ፈልግ

ቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቫቲካን ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ  

የቅድስት መንበር አስተዳደር ዓመታዊ የፋይናንስ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ

በቫቲካን የቅድስት መንበር አስተዳደር፥ ቤተ ክርስቲያን የምትፈጽማቸውን የተልዕኮ አገልግሎቶችን መሠረት ያደረገ የ2022 ዓ. ም. የፋይናንስ ሪፖርት ይፋ አድርጓል። የአስተዳደሩ ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኑንሲዮ ጋላቲኖ፥ “ቤተ ክርስቲያን በምዕመናን ልግስና ያገኘችውን ሃብት በሃላፊነት በመጠቀም የወንጌል ምስክርነቷን መግለጿ ለተዓማኒነቷ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ ሁላችንም እርግጠኞች ነን" ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ውስጥ የሚገኙ ከፍተኛ ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች  ተግባራትን ለማስኬድ 32.27 ሚሊዮን ዩሮ ውጪ ማድረጉን በቫቲካን የቅድስት መንበር አስተዳደር ሐሙስ ነሐሴ 4/2015 ዓ. ም. ይፋ ባደረገው ዓመታዊ የፋይናንስ ሪፖርት አስታውቋል።

የአስተዳደሩ ፕሬዝደንት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኑንሲዮ ጋላቲኖ፥ ከዓመታዊ ሪፖርቱ ጋር በጻፉት ደብዳቤ ላይ እንደገለጹት፥ “እንደ ሌሎች ተቋማት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ጦርነቶች የሚፈጥሩት አለመረጋጋቶች አስተዳደራቸው ላይ ጫናን ፈጥረዋል” ብለው፥ የፋይናንስ አስተዳደራቸው ጥረቱን እና የአስተዳደር ብቃቱን በማበልጸግ ግልጽነትን እንደሚያሳድግ ታላቁ የምጣኔ ሃብት ሊቅ አንቶኒዮ ጄኖቬሲ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተናገረውን ጠቅሰዋል።

የፋይናንስ ሪፖርቱ የቅድስት መንበር አስተዳደር ቤተ ክርስቲያን ጣሊያን ውስጥ ካላት የሪል እስቴት አስተዳደር ከምታገኘው ገቢ ለመንግሥት የምትከፍለው ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስ መጠን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2022 የግብር ዘመን፥ €6.05 ሚሊዮን እና የጣሊያን ኮርፖሬት ታክስ €2.91 ሚሊዮን እንደሆነ አስታውቋ። በዚህም ረገድ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላንቲኖ፥ “የቁጥሮች ግልጽነት፣ የተገኙ ውጤቶች እና የታዩት አሠራሮች ቢያንስ ከግምት ነፃ የሆኑ እና መሠረተ ቢስ ጥርጣሬዎችን ከሚያስወግዱ መንገዶች መካከል አንዱ እንደሆነ አስረድተው፥ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር ግብርን የመሳሰሉ ፍትሃዊ ግዴታዎች ሌሎች ክፍያዎችን በጊዜ ማጠናቀቅ እንደሆነ አስረድተዋል።

በሌላ በኩልም ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኑንሲዮ ጋላቲኖ፥ ከአንድ ዓመት ጥቂት ከፍ ብሎ “ወንጌልን ስበኩ” በሚል ርዕሥ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ፍራንችስኮስ ይፋ ያደረጉት ሐዋርያዊ ደንብ ለቅድስት መንበር አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ ግልጽ እየሆነ መምጣቱን ገልጸው፥ የአስተዳደራቸው ሃላፊነት ዓላማው ትርፍን መሰብሰብ ሳይሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደገለጹት ሁሉ፥ ቤተ ክርስቲያን በምዕመናን ልግስና ያገኘችውን ሃብት ሃላፊነት ባለው መንግድ በመጠቀም፥ በወንጌል ምስክርነት ላይ ያላትን ተዓማኒነት ማቆየት፣ ማጠናከር እና የወንጌል ተልዕኮ ማገዝ እንደሆነ ገልጸው፥ “ይህም ለሦስተኛ ጊዜ በተከታታይ የቀረበው ዓመታዊ የፋይናንስ ሪፖርት ከሚያረጋግጣቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ ነው” ብለው፥ ዛሬም ቢሆን በቅድስት መንበር አስተዳደር ሙያዊ ብቃት ካላቸው የኢንቨስትመንት ቢሮ ጋር በመተባበር በዚህ ልዩ ወቅት መደበኛ እንቅስቃሴዎችን እንደገና በመጀመር ግልጽነት ላይ የተመሠረተ፣ ተአማኒ እና አስተማማኝ አስተዳደር መኖሩን ገልጸዋል።

