ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የቪየትናም ፕሬዝዳንት አቶ ቮ ቫን ቱንግን በቫቲካን ሲቀበሉ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የቪየትናም ፕሬዝዳንት አቶ ቮ ቫን ቱንግን በቫቲካን ሲቀበሉ   (ANSA)

ካርዲናል ፓሮሊን፥ የቅድስት መንበር እና የቪየትናም ስምምነት አዲስ ጅምር እንደሚያመላክት ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ቅድስት መንበር እና ቪዬትናም የደረሱት ስምምነት በሁለቱ አገራት መካከል አዲስ ጅምር መኖሩን እንደሚያመላክት ገለጹ። ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በቃለ ምልልሳቸው ወቅት በቪየትናም የጳጳሳዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤት መከፈትን በማስመልከት አስተያየት የሰጡት ሲሆን፥ ሁለቱም አገራት በመከባበር እና በመተማመ መንፈስ አብረው ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፥ ቪየትናም እና ቅድስት መንበር በቪየትናም ውስጥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንደራሴ ጽሕፈት ቤትን ለመክፈት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አረጋግጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕነታቸው ከቫቲካን መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቆይታ ሁለቱን አገራት ወደ ስምምነት እንዲደርሱ ባደረጉ የተለያዩ ደረጃዎች ላይ ተመስጠው በሰጡት ሁለት አተያየቶች መካከል የመጀመሪያው፥ “የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛ የተጠቀሙበት እና ‘እርስ በርስ ለመከባበር መተዋወቅ ያስፈልጋል’ የሚለው ሲሆን ሁለተኛው እና ሌላኛው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የቀረበው፥ 'ሂደቶችን መጀመር እና ቦታን አለመያዝ' የሚል እንደሆነ ገልጸዋል።

የንግግር መንገዶች

"ከቪየትናም ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት የተጀመረው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1989 ዓ. ም. መሆኑን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በወቅቱ የፍትህ እና የሰላም ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የነበሩት ብፁዕ ካርዲናል ሮጀር ኢቼጋራይ በቪየትናም ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ በቻሉበት ጊዜ እንደ ነበር ገልጸዋል። የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ፍላጎት የቤተ ክርስቲያኗ የዕለት ተዕለት አስተምህሮ እና ምስክርነት ባህሪ በሆነው በፍትህ እና በሰላም መሪ ሃሳቦች የውይይት መንገዶችን መክፈት እንደ ነበር አስረድተዋል።

በመቀጠልም ቅድስት መንበር ዓመታዊ ጉብኝቶችን በመጀመር፥ ከፊሉ ከመንግሥት ባለ ሥልጣናት ጋር ለመገናኘት እና ከፊሉ ደግሞ ከሀገረ ስብከቱ ማኅበረሰቦች ጋር ለመገናኘት እንደ ነበር አስታውሰው፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታህሳስ 2009 ዓ. ም. የቪየትናም ፕሬዚደንት ንጉየን ሚን ትሪት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ጋር መገናኘታቸውን አስታውሰዋል።

"የጋራ መከባበር"

ይህ ጥረት ቀጥሎ ኑሮአቸውን በሲንጋፖር ያደረጉትን ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሊዮፖልዶ ጂሬሊን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥር 13/2011 ዓ. ም. ተወካይ አድርጎ ለመሾም መንገድ የከፈተውን የቪየትናም እና የቅድስት መንበር የጋራ ተግባር ቡድን እንዲቋቋም ማድረጉን ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን አስታውሰዋል። በቅድስት መንበር እና በቪየትናም መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የጋራ መከባበር እና ወደፊት ለመራመድ ያለው ፈቃደኛነት አስፈላጊ እሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

“የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ሁልጊዜም በሂደቱ ውስጥ የሚሳተፍ እና የራሱን አስተያየት እና ግምገማ ያቀርብ እንደነበር ልብ ሊባል ይገባል” ሲሉ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ጨምረው ገልጸዋል። “ከዚያም የመጨረሻውን ውጤት ወዲያው ለማግኘት ሳይሆን የሃይማኖት ነፃነት መርህን ከአካባቢው ሕጎችና ልማዶች ጋር ማስማማት ደረጃ በደረጃ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የሰማይ እና የምድር ዜጎች

