ፈልግ

ሊቀ ጳጳሳ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ ሊቀ ጳጳሳ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ 

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ፥ “የካርዲናልነት ማዕረግ ሰማዕትነትን የሚጠይቅ ከፍተኛ ሃላፊነት ነው!”

በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሊቀ ጳጳሳ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ ለካርዲናልነት ማዕረግ መታጨታቸውን አስመልክተው ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ለካርዲናልነት ማዕረግ ካጯቸው 21 የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መካከል አንዱ የሆኑት አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ ሹመቱ የያዘውን የሰማዕትነት ገድልንም አስታውሰዋል። በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በማድረግ ላይ ባሉት የሰላም ተልዕኮ በማሰላሰል አስተያየታቸውን የሰጡት ሊቀ ጳጳስ ጉጄሮቲ በአገሪቱ ውስጥ የቅድስት መንበር እንደራሴ ሆነው የሠሩበት አጋጣሚ በማስታወስ ክልሉ ውስብስብ ታሪክ ያለው መሆኑን ገልጸው፣ ቅድስት መንበር የሰላም እና የአንድነት ዲፕሎማሲ እንደምታራምድ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጭው መስከረም 19/2016 ዓ. ም. የካርዲናልነት ማዕረግ ከሚሰጧቸው 21 የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መካከል አንዱ የሆኑት ጣሊያናዊ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ ከጥር 8/2015 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የምሥራቅ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ሃላፊ ሆነው አገልግሎታቸውን መጀመራቸው ይታወሳል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ ወደዚህ ሃላፊነት ከመዛወራቸው አስቀድመው የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት በሚገኙባቸው አገራት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2002 ዓ. ም. በጆርጂያ፣ በአርሜኒያ እና አዘርባዣን፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2011 ዓ. ም. ቤላሩስያ፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ 2015-2020 ዓ. ም. በዩክሬይን እንዲሁም በብሪታኒያ የቅድስት መንበር እንደራሴ በመሆን ማገልገላቸውን ገልጸዋል።

ለካርዲናልነት ማዕረግ መታጨታቸውን በድንገት መስማታቸውን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ ሹመቱ ከምንም በላይ ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለበት እና ሰማዕትነትም ጭምር ያለበት ነው ብለዋል። “ከዚህ በፊት በነበረኝ የቅድስት መንበር እንደራሴነት ዓመታት መካከል በርካታ የደም መስዋዕትነቶችን ለመመልከት በቅቻለሁ” ያሉት አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ ብዙ ክርስቲያኖች ለኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ሲሉ የደም ዋጋ ሲከፍሉ ማየታቸውን ገልጸው፥ ከሁሉ በፊት አሁን በእግዚአብሔር የተጠየቁትን ታማኝነት አስፈላጊ ከሆነ ሕይወትን እስከ መስጠት ድረስ ለቤተ ክርስቲያን እና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በተጨባጭ መንገድ ለመግለጽ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የላቲን ፓትሪያርክ የሆኑት የብፁዕ አቡነ ፒዬርባቲስታ ፒዛባላ መልዕክትን እንደሚጋሩት የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ በአገልግሎት ላይ የሚገኙበት የምሥራቅ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ጽሕፈት ቤት መካከለኛውን የምሥራቅ አገራት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን፣ ኤርትራን እና ዩክሬይንን የሚያካትት መሆኑን ገልጸዋል። አካባቢዎቹ ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻልበት ደረጃ፣ በተለይ በዚህ ጊዜ ደም አፋሳሽ ታሪክ ያላቸው እና እስከ ሰማዕትነት ድረስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝነትን በመግልጽ የቆዩባቸው አካባቢዎች መሆናቸውን ገልጸው፥ ከፍተኛ የክርስቲያን ቁጥር እንደነበራቸው የምናውቃቸው እነዚያ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ዛሬ ላይ በጣም ጥቂት ክርስቲያኖች እንዳሏቸው ተናግረዋል።

