ፈልግ

ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የሚሰጥ ምጽዋት ለአለም አቀፍ ቤተክርስቲያን እና ለጳጳሱ ተልዕኮ ድጋፍ ያደርጋል ተባለ!

ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የሚሰጠው አመታዊ ምጽዋዕት ከጥንት ጀምሮ ለጳጳሱ ግምጃ ቤት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የካቶሊክ ቤተክርቲያን ምዕመናን በፈቃደኝነት የሚለግሱት አመታዊ የገንዘብ ድጋፍ ነው። ይህ ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የሚደረገው አመታዊ ድጋፍ ለአለም አቀፍ ቤተክርስቲያን እና ለጳጳሱ ተልዕኮ ልግስና ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ባለፈው አመት ማለትም እ.አ.አ 2022 ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የተደርገው ድጋፍ በተመለከተ የሒሳብ ኦዲት ተደርጎ በአመታዊው ይፋ መግለጫ ሪፖርቱን አቅርቧል፣ የ107 ሚሊዮን ዩሮ ካፒታል መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን  95.5 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ በማድረግ፣ ይህም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ተልዕኮን ለማስቀጠል የዋለ ሲሆን ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የሚደርገው አመታዊ የገንዘብ ድጋፍ  ምእመናን ለቅዱስ አባታችን ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ የጴጥሮስ ተተኪ ለሆኑት ሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን ፍላጎቶች እና እጅግ የተቸገሩትን ለመታደግ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት የሚደርግ ጥረት አካል ነው።

የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን በቫቲካን

እ.ኤ.አ. በ 2022 ዓ.ም ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ምእመናን ለቅዱስ አባታችን ያቀረቡት የገንዘብ ድጋፍ - አጠቃላይ ገቢ 107 ሚሊዮን ዩሮ (ሁሉም መጠኖች በዩሮ የተዘገበ ነው) መሆኑን የኦዲት መግለጫ ሪፖርት የገለጸ ሲሆን ከአተቃላይ ገቢው ላይ  95.5 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ተደርጎ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ ሐዋርያዊ ተልዕኮዎችን በገንዘብ ለመደገፍ እንደ ተቻለ ተግልጿል ።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የካቶሊክ ምእመናን ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የገንዘብ አስተዋጾ ማድረጋቸው የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ አመታዊ በዓል ባለፈው ሰኔ 23/2015 ዓ.ም በተከበረበት ክብረ በዓል ላይ በተካሄደው ዓመታዊ ስብስብ ሪፖርቱ ይፋ እንደ ሆነ ተገልጿል።

ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የሚሰጠው የምጽዋዕት ልገሳ ከተለያዩ ሀገረ ስብከቶች፣ ከግል ለጋሾች፣ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እና መሠረተ ልማቶች የተገኙ ናቸው።

ከሀገረ ስብከቶች የተገኘው ዕርዳታ 27.4 ሚሊዮን ዩሮ (63%)፣ ከተለያዩ ፋውንዴሽን 12.6 ሚሊዮን ዩሮ (29%) ደርሰዋል። ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በ11 ሚሊዮን ዩሮ (25.3%)፣ ኮሪያ (8%)፣ ጣሊያን (6.7%)፣ ብራዚል (3.4%) እና ጀርመን (3%) በመከተል ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረከቱ ሀገራት ናቸው።

ከልገሳ በተጨማሪ የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር በፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ገቢ አስገኝቷል፣ ይህም ለፈንዱ ከተመደቡት የሪል እስቴት ንብረቶች ሽያጭ ከፍተኛ ካፒታልን ጨምሮ ማለት ነው።

ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ድጋፍ እና የበጎ አድራጎት ተነሳሽነት

እ.ኤ.አ. በ 2022 ዓ.ም ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ከዓለም ዙሪያ የተደረገው 107 ሚልዮን ዩሮ ድጋፍ እንደ ተደረገ ቀድም ሲል መግለጻችን የሚታወስ ሲሆን እነዚህ መዋጮዎች የቅድስት መንበር የተለያዩ አገልግሎት መስጫ የአስተዳደር ተቋማት አካላትን እና ተልዕኮዋቸውን ተግባራትን መደገፍ እና “የተቸገሩትን ለመርዳት የበጎ አድራጎት ሥራዎችን” በማድረግ ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎችን አገልግሏል።

