብጥ “በዲጂታል ዘመን ውስጥ የሰላም ባሕልን ማሳደግ” የሚል እንደ ነበር ታውቋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል መድረኩ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ባደረጉት ንግግር፥ የልዑካን ቡድናቸው ‘በዲጂታል ዘመን የሰላምን ባሕል ማጎልበት’ በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን የዘንድሮው ከፍተኛ መድረክ በደስታ መቀበሉን ገልጸው፥ በዲጂታል ዘመን ከሰላም ግንባታ አንፃር የቀረቡትን ውስብስብ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ መንገዶችን እና ያሉ ዕድሎችንም አቅርበዋል። ሁለት ወሳኝ ገጽታዎችን የዳሰሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፥ ንግግራቸውን ዕውቀት በተመላበት በግልጽ እና በጥበብ አቅርበዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በትምህርት ላይ ያላቸው ተጽዕኖ

በቅድሚያ፥ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በትምህርት ውስጥ ባለቸው ወሳኝ ሚና ላይ አጽንዖት የሰጡት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፥ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች በትምህርት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንዳላቸው ተናግረው፥ ሰላምን ያማከሉ እሴቶችን ለማዳበር ያላቸውን አቅም በመገንዘብ፣ በቴክኖሎጂ ላይ ከመጠን በላይ ጥገኛ መሆን፥ ትምህርት የቴክኒክ እውቀትን ለማስተላለፍ ብቻ እንዳይሆን አስጠንቅቋል።

የሰላም ባሕል ስምምነትን ጠቅሰው የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፥ የተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ማለትም ወላጆች፣ መምህራን፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት ተቋማት አካላት እና ሌሎች አካላትም የሰላም ባሕልን በመቅረጽ ረገድ ያላቸውን የጋራ ኃላፊነት አመላክተዋል።

ዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እና ኃላፊነት የሚሰማው አገላለጽ

የሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ንግግር ሁለተኛው ቁልፍ ትኩረት፥ ውይይትን እና ኃላፊነት የተሞላበት አገላለጽን በማስተዋወቅ ረገድ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች የሚጫወቱትን ሚና የተመለከተ ሲሆን፥ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች እርስ በርስ የመገናኘት፣ የመወያየት እና የመደማመጥ ባሕልን በማስፋፋት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ አስረድተዋል።

እነዚህ የፈጠራ ውጤቶች ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በማመቻቸት ያላቸውን ኃይል በመገንዘብ፥ በኃላፊነት የመጠቀም አስፈላጊነት መኖሩንም ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ኅብረተሰቡ ለእውነታው መርህ ቅድሚያ እንዲሰጥ እና የዲጂታል ዘመን የሐሰት መረጃ ዘመን እንዳይሆን በማለት ያስተላለፉትን መልዕክት ጠቅሰዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ፥ “ለቴክኖሎጂ ዕድገት ምስጋና ይግባውና የሰላም ባሕልን እና የተሻለ ዓለምን ማስተዋወቅ የሚቻለው በጋራ ጥቅም ራዕይ፣ በነፃነት ሥነ-ምግባር፣ ኃላፊነት በተሞላበት አሠራር እና በወንድማማችነት ባሕል ነው” ብለው፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥሪ፥ ቴክኖሎጂ በሥነ-ምግባር ሲመራ በጎውን ለማድረግ ኃይል እንዳለው ሁላችንንም ያስታውሰናል ብለዋል።

 

07 September 2023, 14:39