“ዋስትናችን፣ ጌታችን እና መምህራችን፣ ደሙንም ያፈሰሰልን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ከሌሎች ብዙ ቤተ ክርስቲያናት በተለየ መንገድ የቤተ ክርስቲያን መሥራች ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተወለድን ነን” ብለዋል። የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት እምነት በንጉሣዊ ሃይማኖቶች እና ከዚያም በሌሎች አሃዳዊ ሃይማኖቶች ውስጥ ትልቅ መገረምን ያስከተለበት፣ በተከበረ የሰው ልጅ ላይ አስከፊ የጭካኔ ተግባር እንዲደርስ የተደረገበት ዋናው ምክንያት ይህ ነው” ብለው፥“እኛ መንግሥትን የመሠረተ አሸናፊ ነቢይ የሌለን፤ ምድራዊ ከተማ ያለን ሕዝቦች ሳንሆን ነገር ግን ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም የምንጓዝ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን” ብለዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2025 ዓ. ም. የሚከበረውን የኢዮቤልዩ በዓል በማስመልከት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቋቋሙትን አዲስ የሰማዕታት ኮሚሽን በደስታ ተቀብለናል ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ በርዕሠ ሊቃነ ጵጵስናቸው ወቅት ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ አዲስ ነገርን ያመጡት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቀጣይነት ያለው ሐዋርያዊ ተግባር እንደሆነ እና ይህ ተግባርም አሁን በላቀ ሁኔታ ወደ ኅብረት እና በደም ወደ ተገነባ ሰማዕትነት እየመራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ይህ ኅብረት በተለይም በልዩ ልዩ የክርስትና እምነቶች መካከል በገሃድ የሚታይ አንድነት እንደሆነ አስረድተዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ በማከልም “ለካርዲናልነት ማዕረግ መታጨቴ በጣም ያስገረመኝ እና ብዙ ያነጸኝ በመሆኑ ሃላፊነቱን ለመውሰድ ከተጠራሁ በሙሉ ልብ የምተባበርበት ነው” ብለዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ልዩ የሰላም መልዕክተኛ የብጹዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ተልዕኮን በዝርዝር ገና አላወቅሁም ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ በቤላሩስ፣ በዩክሬይን እና በጆርጂያ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ሆነው ማገልገላቸውን አስታውሰው፥ ማለት የሚችሉት ነገር ቢኖር “ከጀርባው እኛ ምዕራባውያን ብዙውን ጊዜ ሙሉ በሙሉ የማናውቅባቸው ውስብስብ ነገሮች አሉ” ብለዋል።

“የሶቪዬት ኅብረት ውድቀት እና የሶቪዬት ኅብረት ሕዝቦች ውስጣዊ አሳዛኝ ሁኔታዎችም ጭምር በምዕራቡ ዓለም በጥልቀት ታይቷል ወይም ግንዛቤን አግኝቷል የሚል ስሜት የለኝም” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ “በዚህ ምክንያት የብፁዕ ካርዲናል ማቴዎ ዙፒ ተልዕኮ ችግሮችን በመፍታት ረገድ ካለው የግል ችግር ጋር ብቻ ሳይሆን ከችግሮቹ ውስብስብነት ጋርም የተያያዘ ነው በማለት አስረድተዋል። በግልጽ መናገር የሚችሉትም “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር ከማንኛውም ምክንያታዊ አማራጮች በላይ ሰላምን እንደሚሹ እና ይህ ደግሞ ከምክንያታዊነት በላይ ከሆነ ጥልቅ እምነታቸው የተወለደ ነው” ብለዋል።

በጥቅምት ወር ላይ ሊካሄድ ከታቀደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ቀደም ብሎ በመጭው መስከረም 19/2016 ዓ. ም. የሚፈጸመውን የአዳዲስ ካርዲናሎች ሹመት ሥነ ሥር ዓት በታላቅ ተስፋ እንድሚጠብቁት የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ፥ በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ሰዎች ሁል ጊዜ ዝግጁዎች መሆናቸውን፣ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እና በሌሎች በርካታ ታሪካዊ ክንውኖች መንፈስ ቅዱስ አስገራሚ ሥራዎችን መሥራቱን አስታውሰዋል። በማከልም “በዚህ ሥነ-ሥርዓት ላይ እራሳችንን ለማሞገስ፣ ስኬቶቻችንን ለማስታወስ ወይም ደማቅ ዝግጅቶችን ለመመልክት ሳይሆን ነገር ግን ልባችን ለመንፈስ ቅዱስ ዝግጁ መሆኑን ለማስታወስ ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ለካርዲናልነት ማዕረግ ካጯቸው 21 የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መካከል አንዱ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክላውዲዮ ጉጄሮቲ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ገልጸዋል።

12 July 2023, 17:08