ከተሰጡት አጠቃላይ መዋጮ ውስጥ 77.6 ሚሊዮን ዩሮ የብፁዓን ጳጳሳት ሐዋሪያዊ ተልእኮ ለማስፈጸም የቅድስት መንበር የሚያስተዋውቁ ተግባራትን ለማገዝ የተከፋፈለ ሲሆን 16.2 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ ለአቅመ ደካሞች ቀጥተኛ የዕርዳታ ፕሮጀክቶች መዋሉ ታውቋል።

እ.ኤ.አ. በ2022 ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የተሰጠው ምጽዋዕት የተደገፈው ቀጥተኛ የእርዳታ ፕሮጄክቶች ለተቸገሩ ሰዎች እና ቤተሰቦች ፣ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ፣ ሀገረ ስብከቶች ፣ አድባራት ፣ የሃይማኖት ተቋማት እና በተፈጥሮ አደጋዎች ወይም ጦርነቶች የተጎዱ ሰዎችን ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች ድጋፍ አድርጓል።

የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት።

ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት በኩል ለእነዚህ ፕሮጀክቶች 36 ሚሊዮን ዩሮ የሰጡ ሲሆን 16.2 ሚሊዮን ዩሮ ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ከተሰጠው ምጽዋዕት የተደገፈ ነው።

ፕሮጀክቶቹ ለ72 የተለያዩ ሀገራት የተከፋፈለ ሲሆን፥ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ከተመደበው የገንዘብ መጠን አንጻር የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛውን ድርሻ (34%) አግኝተዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ምጽዋዕት የገንዘብ ድጋፍ የተደረገላቸው ፕሮጀክቶች በማህበራዊ ፕሮጀክቶች፣ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ለወንጌል አገልግሎት ድጋፍ እና በአዲስ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማስፋት እና ለማስቀተል ተከፋፍለዋል።

የእነዚህ ፕሮጀክቶች ምሳሌዎች በዩክሬን ውስጥ በጦርነት ለተጎዱ ህዝቦች ድጋፍ፣ በጎርፍ ለተጎዱ ህዝቦች እርዳታ፣ የጤና አጠባበቅ ተነሳሽነት፣ የትምህርት ፕሮጀክቶች እና የአብያተ ክርስቲያናት እና ሕንፃዎች ግንባታ እና እድሳት ያካትታሉ።

የጳጳሱን ሐዋርያዊ ተልዕኮ ማስተዋወቅ

ምእመናን ለቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ያበረከቱት አስተዋጾ የቅዱስ አባታችንን ሐዋርያዊ ተልእኮ የሚደግፍ ሲሆን ይህም ወንጌልን መስበክ፣ የሰው ልጅ ልማትን ማስተዋወቅ፣ ካህናትን ማሠልጠን፣ ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን ሰላምን ማስፈን እና በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን ማጎልበት ይገኙበታል።

እ.ኤ.አ. በ 2022 ዓ.ም የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ምጽዋዕት ለ 70 ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች እና በ “ሐዋሪያዊ ተልእኮ ቡድን” ስር ለተሰባሰቡ አካላት 77.6 ሚሊዮን ዩሮ አበርክቷል ፣ በዚህም የእነዚህን አካላት አጠቃላይ ወጪ 20% ይሸፍናል።

እነዚህ አካላት በችግር ውስጥ ያሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን መደገፍ፣ የወንጌል ስርጭት፣ የመልእክት ስርጭት፣ የበጎ አድራጎት አገልግሎት፣ ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ለምዕመናን እና ሌሎችንም ጨምሮ ለተለያዩ ዓላማዎች ያገለግላሉ።

ማጽናኛ ለመስጠት ወደ ሌሎች መቅረብ

የ2022 ዓ.ም የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር የተደረገው አመታዊ ምጽዋዕት ይፋ ማድረጊያ አመታዊ ሪፖርት እ.አ.አ በጥቅምት 29/2014 በጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ባደረጉበት ወቅት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተናገሩት በሚከተለው ጥቅስ ተጠናቀቀ።

“እኛ ሁላችን ቤተ ክርስቲያን ነን! ጌታ ኢየሱስን የሚከተሉ ሁሉ እና በስሙ ወደ ታናናሾች እና ወደ በመከራ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የሚቀርቡ ሁሉ ትንሽ እፎይታን ፣ መጽናናትን እና ሰላምን ለመስጠት የሚችሉ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው”።

03 July 2023, 11:32