ፈልግ

የቅድስት መንበር ፍርድ ቤት ችሎት የቅድስት መንበር ፍርድ ቤት ችሎት   (Vatican Media)

የቫቲካን የፍትህ ጽ/ቤት በተከሳሾች ላይ የቅጣት ብይን ጥያቄዎችን አቀረበ

በቫቲካን የፍትህ ጽሕፈት ቤት አባል የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ዲዲ ለንደን ከሚገኝ ሕንጻ ግዥ ጋር በተያያዘ በፍርድ ችሎት በተከሰሱት አሥር ሰዎች ላይ በጠቅላላው የሰባ ሦስት ዓመታት እስራት እና የገንዘብ ቅጣቶች እንዲበየንባቸው ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የፍትህ ጽሕፈት ቤቱ በለንደን የክስ ችሎት በተከሰሱት አሥሩ ተከሳሾች ላይ የሰባ ሦስት ዓመት እስራት እና የተለያዩ ዓይነት የመያዣ እና የገንዘብ ቅጣቶች እንዲበየንባቸው ጠይቋል። ከተከሳሾቹ መካከል አንዱ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል አንጄሎ ቤቹ የተሰጣቸውን ሥልጣንን በአግባብ ባለ መጠቀም የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት የፋይናንስ ኢንቨስትመንቶችን በትክክለኛው መንገድ ባለመምራታቸው በተከሰሱበት ጥፋት 10,329 ዩሮ እና የሰባት ዓመት ከሦስት ወር እስራት እንዲቀጡ በተጨማሪም ከሥራ እንዲታገዱ አቶ አሌሳንድሮ ዲዲ ጠይቀዋል።

ሌሎች ማዕቀቦች

ሌሎች ማዕቀቦች ከተጣሉባቸው መካከል አንዱ እና ሥልጣንን በአግባብ ባለ መጠቀም የተከሰሱት አቡነ ማውሮ ካርሊኖ ከሥራቸው በዘላቂነት በመታገድ ከ8,000 ዩሮ ቅጣት በተጨማሪ የአምስት ዓመት ከአራት ወር እስራት እንዲበየንባቸው አቶ አሌሳንድሮ ጠይቀዋል።

ገንዘብ በማጭበርበር፣ የሥራ ሃላፊነታቸውን አላግባብ በመጠቀም፣ በሙስና፣ በምዝበራ፣ የሃሰት ሠነዶችን በማቅረብ ቅድስት መንበርን ለመጉዳት በማሰባቸው ክስ የተመሠረተባቸው አቶ ኤንሪኮ ክራሶ በዘላቂነት ከሥራቸው ታግደው የ18,000 ዩሮ ቅጣት እና ዘጠኝ ዓመት ከዘጠኝ ወር እስራት እንዲበየንባቸው ተጠይቋል።

የሥራ ሃላፊነታቸውን እና ስልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም የመሥሪያ ቤታቸውን ደንብ በመጣስ ምክንያት ክስ የተመሠረተባቸው ሌላኛው ተከሳሽ አቶ ቶማሶ ዲ ሩዛ፥ አራት ዓመት ከሦስት ወር እስራት በተጨማሪ ከሥራቸው በጊዜያዊነት ታግደው የ 9,600 ዩሮ የገንዘብ ቅጣት እንዲበየንባቸው ተጠይቋል።

ቼቺሊያ ማሮኛ በማጭበርበር ወንጅል የአራት ዓመት ከስምንት ወር እስራት እና ከሥራቸው በዘላቂነት እንዲታገዱ እና የ10,329 ዩሮ የገንዘብ ቅጣት እንዲበየንባቸው ተጠይቋል።

በገንዘብ ማጭበርበር፣ የሥራ ሃላፊነታቨውን በአግባብ ባለ መጠቀም እና በሙስና ወንጀል የተከሰሱት አቶ ራፋኤሌ ሚንቾኔ የ 11 ዓመት ከአምስት ወር እስራት፣ በዘላቂነት ከሥራቸው ታግደው የ15,450 ዩሮ የገንዘብ ቅጣት እንዲበየንባቸው ተጠይቋል።

አቶ ኒኮላ ስኩይላቼ ገንዘብን በማጭበርበር ወንጀል የስድስት ዓመት እስራት እና ከሙያዊ እንቅስቃሴያቸው በመታገድ የ12,500 ዩሮ የገንዘብ ቅጣት እንዲበየንባቸው ተጠይቋል።

