ፈልግ

የሊዝበን ከተማ ረዳት ጳጳስ እና የዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀን ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ብጹዕ አቡነ አጉያር የሊዝበን ከተማ ረዳት ጳጳስ እና የዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀን ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ብጹዕ አቡነ አጉያር 

ብጹዕ አቡነ አግያር የዩክሬይን ወጣቶች በድፍረት እና በደስታ መሞላታቸውን ገለጹ

በፖርቱጋል የሊዝበን ከተማ ረዳት ጳጳስ እና የዓለም አቀፍ ወጣቶች ቀን ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ብጹዕ አቡነ አሜሪኮ አጉያር በሐምሌ ወር ማለቂያ ላይ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል ላይ መገኘት የማይችሉ የዩክሬይን ወጣቶችን ጎብኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ለካርዲናልነት ማዕረግ ያጯቸው ብጹዕ አቡነ አሜሪኮ አግያር በዩክሬይን ያደረጉትን ጉብኝት ፈጽመው ሐምሌ 11/2015 ዓ. ም. ወደ ሊዝበን ተመልሰዋል። በጦርነት በተመሰቃቀለች ዩክሬይን ውስጥ ቡቻ እና ኢርፒን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞችን የጎበኙት አቡነ አግያር በዛርቫኒሺያ እና በቤርዲቺቭ ግዛቶች ወደሚገኙ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደሶች ንግደት በማድረግ ላይ ከነበሩ ወጣቶች ጋር ተገናኝተዋል።

በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ መገኘት ለማይችሉት የዩክሬይን ወጣቶች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ያካፈሉት አቡነ አግያር፥ በጉብኝታቸው ወቅት ከወጣቶች ጋር ያደረጓቸው ውይይቶች ጥልቅ እና ስሜታዊ እንደ ነበሩ አስረድተው፥ ከወጣቶቹ ድፍረትን፣ ከማይናወጥ እምነታቸው ምስክርነትን እና ተስፋን ቀስመው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

የአቡነ አጉያር የዩክሬይን ጉብኝት

አቡነ አሜሪኮ አግያር ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር በነበራቸው ቆይታ በዩክሬይን ጉብኝታቸው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ድጋፍ ለወጣቶች አካፍለው መመላሰቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ ቀደም ባቀረቡት ግብዣ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ በአካል መገኘት የማይችሉትን ጨምሮ ሁሉም ወጣቶች እንዲሳተፉት ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ቀደም ሲል አንዳንድ ጥርጣሬዎች ቢኖራቸውም በኋላ ላይ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ቃል በመቀበል በአዎንታዊ ምላሽ የሰጡት አቡነ አግያር፥ የዩክሬን ተልዕኮአቸውን ለመራው እግዚአብሔር ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በጉብኝታቸው ወቅት በዩክሬን ሕዝብ ስቃይ እና ችግር መካከል ኢየሱስ ክርስቶስን በመመልከት በደስታ መሞላታቸውን የገለጹት አቡነ አግያር፥ እግዚአብሔርን ከልባችን ውስጥ ማስወገድ ወደ ጭካኔ፣ ወደ ክፋት፣ ወደ ውሸት፣ ወደ ሞት፣ ወደ ዓመፅ እና ወደ ጦርነት እንደሚመራ ተናግረው፥ ስለ ሕያው እግዚአብሔር የመመስከር አስፈላጊነትን ተናግረዋል።

“ወጣቶች ህልማቸውን ማቋረጥ የለባቸውም”

ከወጣት ዩክሬናውያን ጋር ያደረጓቸውን ስብሰባዎች በማስመልከት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቡነ አግያር፥ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በመጥቀስ “በእናት ልብ ውስጥ የዩክሬይን ወጣቶችን ማግኘት ልዩ እና አስደሳች፥ ወጣቶቹም የሚወዳቸው መኖሩን እና እንክብካቤም እንደሚደረግላቸው መገንዘባቸውን መመልከት መልካም ተሞክሮ ነው” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶች በፈታኝ የጦርነት ወቅትም ሕልማቸውን እንዳያቋርጡ ብርታት መስጠታቸውን አቡነ አግያር አስታውሰዋል። “በወጣት ዩክሬናውያን ዓይን እና ልብ ውስጥ ድፍረት እና ደስታ መኖሩን ተመልክቻለሁ” ያሉት አቡነ አግያር፥ በንቃት ለዩክሬይን ሰላም ፍለጋ ዝግጁዎች መሆናቸውን በተጨባጭ አሳይተዋል ብለዋል።

የዩክሬይንን ጦርነት በፌስቲቫሉ ላይ ማስታወስ

አቡነ አግያር በመጨረሻም በሊዝበን የሚከበረውን የዓለም ወጣቶች ቀን በማስመልከት እንደተናገሩት፥ በጦርነቱ የተጎዱትን ወጣት ዩክሬናውያን ችግሮች ለመረዳት እና ለመፍታት እየተካሄደ ያለውን ጥረት ጠቅሰው፥ “የፌስቲቫሉ ግብ ተጨማሪ ሕመሞችን እና ውጥረቶችን ማስከተል ሳይሆን ጊዜ እና ጸሎት የሚያመጡትን የሰላም ስጦታ ተስፋ ማድረግ ነው” ብለዋል።

በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለሰላም እንደሚጸለይ የገለጹት አቡነ አግያር፥ የዩክሬይን እና በጦርነት የተጎዱ የሌሎች አካባቢዎች ወጣቶች በሊዝበን መገኘት የፌስቲቫሉ ዋና ትኩረት እንደሆን አፅንዖት ሰጥተዋል።

20 July 2023, 15:52