አዝጋሚ ሽምግልናው ወደ እርስ በርስ ግንኙነት የመራ መሆኑን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ጳጳሳዊ እንደራሴ ጽሕፈት ቤትን ለመክፈት ያለመው የመጨረሻ ስምምነቱ ጳጳሳዊ መኖሪያ ቤት ተወካይ ከቪየትናም ቤተ ክርስቲያን እና ከአገሪቱ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመስማማት ሐዋርያዊ አገልግሎቶችን ለማከናወን ቅድመ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት በተጨማሪ በቪየትናም ውስጥ ያተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ውክልናዎችን ቋሚ ለማድረግ ማገዙን አስረድተዋል።

ወንጌልን በተግባር በመኖር መርህ ላይ አፅንዖት የሰጡት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን “ይህም እሴት በ2ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ክርስቲያኖች በተመሳሳይ ጊዜ የሰማይ እና የምድር ዜጎች መሆናቸውን የሚያሳዩበት ነው" ብለዋል። የሁለቱ አገራት ልኡካን በውይይታቸው የቪየትናም ቤተ ክርስቲያን ሕይወት ከግምት ውስጥ በማስገባት የእምነት እና የሃይማኖት ነፃነን ያከበረ እንደነበር ገልጸዋል።

ግንኙነቶችን ማሻሻል

በቪየትናም የጳጳሳዊ መኖሪያ ቤት ተወካይን እንደ ተጨባጭ የመገናኛ ድልድይ እንደሆነ የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ይህም በቪየትናም እና በቅድስት መንበር መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ለማሻሻል የግድ እንደሆነ እና በአገሪቱ ቤተ ክርስቲያን በሚከበሩ በዓላት ላይ በመሳተፍ ግንኙነቶችን ሊያጠናክር እንደሚቻል አስረድተዋል። የጳጳሳዊ መኖሪያ ቤት ተወካይ ልክ እንደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እንደራሴ በቅድስት መንበር እና በቪየትናም መንግሥት መካከል ያለውን የወዳጅነት ግንኙነት የማጠናከር እና ከዲፕሎማቶች ጋር የግል ስብሰባዎችን የማካሄድ ዕድል ያለው መሆኑን ተናግረው፥ ይህ ሁሉ የሚሆነው የሀገሪቱን ሕግ በማክበር እና በመተማመን መንፈስ፥ እስከ አሁን ባለው መልካም የሁለትዮሽ ግንኙነት መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስታውቀዋል።

አዲስ ጅማሬ

በቪየትናም እና በቅድስት መንበር መካከል ስለሚኖረው የወደፊት ግንኙነት የተናገሩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ “በቪየትናም ሕዝብ ላይ ሁሌም አዎንታዊ ስሜት እንዲኖረኝ ያደረገው ምናልባትም በልጅነት ዕድሜዬ በትውልድ አገር ጣሊያን ውስጥ ያሳዩት የትኅትና እና የታታሪነት ባህሪ ነው” በማለት ገልጸዋል። ለቪየትናማውያን የሥራ ልምድ አፅንዖትን የሰጡት ብጹዕ ካርዲናል ፔየትሮ ፓሮሊን፥ በጥልቅ የሥራ ችሎታቸው፣ በጉልበት ሥራ ብቻ ሳይሆን በሚያከናውኑት ሥራ ሁሉ ቁርጠኝነት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

"መጭው ጊዜ ወደ ሌላ ግብ ለመድረስ የሚጣደፉበት ሳይሆን እርስ በርስ ለመተጋገዝ ፈቃደኛ የሆኑት ሁሉ የሚፈልጉት መልካም ነገር ለማግኘት አብረን ወደሚጓዙበት መንገድ ይጋብዘናል" ብለዋል።"በቅድስት መንበር እና በቪየትናም መካከል የተደረሰው ስምምነት የሚያመለክተው የመጨረሻውን መስመርን ብቻ እንዳልሆነ የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ነገር ግን አዲስ ጅምር፣ እርስ በርስ የመከባበር እና የመተማመን ምልክት ነው" በማለት ገልጸዋል።

 

29 July 2023, 15:27