ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሊዝበን በተከበረው የዓለም ወጣቶች በዓል ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሊዝበን በተከበረው የዓለም ወጣቶች በዓል ላይ  (Vatican Media) ርዕሰ አንቀጽ

“በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ሁሉም ሰው ቦታ አለው!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ፥ “እግዚአብሔር ሁላችንን እንደሚወደን ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም ሁሉን ሰው በፍቅር እንድትቀበል” በማለት ባቀረቡትን ጥሪ ላይ የቫቲካን ዜና አገልግሎት ርዕሠ አንቀጽ አዘጋጅ አቶ አንድሬያ ቶርኔሊ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚገኝ ኤድዋርድ ሰባተኛ መናፈሻ፥  ሐሙስ ሐምሌ 27/2015 ዓ. ም. በተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል በሥፍራው የነበሩ ግማሽ ሚሊዮን ወጣቶች "በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሁሉም ሰው የሚበቃ ቦታ አለ!" የሚለውን ሐረግ እንዲደግሙት አበረታቷቸዋል።

ከመሪዎቻቸው እና ከአስተማሪዎቻቸው ጋር በመሆን ከመላው ዓለም ወደ ፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የተጓዙ ወጣቶችን ቅዱስነታቸው በማበረታታት መንፈሳቸውንም አድሰዋል። "ለሁሉም ሰው የሚሆን በቂ ሥፍራ አለ" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በመልዕክታቸው ላይ የመጀመሪያዎቹን አሥር የሐዋርያዊ መሪነት ዓመታትን በማስታወስ በምህረት አርማ ሥር ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት መጀመራቸን በሚገባ ያሳያል።

ቅዱስነታቸው “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሁሉም ሰው ቦታ አለ” በማለት ደጋግመው የተናገሩትን ሲይብራሩ፥ ሁሉም ሰው አስፈላጊ እንደሆነ እና የማይጠቅም ሰው ፈጽሞ አለመኖሩን ገልጸዋል። “አባት ሆይ! እኔ ኃጢአተኛ ነኝ! ለእኔ ለኃጢአተኛው ባንተ ዘንድ ቦታ አለኝን?” ብለው ለሚጠይቁት በሙሉ “እግዚአብሔር እኛን እንደ ማንነታችን ተቀብሎን ለእያንዳንዳችን  ቦታ ይሰጠናል” በማለት ተናግረዋል።

“እኛ እንድምንፈልገው ወይም ማኅብረተሰባችን ከእኛ እንደሚጠብቀው ሳይሆን እግዚአብሔር እኛን እንደ ማንነታችን ይወደናል” ብለው፥ እርሱ በሕይወታችን ውስጥ መሻሻልን እንድናሳይ፥ ከጉድለቶቻችን ጋር፣ ከውስንነታችን እና ፍላጎቶቻችን ጋር ይወደናል” ብለዋል። እግዚአብሔር አፍቃሪ፣ የሚወደን አባት ስለሆነ በእርሱ እምነት ይኑረን” ብለዋል።

ሁሉም ሰው ሃሳቡን ብቻ በሚሰጥበት እና ማንም ሰው የሌላውን ሃሳብ በማይሰማበት በዚህ ዘመን፣ ብዙዎች ያልሆኑትን ለመምሰል በሚሞክሩበት ዘመን ውስጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሚያስታውሱን የበለጠ ማራኪ እና ለውጥ የሚያስገኝ መልዕክት የለም። እግዚአብሔር እኛን ዘወትር በመውደድ ይቅር ይለናል፤ እጆቹን ዘርግቶ ይቀበለናል፤ ምህረትም ያደርግልናል።

ይህ ግንዛቤ ከሰው አቅም በላይ የሆነ እና ወደ መለኮታዊ ኃይል የሚደርስ አመክንዮን የሚያመለክት ነው። በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ስለ ዘኬዎስ ከተገለጸው ታሪክ እንደምንማረው፥ ዘኬዎስ በኢያሪኮ ነዋሪዎች ዘንድ የማይወደድ ኃጢአተኛው ቀራጭ ነው። ሌሎች ስለ እርሱ በሰጡት አስተያየት እና ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ ለማወቅ ባለው ጉጉት፥ ዘኬዎስ ዛፍ ላይ ወጥቶ፣ በቅጠሎችም በግማሽ ተደብቆ ኢየሱስ እስኪያልፍ ድረስ ይጠባበቅ ነበር።

በሥፍራው የነበሩ ሰዎች አስተያየት ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ ወደ ዘኬዎስ ተመልክቶ በመጀመሪያ ወደደው፣ ቀጥሎም ወደ ዘኬዎስ ቤት ሄደ። የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ለመቀበል ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ የለም። እርሱን ለመከተል ምንም መመሪያ አያስፈልግም። ምንም የመሰናዶ ስልጠና ወይም የመማሪያ ዘዴ የለም።

ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅር እና በምሕረት ተሞልቶ ከአጠገባችን ሲያልፍ መገኘት ብቻ በቂ ነው። በመንገዳችን ላይ የሚገኙ ዕለታዊ እንቅፋቶቻችንን በማስወገድ ለሚያቀርብልን ምስክሮች እውቅናን በመስጠት እርሱ እንዲያቅፈን መፍቀድ ብቻ ያስፈልገናል። ናዝራዊውን ኢየሱስ ክርስቶስን በቤቱ ለማዕድ ለመጋበዝ ዕድል ለነበረው ለዘኬዎስ እንዳደረገው ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ቦታ አላት። የእርሱ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ አስገራሚ እና ነፃ ስጦታ በጸጋ ብቻ የተሰጠ ነው።

የኢየሱስ ክርስቶስ እይታ እና ጥሪ የዘኬዎስን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ለውጦታል። ምክንያቱም ከመቼውም ጊዜ በላይ ስለተወደደ፣ ሕልውናው ውስጥ ያለውን የኃጢአት ሕይወት በጥልቀት መረዳት ችሏል። ቢሆንም መለወጥ ለዘኬዎስ ፍቅርን እና ይቅርታን ለማግኘት ቅድመ ሁኔታ አልነበረም። መለኮታዊ ምሕረት ማግኘቱ ኃጢአቱን እንዲገነዘብ አስችሎታል። መለኮታዊ ምሕረት ማግኘቱ ምስኪን ኃጢአተኛ መሆኑን እንዲያውቅ አድርጎታል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የእግዚአብሔርን ምሕረት በመጓጓት ላይ ለሚገኙ ወጣቶች በድጋሚ ያቀረቡት ግብዣ ዛሬ ለወንጌል ስርጭት ዋና ቁልፍ ነው። እንደ ማንነታችን የሚያቅፈን፣ ስሜታችን አውቆ ምን እንደምንፈል የሚረዳን፣ እርስ በእርስ እንድንፈላለግ፣ እንድንዋደድ እና ይቅር እንድባባል የሚያደርግ ሰው ካለን ሌላ ምን ያስፈልገናል? እንደ ማንነታችን በእግዚአብሔር ዘንድ ለሁላችንም ቦታ እንዳለን እርግጠኛ ከሆንን ሌላ ምን ያስፈልገናል?

 

05 August 2023, 17:21