አስተዳደራዊ ደኅንነትን በሚመለከት በቅድስት መንበር አስተዳደር የኢንቨስትመንት ፖሊሲ መስፈርቶችን በጥንቃቄ በመመልከት በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ ትርፋማነት መካከል ላይ ያለውን ትክክለኛ ሚዛን በመረዳት አስተዋይ የሆነ የንብረት ድልድልን በመደገፍ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. ምንም እንኳን እርግጠኛ ያልሆነ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ቢኖርም፥ በተወሰነ መልኩ ተጋላጭነቱ 25% አካባቢ እንደ ነበር፥ ነገር ግን የቅድስት መንበር የወደፊት ዕጣ ፈንታ እርግጠኛ ያልሆኑ የፋይናንስ ቁርጠኝነቶችን እና የአስተዳደር ለውጦችን ከአዲሱ ሐዋርያዊ ደንብ ጋር በማቆራኘት ከፍተኛ ጥንቃቄ በታከለበት አካሄድ መሥራት እንደሆነ ተገልጿል።

በዚህ ግልጽነት መንፈስ የፋይናንስ ሪፖርቱ የተገኙ ውጤቶችን እና ያጋጠሙትን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች አጠቃላይ ዕይታ ያቀረበ ሲሆን፥ በተለይም ከኤኮኖሚው አንፃር የ2022 የበጀት ዓመት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በዩክሬን በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት አሉታዊ ቀውሶችን ያስተናገደ እንደ ነበር ታውቋል። በተጨማሪም፥ በመጀመሪያዎቹ ወራት ውስጥ ቀድሞውኑ እንደታየው የዋጋ ግሽበት እና በወጪዎች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ በመታየቱ ምክንያት በቅድስት መንበር አስተዳደር በተለያዩ የእንቅስቃሴ መስኮች እና የሥራ ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል ።

በተለይ የደህንነት አስተዳደር ውጤት እንደ ጎርጎሮአውያኑ በ 2021 ዓ. ም. ከተመዘገበው 19.85 ሚሊዮን ዩሮ አዎንታዊ ውጤት ጋር ሲነፃፀር 6.7 ሚሊዮን ይሮ እንደነበረ ተመልክቷል። በተመሳሳይም የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች ከ 10 ሚሊዮን ዩሮ ወደ 13 ሚሊዮን ዩሮ መጨመሩ ተመልክቷል። ካለው ከፍተኛ የገበያ ዋጋ፣ ደካማ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የድርጅት ትርፍ በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉ እና ከዋጋ ንረት ማሽቆልቆል አንጻር ከ 2021 ጋር ሲነጻጸር የገቢ እና ወጭ መጠንን ጠብቆ ማቆየት አሁንም የማያቋርጥ እና ጥንቃቄ የተሞላበት የመቆጣጠሪያ ፖሊሲን መከተል እንደሚጠይቅ ተመልክቷል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከታኅሳስ 31/2022 ዓ. ም. ጀምሮ በቅድስት መንበር የሚተዳደር የፋይናንስ ኢንቨስትመንት ወደ 1.777 ሚሊዮን ዩሮ የሚጠጋ ሲሆን፥ ይህም ሁለቱንም የንብረት አስተዳደር እና የሦስተኛ ወገን አስተዳደርን ማለትም የቅድስት መንበር አካላትን ወይም ተዛማጅ አካላትን የሚያጠቃልል እንደሆነ ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪም የቅድስት መንበር አስተዳደር ሌሎች ተግባራትን ያሚቆጣጠር ሲሆን፥ ከጠቅላላ የድርጅቱ አሠራር ጋር የተያያዙ ወጪዎችን ጨምሮ ወደ ሮም የሚደረጉ መንፈሳዊ ንግደቶችን የሚያመቻች ተቋምንም እንደሚያስተዳድር ሲታወቅ፥ ከበጀት ጋር ተያይዞ በቀረበው ሪፖርት ላይ ውጤቱን ለማመቻቸት እና የአሰራር ዘዴዎችን ለማሻሻል የተያዘውን የሦስት ዓመት ዕቅድ ሪፖርቱ ዋቢ አድርጎ፥ በተለይም ዕቅዶቹ ከተሳኩ የ 55.4 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ እንደሚገኝ ይገመታል።

 

12 August 2023, 17:01