ፈልግ

የቻይና ካቶሊክ ምዕመናን በሻንጋይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ጸሎት ሲያቀርቡ የቻይና ካቶሊክ ምዕመናን በሻንጋይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ጸሎት ሲያቀርቡ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሻንጋይ አዲስ ጳጳስ መሾማቸውን ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በቻይና ሕዝባዊት ሪፐብሊክ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዲሁም በሁለቱ አገራት መካከል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2018 እና ከዚያም በ 2020 እና በ 2022 ዓ. ም. የተፈረመውን ጊዜያዊ ስምምነት በማስመልከት ማብራሪያ ሰጥተዋል። ስምምነቱ በቻይና ሕዝባዊት ሪፐብሊክ የሚሰጠውን የጳጳሳት ሹመት የሚመለከት መሆኑን ገልጸው፣ መሠረታዊ መርሆውን የተከተለ በመሆኑ ሊከበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሂደቱ መተማመንን ሊቀንሱ የሚችሉ እንቅፋቶች ያሉበት ውስብስብ መንገድ መሆኑን ገልጸው፣ ቢሆንም ከመሰናክሎች ባሻገር ጥንካሬን በመጨመር የጋራ ውይይቶችን ለማድረግ የሚረዳ የግዴታ መንገድ መሆኑን ጠቅሰዋል። በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የተሾሙትን የሻንጋይ ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ ሼን ቢን ያስወሱት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፣ ቀደም ሲል የተደረገውን ስምምነት ሳያካትት የቻይና ባለሥልጣናት ቅድስት መንበርን በማሳወቅ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ሼን ቢንን በአዲስ ሀገረ ስብከት እንደመደቧቸው ገልጸዋል።

በይደር ላይ የሚገኙ ጉዳዮች

“ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ ሼን ቢን ትጉህ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ናቸው” በማለት በቃለ ምልልሳቸው የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሀገረ ስብከቱ ታላቅ ጥቅም ማበርከት እንደሚችሉ በመገንዘብ ከሕገ ቀኖናዊ መንገድ ውጭ ለጳጳስነት መምረጣቸውን አስረድተዋል። ይሁን እንጂ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ይህ ሂደት “በቫቲካን እና በቻይና መካከል ላለፉት ዓመታት በተግባር ሲገለጽ የቆየውን ስምምነት የተመለከተ የውይይት እና የትብብር መንፈስ ችላ ያለ ይመስላል” ብለው፥ ፍትሃዊ እና ጥበብ የተሞላበት መፍትሄን የሚያስፈልጋቸው እና ከጵጵስና ማዕረግ ታግደው የቆዩት አባ ታዴዎስ ማ ዳኪን እና ጡረታ የወጡት ብጹዕ ዮሴፍ ሺንግ ዌንዚ መኖራቸውን አስታውሰዋል።

አለመግባባቶችን የሚያስወግዱ ስምምነቶች

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ከቻይና ባለስልጣናት ጋር በመከባበር መንፈስ ግልጽ ውይይት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ በየጊዜው የሚነሱ ችግሮች የቤተ ክርስቲያን አካል ከሆኑ ቻይና ውስጥ ምንም ዓይነት እንቅፋት እንደማይኖር በድጋሚ ተናግረዋል። ነገር ግን በሁለቱ ወገኖች መካከል ስምምነት ከሌለ ችግሮች በተከታታይ ሊፈጠሩ እንደሚችሉ በመግለጽ ስምምነቱ በትክክል መተግበሩ ችግሮችን ለማስወገድ ያስችላል ብለዋል። የሀገረ ስብከት የአገልግሎት ሥፍራ ምድባን ጨምሮ ቻይና ውስጥ የሚሰጡ የጵጵስና ሹመቶችን በስምምነት በማካሄድ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው የውይይት መንፈስ እንዲቀጥል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረው፥ አለመግባባቶችን የሚፈጥሩ ግጭቶችን በጋራ መከላከል አለብን ብለዋል።

ሦስቱ አስቸኳይ ጉዳዮች

አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጣቸው በሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ በተለይ ሦስቱን ርዕሠ ጉዳዮችን ለይተው፥ እነርሱም የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ፣ የቻይና ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳት ጋር ያለውን ግንኙነት እና የወንጌል ስርጭት አገልግሎት እንደሆኑ ገልጸዋል። የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ምስረታ የቅድስት መንበር ፍላጎት መሆኑን ገልጸው፥ በቻይና ውስጥ በምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አመራር ውስጥ የጳጳሳት ኃላፊነት በቤተ ክርስቲያኒቱ እድገትን ለማምጣት ያለውን ፍላጎት ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

በዚህ መሠረት የቻይና ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ከሮም ጳጳስ ጋር መደበኛ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ ይህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር እና አስተምህሮ እንደሆነ እና የቻይና ባለሥልጣናት ይህን መዋቅር መለወጥ የማይፈልጉ በመሆናቸው ውጤታማ ኅብረት መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል። የቻይና ካቶሊካዊ ምዕመናን የወንጌል አገልግሎት ሥራን ሊያዘገዩ እና ሊያደናቅፉ የሚችሉ ብዙ ጥንቃቄዎች ቢኖሩም የተደበቁ ተብለው የተገለጹት የወንጌል አገልግሎቶች እንኳ እምነት ሊጣልባቸው ይገባል” በማለት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ተናግረዋል። “የቻይና መንግሥት በካቶሊክ እምነት ላይ ያለውን አለመተማመን ማስወገድ እንደሚያስፈልግ እና ሃይማኖቱን እንደ ባዕድ ከመቁጠር ይልቅ የዚያ ታላቅ ሕዝብ ባሕል አካል አድርጎ መቁጠር ያስፈልጋል” ብለዋል።

ቻይና ውስጥ መገናኛ ጽሕፈት ቤት መክፈት

ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ይህን ቃለ መጠይቅ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆኑበት ዋናው ምክንያት ቻይና ውስጥ ያሉ ካቶሊካዊ ምእመናን ብቻ ሳይሆኑ በሁሉም ቦታ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን እውነቱን በትክክል የማወቅ መብት ስላላቸው ነው ብለዋል። በጉዞ ላይ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች መተማመንን ለማዳከም እና አወንታዊ ጉልበትን ለመቀነስ የተቀመጡ መሆናቸውን ያመኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን፥ ቢሆንም ለውይይት አስፈላጊነት የሚሰጡ ምክንያቶች የበለጠ ጠንካራ እንደሆኑ ያላቸውን እምነት ገልጸው፥ በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገው ውይይት ይበልጥ ፈጣን እና ፍሬያማ እንዲሆን ለመርዳት በቻይና የቅድስት መንበር የመገናኛ ጽሕፈት ቤት እንዲከፈት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ሐሳብ አቅርበዋል። አክለውም “ቻይና ውስጥ የሚከፈተው የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤቱ ከሲቪል ባለስልጣናት ጋር ለመነጋገር ብቻ ሳይሆን በቻይና ቤተ ክርስትያን ውስጥ ሙሉ እርቅ እንዲፈጠር አስተዋፅኦ ያደርጋል" ብለዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ሲደመድሙ፥ “ታሪካዊ ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ስምምነት ብንፈራረምም ነገር ግን ሙሉ በሙሉ እና ትክክለኛ በሆነ መንገድ በተግባር መገለጽ አለበት” ብለው፥ ቅድስት መንበር የጋራ ጉዞው እንዲቀጥል የበኩሏን ድርሻ ለመወጣት ቆርጣ መነሳቷን አረጋግጠዋል።

17 July 2023, 15:07