ፈልግ

ቁርኣንን በማቃጠል ምክንያት በባግዳድ የተነሳው ተቃውሞ ቁርኣንን በማቃጠል ምክንያት በባግዳድ የተነሳው ተቃውሞ 

ቅድስት መንበር በንዋየ ቅዱሳት ላይ የሚፈጸም ንቀትን በጥብቅ ማውገዟ ተገለጸ

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ተወካይ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዴቪድ ፑዘር በ53ኛው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ በሰጡት መግለጫ፥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሌላውን ለመናቅ መቼም ቢሆን ምክንያት መሆን የለበትም ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት መንበር በሃይማኖታዊ ንዋያተ ቅዱሳት፣ ምልክቶች እና የአምልኮ ሥፍራዎች ላይ የሚፈጸም ርኩሰት፣ ውድመት ወይም ንቀት በጽኑ አውግዛ፥ እነዚህ ድርጊቶች ውድ የሆነውን ሃሳብ በነጻነት የመግለጽ ስጦታን አላግባብ መጠቀም መሆኑን ገልጻ፥ በሕዝቦች መካከል ጥላቻን፣ አለመቻቻልን እና ከፍተኛ ቅራኔን እንደሚፈጥሩ ገልጻለች።

ጄኔቫ በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት ጽሕፈት ቤት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የቅድስት መንበር ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዴቪድ ፑዘር በድርጅቱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 53ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፥ “ሆን ብሎ ሃይማኖታዊ እምነቶችን፣ ወጎችን ወይም ንዋያተ ቅድሳትን ማንቋሸሽ የአማኙን ሰብዓዊ ክብር ማጥቃት ነው” በማለት ገልጸዋል።

ጉባኤው በአንዳንድ የአውሮፓ እና ሌሎች አገራት ውስጥ በቁርኣን ላይ በተደጋጋሚ በታየው የማንቋሸሽ ተግባር ላይ የተወያየ ሲሆን፥ አባል አገራቱ ሃይማኖትን መሠረት ባደረጉ ባላንጣነት ላይ ክስ እንዲቀርብ የሚጠይቅ ውሳኔ አስተላልፏል። ሰኔ 21/2015 ዓ. ም. በስዊድን መዲና ስቶክሆልም የታየውን ክስተት የጠቀሰው ሰንዱ፥ አንድ ሰው ከመስጊድ ውጭ የእስልምና እምነት ቅዱስ መጽሐፍ የሆነውን የቁርዓን ገፆችን ሲያቃጠል መታየቱ አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ ከመላው ዓለም ውግዘትን ማነሳሳቱን ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግ መሠረት ወንጀለኞቹ በሕግ እንዲጠየቁ ይገባል ብሏል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ 'አል-ኢትሃድ' ከተሰኘ የአረብ ኢሚሬቶች ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በሙስሊሞች የኢድ አል አድሃ በዓል መጀመሪያ ቀን ቁርዓን ሲናቅ መታየቱ አስደንጋጭ እና አስጨናቂ ተግባር ነበር ማለታቸውን ብፁዕ አቡነ ዴቪድ ፑዘር በንግግራቸው ወቅት አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰኔ 26/2015 ዓ. ም. ታትሞ በወጣው 'አል-ኢትሃድ' ዕለታዊ ጋዜጣ በኩል በሰጡት አስተያየት በተፈጸመው ድርጊት ማዘናቸውን ገልጸው፥ "በምዕመናን ዘንድ የተቀደሰ ተብሎ የሚታሰብ ማንኛውም መጽሐፍ ለአማኞች ሲባል ክብር ሊሰጠው ይገባል” ብለው፥ “ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ሌላውን ለመናቅ በፍፁም ምክንያት ሊሆን እንደማይገባ እና ይህን መፍቀድ ውድቅ ሊደረግ ይገባል” ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፥ "እምነት ያላቸው ሰዎች የሰውን ልጅ የሚያስከብር፣ ሰብዓዊ መብቶችን የሚያስጠብቅ እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎለብት ዓለም በመገንባት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ" ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የቅድስት መንበር ቋሚ መልዕክተኛ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዴቪድ ፑዘር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን መልዕክት በማስታወስ በደመደሙት ንግግራቸው፥ “ዛሬ የጦር መሣሪያ አምራቾችን እና ግጭት ቀስቃሾችን ሳይሆን ሰላም ፈጣሪዎችን፣ እሳት የሚጭሩትን ሳይሆን የእሳት አደጋ የሚከላከሉትን፣ በሕዝብ እና በንብረት ላይ ጥፋት የሚያደርሱትን ሳይሆን እርቅ የሚያመጡትን እንፈልጋለን” ብለዋል።

ሐምሌ 5/2015 ዓ. ም.  በ 28 ድምጽ ድጋፍ እና በ 12 ድምጽ ተቃውሞ የጸደቀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ውሳኔ፥ አባል ሀገራቱ ብሔራዊ ሕጎቻቸውን፣ ፖሊሲዎቻቸውን እና የሕግ ማስፈጸሚያ ማዕቀፎቻቸውን እንዲመረምሩ ጠይቆ፥ ሃይማኖታዊ የጥላቻ ድርጊቶችን ለመከላከል እና ሕግ ፊት ለማቅረብ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ክፍተቶችን እንዲለዩ እና እንዲያስተካክሉ አሳስቧል።

የመንግሥታቱ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ውሳኔ በእስላማዊ የአንድነት ድርጅት ድጋፍ ያገኘ ቢሆንም፥ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን መሠረት ያደረጉ የዩናይትድ ስቴትስ፣ የፈረንሳይ እና የጀርመን መንግሥታት ጨምሮ በሌሎች የምዕራባውያን አገራት ልዑካን በኩል ተቃውሞ እንዳጋጠመው ተመልክቷል።

15 July 2023, 16:30