ፈልግ

ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን   (Vatican Media)

ከትውልድ እስከ ትውልድ ወንድማማችነትን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ

በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የአረጋውያን ሕይወት መምሪያ ተጠሪ የሆኑት አቶ ቪቶሪዮ ሼልዞ፥ የበለጠ ወንድማማችነት ያለውን ዓለም ለመገንባት በትውልዶች መካከል አዲስ ትስስር መፍጠር እንደሚያስፈል አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር እሑድ ሐምሌ 16/2015 ዓ. ም. በተከበረው ሦስተኛ ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን ላይ ከመላው ጣሊያን የመጡ ከስድስት ሽህ በላይ አረጋውያን ተካፋይ መሆናቸው ተመልክቷል።

የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን በየዓመቱ እንዲከበር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2021 ዓ. ም. መወሰናቸው የሚታወስ ሲሆን ዓላማውም፥ “ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየውን መንፈሳዊ እና ሰብዓዊ ሀብት ጠብቆ ለማቆየት እንዲረዳ በማሰብ  የኢየሱስ ክርስቶስ አያቶች የሆኑት ቅዱስ ኢያቄም እና ቅድስት ሐና ዓመታዊ በዓል በሚከበርበት የሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ እንዲከበር መወሰናቸው ይታወሳል።

ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን እና የዓለም ወጣቶ ቀን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለዓለም የአረጋውይን ቀን እንዲሆን በማለት የመረጡት መሪ ጥቅስ፥ በሉቃ. 1:50 ላይ የተጻፈው “እግዚአብሔር ለሚፈሩት ሰዎች ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ ምሕረቱን ያደርጋል” የሚል ሲሆን፥ በሉቃስ ወንጌል ላይ  እንደተገለጸው፥ ወጣቷ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ከኤልሳቤጥ ጋር ስትገናኝ የተሰማትን ደስታ በማስታወስ በአረጋውያን እና በወጣቶች መካከል ያለውን ግንኙነት በማሳደግ በክርስቲያኖች መካከል ደስታን ለማምጣት መፈለጋቸው ታውቋል።

ዓለም አቀፍ የዓረጋውያን ቀን፥ ከሐምሌ 26-30/2015 ዓ. ም. ድረስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ከሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ቀደም ብሎ መሆኑ ታውቋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እነዚህ ሁለት ትላልቅ በዓላትን ማለትም ዓለም አቀፍ የአረጋውያን ቀን እና የወጣቶች ቀን በአንድ ወቅት እንዲከበሩ ያደረጉት በወጣቶች እና በአረጋውያን መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሳደግ እና በትውልዶች መካከል መተባበን ለመፍጠር በማሰብ እንደሆነ ታውቋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ የቀረበው መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የበዓሉን ዓለም አቀፋዊነት አጉልቶ ያሳየ ሲሆን፥ ሥነ ሥርዓቱን ከአምስቱም አኅጉራት የመጡ አረጋዊን መካፈላቸው ታውቋል። በዕለቱ በቀረበው መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በሊዝበን ከተማ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለሚገኙ አምስት መንፈሳዊ ነጋዲያን ወጣቶች ቅዱስ መስቀል በምሳሌነት መሰጠቱ ታውቋል።

ማኅበረሰባዊ ወንድማማችነትን በተጨባጭ ማሳየት

እሑድ ሐምሌ 16/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የተከበረውን የዓረጋውያን ቀን በማስመልከት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት ትሲያና ካምፒሲ እና ቪቶሪዮ ሼልዞ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶችም እና አዛውንቶች በተለያየ ኅብረተሰብ ውስጥ ያላቸው ግንኙነት እንዲያስቡበት መጋበዛቸውን አስታውሰዋል። በተለይም ከወረርሽኙ በኋላ አረጋውያን በበለጠ ብቸኝነት እንደሚጠቁ እና ወጣቶችም በጥላቻ የሚሰቃዩበት ሁኔታ እንዳለ መናገራቸውን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ሁላችን ወንድማማቾች ነን” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፥  የወንድማማችነት ትስስር ጠንካራ ኅብረተሰብን ሊገነባ እንደሚችል መግለጻቸውን፥ በቅድስት መንበር የምእመናን እና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የአረጋውያን ሕይወት መምሪያ ተጠሪ የሆኑት አቶ ቪቶሪዮ ሼልዞ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተናግረው፥ “በመሆኑም እያንዳንዱ በራሱ መንገድ የሚሄድ በሚመስል ትውልድ መካከል አዲስ ትስስር መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፥ ወጣቶችን እና አዛውንትን በማገናኘት የወንድማማችነትን ማኅበራዊ ትስስርን እንደገና መፍጠር እንችላለን” ብለዋል።

ወጣቶች እና የሰላም ህልማቸው

በሁለቱ ትውልዶች መካከል የሚደረግ ግንኙነት ለሁለቱም ጠቃሚ ይሆናል ያሉት አቶ ሼልዞ በተለይም አሁን ያለው ሁኔታ አውሮፓን በአዲስ የጦርነት ስጋት ውስጥ ማስገባቱን ተናግረዋል። "ሰላምን የገነባ ትውልድ ልጆች ነን” ያሉት አቶ ሼልዞ፥ ባለፉት 80 ዓመታት ውስጥ ዓረጋውያን በአውሮፓ የገነቡትን እና የኖሩትን የሰላም ሕልም የዛሬ ወጣቶች ሊመሰክሩት ያስፈልጋል" ብለው፥ በሌላ በኩል ወጣቶች ከዓረጋውያን ጋር የሚያደርጉት ግንኙነት አረጋውያንን ከብቸኝነት ስሜት እንዲወጡ ይረዳቸዋል በማለት አክለዋል።

የመንፈስ ቅዱስ ሚና

በሉቃ. 1:50 ላይ እንደተጻፈው፥  “እግዚአብሔር ለሚፈሩት ሰዎች ሁሉ ከትውልድ እስከ ትውልድ ምሕረቱን ያደርጋል” የሚለውን የአረጋውይን ቀን መሪ ጥቅስ ያስታወሱት አቶ ሼልዞ፥ በዚህ ጥቅስ አማካይነት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በወጣቶች እና በዓረጋውያን መካከል በሚደረግ ግንኙነት የመንፈስ ቅዱስን መኖር እንድናይ አስተምረውናል" ብሏል።

 

24 July 2023, 15:07