ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአረጋውያን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአረጋውያን ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ 

ቅድስት መንበር የአረጋውያንን ቀን ለሚያከብሩት ምዕመናን የእግዚአብሔር የምሕረት ጸጋ መላኩን ገለጸች

እሁድ ሐምሌ 16/2015 ዓ. ም. የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን በጸሎት ለሚያስታውሱ ምዕመናን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የእግዚአብሔርን ምሕረት በቡራኬ መላካቸውን የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ማረሚያ ቤት አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በምእመናን መካከል ፍቅርን ለማዳበር የሚደረገውን እንቅስቃሴ ለማበረታታት በቅድስት መንበር የምእመናንና የቤተሰብ ሕይወት መምሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ፕሬዚደንት ከሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ዮሴፍ ፋሬል የቀረበለትን ጥያቄ ሐዋርያዊ ማረሚያ ቤቱ ተቀብሎታል። ብጹዕ ካርዲናል ኬቪን ዮሴፍ ፋሬል በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምኞት ተቋቁሞ ሐምሌ 16/2015 ዓ. ም. በሚከበረው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን ላይ ለሚሳተፉት ካቶሊካዊ ምዕመናን የእግዚአብሔር የምሕረት ጸጋ እንዲላክላቸው ጠይቀዋል። ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን መሪ ጥቅስ፥ በሉቃ. 1፡50 ላይ የተጻፈው እና “ምሕረቱም ከትውልድ እስከ ትውልድ እርሱን በሚፈሩት ላይ ይኖራል” የሚል እንደሆነ ታውቋል።

ምዕመናን ለእግዚአብሔር ምሕረት የሚዘጋጁባቸው መንገዶች

በሐዋርያዊ ማረሚያ ቤት ተረቅቆ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸደቀው ሐዋርያዊ ድንጋጌ እንዳመለከተው፥ በቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሚመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ላይ ለሚሳተፉት አያቶች እና አረጋውያን እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚቀርበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ለሚካፈሉት ምእመናን በሙሉ የእግዚአብሔር የምሕረት ጸጋ የሚደርሳቸው መሆኑን ሐዋርያዊ ማረሚያ ቤቱ አስታውቋል።

የምሕረት ጸጋው፥ ዘወትር ለምዕመናን የሚሰጡትን የኑዛዜ እና የቅዱስ ቁርባን ምስጢራት የተለመዱ ቅድመ ዝግጅቶችን ማሟላት እንዲሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በጸሎት ማስታወስን የሚጠይቅ ሲሆን፥ ቀደም ሲል በተፈጸመው ኃጢአት ለተሰጠው ጊዜያዊ ቅጣት ይቅርታን የሚያስገኝ እና ከሞት በኋላ የኃጢአት ካሳን በመክፈል ላይ ለሚገኙ ነፍሳትም ሊደርስ እንደሚችል ሐዋርያዊ ማረሚያ ቤቱ ገልጿል።

የምሕረት ጸጋው፥ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው አረጋውያን ወንድሞችን እና እህቶችን፣ ከማኅበረሰቡ ተገልለው ችግር ላይ የወደቁትን፣ የታመሙትን  እና በሌሎች ችግሮች ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች፥ ጊዜያቸውን ሰውተው በአካልም ሆነ በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል ደርሰው የሚጠይቁትን በሙሉ የሚደርሳቸው መሆኑን ሐዋርያዊ ማረሚያ ቤቱ አስታውቋል።

በከባድ ችግር ምክንያት በዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን የሚቀርበውን የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በመንፈስ ወይም በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች አማካይነት ለሚሳተፉት ምዕምናንም ጭምር የምሕረት ጸጋው እንደሚደርሳቸው ሐዋርያዊ ማረሚያ ቤቱ አስታውቆ፥ ነገር ግን ጸጋውን ለመቀበል የሚመኙ ምእመናን ከኃጢአት ርቀው የተለመዱ ሦስቱን ቅድመ ዝግጅቶች ቶሎ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስቧል።

አረጋውያን የጥበብ እና የልምድ ምንጭ ናቸው

የሐዋርያዊ ማረሚያ ቤት ድንጋጌ በማከልም ሥልጣኑ የተሰጣቸው ካህናት ንስሐ መግባት ለሚፈልጉ ምዕመናን በበጎ መንፈስ ራሳቸውን በማቅረብ ኑዛዜያቸውን እንዲያዳምጡ አሳስቦ፥ የምሕረት ጸጋው ለምዕምናኑ የሚደርሰው ሐምሌ 16/2015 ዓ. ም. በሚከበረው ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን መሆኑን አስታውቋል።

በቅድስት መንበር ሥር የሚገኘው ሐዋርያዊ ማረሚያ ቤቱ ምእመናን መንፈሳዊ ሕይወታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ በማሳደግ፣ አቅመ ደካማ የሆኑ አረጋውያንን በመደገፍ ከእግዚአብሔር ምሕረትን የሚቀበሉበት ዕድል መኖሩን አስታውቆ፥ በቫቲካን በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ እሁድ ሐምሌ 16/2015 ዓ. ም. በመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚከበረው ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የአያቶች እና የአረጋውያን ቀን፥ አረጋውያን ለኅብረተሰብ እና ለቤተ ክርስቲያን የሚያቀርቡትን ወደር የሌለውን ጥበብ፣ ልምድ እና ፍቅር የሚያስታውስ መሆኑ ገልጿል።

06 July 2023, 14:41