ፈልግ

የፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሚከበር የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል የፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሚከበር የዓለም ወጣቶች ፌስቲቫል  (AFP or licensors)

የዓለም ወጣቶች ቀን በአረጋውያን እና በወጣቶች መካከል መልካም ግንኙነት እንደሚፈጥር ተገለጸ

በቫቲካን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አባ ዮዋዎ ቻጋስ፥ ከሐምሌ 26-30/2015 ዓ. ም. ድረስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ለመገናኘት ከመላው ዓለም ወደ ሊዝበን የሚመጡ ወጣቶች ደስታን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ዓለም አቀፍ የወጣቶች በዓል መንፈሳዊ ለውጥን የሚያመጣ ክስተት እና በወጣቶች እና በአረጋውያን መካከል መልካም የልምድ ልውውጥ የሚደረግበት ይሆናል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አባ ዮዋዎ ቻጋስ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉትን ቃለ ምልልስ ወጣቶች በሊዝበን ከሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የኢየሱስ ክርስቶስን መለወጥ እና የፋሲካን ልምድ ከልብ ተረድተው እንደሚመለሱ ገልጸዋል። በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የወጣቶች ቢሮ ተጠሪ የሆኑት አባ ዮዋዎ ቻጋስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፖርቱጋል ከሚያደርጉት 42ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝት ከማድረጋቸው ጥቂት ቀናት ቀደም ብለው እንደተናገሩት ባሁኑ ጊዜ በወጣቶች ላይ የሚታየውን ደስታ እና ቅንዓት አስመልክተው ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በተለይ ወጣቶችን በልዩ ሁኔታ ሲጠባበቁ በነበሩ አረጋውያን ልብ ሳይቀር ደስታው እንደሚታይ ገልጸዋል።

በጉጉት የሚጠበቅ የወጣቶች ፌስቲቫል

ከፖርቱጋል መንግሥት እና ከቤተ ክኅነት ባለስልጣናት የቀረበላቸውን ግብዣ የተቀበሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐምሌ ወር ወደ ሊዝበን እና ወደ ፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ በዓለም የወጣቶች ቀን ላይ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ቅዱስነታቸው በፖርቱጋል ከሐምሌ 26-30/2015 ድረስ በዋና ከተማዋ ሊዝበን በሚያደርጉት ቆይታ ሐምሌ 29/2015 ዓ. ም. ወደ ፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ መንፈሳዊ ንግደት እንደሚያደርጉ የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መርሃ ግብር ያመለክታል።

የፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የምታስተናግደው የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሚመሩት አራተኛው የዓለም ወጣቶች ቀን ሲሆን፥ ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2013 ዓ. ም. በብራዚል ሪዮ ዴ ጄኔሮ፣  በ 2016 ዓ. ም. በፖላንድ ክራኮቪያ፣ በ2019 ዓ. ም. በፓናማ ሲቲ በተከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ተገኝተው ለወጣቶች መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

ዘንድሮ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ላይ የሚከበረው 37ኛው ዓለም የወጣቶች ቀን እንደ ጎርጎርሳውያኑ በ2022 ዓ. ም. ሊከበር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ይታወሳል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዘንድሮ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን የመረጡት መሪ ጭብጥ ከሉቃ. 1:39 የተወሰደ እና “ማርያም በፍጥነት ተነስታ ሄደች” የሚል እንደሆነ ይታወቃል።

በሊዝበን ከተማ የሚታይ ተጨባጭ ሁኔታ

በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የወጣቶች ቢሮ ተጠሪ የሆኑት አባ ዮዋዎ ቻጋስ፥ በፖርቱጋል ሐዋርያዊ ጉብኝት የሚያደርጉትን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በደስታ ለመቀበል የአገሩ ሕዝብ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፥ በአገሪቱ የሚገኙ ቁምስናዎች እና አብያተ ክርስቲያናት ከመላው ዓለም የሚመጡ ወጣቶችን ለመቀበል ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፥ በዝግጅቱ ላይ አረጋውያንም በንቃት መሳተፋቸው አክለው ገልጸዋል።

በአረጋውያን እና በወጣቶች መካከል ያለው ግንኙነት

ቤተ ክርስቲያን ያለፈው እሁድ ሐምሌ 16/2015 ዓ. ም. 3ኛውን የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን በድምቀት ማክበሯን ያስታወሱት አባ ዮዋዎ፥ አረጋውያንም በበኩላቸው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን ለመቀበል በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ተናግረው፥ ይህም በወጣቶች እና በአረጋውያን መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

ወጣቶች ከኢየሱስ ጋር ለመገናኘት ያላቸው ፍላጎት

በከፍተኛ ድምቀት ሊከበር እየተጠበቀ ያለው የዓለም ወጣቶች ቀን፥ የመላው ዓለም ወጣቶች ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ወጣቶች እርስ በርስ ለመገናኘት ያላቸውን ፍላጎት ከፍ ማድረጉን አባ ዮዋዎ ገልጸዋል።

ከሐምሌ 10/2015 ዓ. ም. ጀምሮ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሚገኙት በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የወጣቶች ቢሮ ተጠሪ የሆኑት አባ ዮዋዎ ቻጋስ፥ በዚህ ወቅት ከመላው ዓለም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወጣቶች ወደ ፖርቱጋል መዲና ሊዝበን እየገቡ መሆናቸውን ተናግረዋል። ወጣቶቹ በደስታ እና በቅንዓት መሞላታቸውን የገለጹት አባ ዮዋዎ፥ በከተማይቱ ውስጥ በየቦታ በጎ ፈቃደኞች መሰማራታቸውን ገልጸው፥ በፖርቱጋል የሚገኙ ሀገረ ስብከቶችን ጨምሮ ወጣቶች በፌስቲቫሉ ለመገኘት እና እርስ በርስ ለማገናኘት ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም ወጣቶች ቀን 'ምስጢር'

ካለፉት አርባ ዓመታት ወዲህ የዓለም ወጣቶች ቀን እየተጠናከረ እና እያደገ የመጣበት ምስጢር ምን እነደሆነ የተጠየቁት አባ ዮዋዎ፥ “መንፈሳዊ ንግደት በማድረግ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት አዲሱን ትውልድ ሁል ጊዜ በጉጉት እንዲጠብቅ አድርጎታል” ብለዋል። "የዓለም ወጣቶች ቀንን ያስጀመሩት የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደነበሩ ያስታወሱት አባ ዮዋዎ፥ ይህም በምሕረት ዓመት እንደነበር ገልጸው፥ በዓሉ የመስቀል እና የትንሳኤ በዓል፣ የፋሲካም ምሥጢር በመሆኑ መንፈሳዊ ንግደት የሚደረግበት ወቅት እንደሆነም አስረድተዋል።

ከኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚገኝ ለውጥ

የዓለም ወጣቶች ቀን፥ ወጣቶች በኢየሱስ ክርስቶስ ክህነታዊ አገልግሎት እንዲሳተፉ የተጋበዙበት ነው” ያሉት አባ ዮዋዎ፥ ይህን በዓል በኅብረት ለማክበር ወደ ልዩ ልዩ አገራት የሚደረግ መንፈሳዊ ንግደት መስዋዕትነትን ይጠይቃል ብለዋል። አባ ዮዋዎ በማከልም ወጣቶች ሊዝበን ላይ ከሚያከብሩት የዓለም ወጣቶች ቀን በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘውን ለውጥ ተቀብለው፥ በልባቸውም ለውጥ በማምጣት እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

26 July 2023, 12:58