ሌላኛው ተከሳሽ አቶ ፋብሪዚዮ ቲራባሲ ገንዘብ በማጭበርበር፣ ሥልጣንን በአግባብ ባለ መጠቀም እና በሙስና ወንጀል 13 ዓመት ከሦስት ወር እስር በዘላቂነት ከሥራቸው ታግደው 18,750 ዩሮ የገንዘብ ቅጣት እንዲበየንባቸው ተጠይቋል።

ጃንሉዊጂ ቶርዚ የተባሉት ተከሳሽ ገንዘብ በማጭበርበር፣ በሙስና እና በዝርፊያ ወንጀል የሰባት ዓመት ከስድስት ወር እስራት እና ለጊዜው ከሥራ ታግደው የ 9,000 ዩሮ የገንዘብ ቅጣት እንዲበየንባቸው ተጠይቋል።

የሥራ ሃላፊነታቸውን አላግባብ ተጠቅመዋል የትባሉት አቶ ሬኔ ብሩልሃርት የሦስት ዓመት ከስምንት ወር እስራት እና ከሥራቸው በጊዜያዊነት በመታገድ የ 10,239 ዩሮ የገንዘብ ቅጣት እንዲበየንባቸው የተጠየቀ ሲሆን፥ በችሎቱ ላይ  ከተከሳሾቹ መካከል አንዳቸውም እንዳልተገኙ ተመልክቷል። በብዙ ሚሊዮን በሚቆጠር ዩሮ መጥፋት የብይን ጥያቄ ከቀረበባቸው ኩባንያዎች መካከል፥ “Logsic Humanitarne Dejavnosti” ፣ “Prestige Family Office” ፣ Capital Investment” እና “HP Finance” የሚባሉት ይገኙበታል።

የግምገማ መስፈርቶች

በቫቲካን የፍትህ ጽሕፈት ቤት አባል የሆኑት አቶ አሌሳንድሮ ዲዲ የብይን ጥያቄዎችን ለመመልከት የተጠቀሙበትን መስፈርት ያብራሩ ሲሆን፥ በተለይም “ዛናርዴሊ” እየተባለ የሚጠራው እና በቫቲካን የፀደቀው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የእገዳ አያያዝ ዘዴ ትክክለኛነት እንደሌለው ገልጸው፥ ነገር ግን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 13/2023 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የታወጀውን እና “አበረታች መርሕ” በመባል በቫቲካን ግዛት መሠረታዊ ሕግ አንቀጽ 21 ላይ በመመርኮዝ ተመርኩዞ ሕጉን በሥራ ላይ ለማዋል ዳኛው ፍትሃዊ መርህ ተከትሎ ፍትህን ወደነበረበት ለመመለስ እና በተዋዋይ ወገኖች መካከል ዕርቅ እንዲፈጠር ያደርጋል። በተጨማሪም በወንጀል ጉዳዮች ላይ ዳኛው ቅጣቱን የሚወስነው ጥፋተኛው በሠራው ወንጀል ልክ ከወንጀሉ በሚመለስበት እና የተጣሰው የሕጋዊ ሥርዓት ወደ ነበረበት በሚመለስበት መሠረት እንደሆነ ታውቋል።

የካርዲናል አንጄሎ ቤቹ የመከላከያ ቃል

ከችሎቱ በኋላ ሁለቱ ዳኞች አቶ ማሪያ ኮንቼታ ማርዞ እና አቶ ፋቢዮ ቪሊዮኔ ከብፁዕ ካርዲናል አንጀሎ ቤቹ ጠበቆች ጋር ሆነው ባወጡት የጋራ መግለጫ፥ “በቫቲካን የፍትህ ጽሕፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት የአቶ አሌሳንድሮ ዲዲ የብይን ጥያቄዎች የካርዲናሉን ፍጹም ንፁህነት ያረጋገጠውን የፍርድ ሂደት ውጤት ያላገናዘበ ነው” በማለት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ከለንደን ቤተመንግስት ጋር ለተያያዘው ቀዶ ጥገና እና ለማንኛውም ሌሎች ክፍያዎች። ዳኞቹ እና ጠበቆቹ አክለውም፥ “የአቶ አሌሳንድሮ ዲዲ የብይን ጥያቄን በተመለከተ የአንድ ቀን ቅጣት ብይን እንኳን ፍትሃዊ ሊሆን አይችልም” ብለዋል።

 

27 July 2023, 14:34