ፈልግ

በታንዛኒያ የሚገኙ የንፁህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅበር ገዳም አባላት  በታንዛኒያ የሚገኙ የንፁህ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅበር ገዳም አባላት  

የማኅበረ ካኅናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት የክኅነት አገልግሎት ውበትን በድጋሚ ማወቅ እንደሚገባ አሳሰበ

በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1995 ዓ. ም. የተቋቋመው ዓመታዊው የቅዱስ ልበ ኢየሱስ በዓል በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዓርብ ሰኔ 16/2015 ዓ. ም. ተከብሮ ውሏል። በቅድስት መንበር የማኅበረ ካኅናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ተፈርሞ በዕለቱ ይፋ የሆነው መልዕክት፥ ለመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ የተሰጠውን የቅድስና ስጦታን ካኅናት ብቻ ማግኘት እንደሚችሉ አስምሮበታል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የማኅበረ ካኅናት ጳጳሳዊ ጽሕፈትቤቱ የክኅነት ቅድስና እና የቅዱስ ልበ ኢየሱስ ዓመታዊ በዓል አንድ ላይ በተከበረበት ዓርብ ሰኔ 16/2015 ዓ. ም. መልዕክቱን ይፋ አድርጓል። የጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1995 ዓ. ም. የክኅነት ቅድስና ቀንን ምክንያት በማድረግ፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ልብ እናስብ ዘንድ፣ አዕምሮአችንን እና ልባችንን በእርሱ ላይ እናሳርፍ ዘንድ ያለማቋረጥ ከተወጋው ጎኑ የሚፈሰው የጸጋ እና የምሕረት ወንዝ የክኅነት አገልግሎት ውበት መልሰን ማግኘት እና የተቀበለውን ስጦታ ለማደስ ያግዘናል" በማለት ያስተላለፉት መልዕክት ጠቅሷል።

በቅድስት መንበር የማኅበረ ካኅናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ላዛሮ ዩ ሄንግ ሲክ እና ዋና ጸሐፊው ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንድሬስ ገብርኤል ፌራዳ ሞሬራ፣ ምዕመናን በሙሉ ለተጨማሪ የክኅነት አገልግሎት ጥሪ እና ለምንኩስና ሕይወት ስጦታ ከእግዚአብሔር እንዲለምኑ አደራ ብለዋል። የዕለቱን ዓላማ በማስታወስ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የማኅበረ ካኅናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ብጹዕ ካርዲናል ላዛሮ ዩ ሄንግ ሲክ፥     “ለካኅናት ቅድስና የሚቀርብ ጸሎት ለአገልግሎቱ የተጠሩት ሰዎች የሚያገኙትን የቅድስና ስጦታ የእግዚአብሔር ሕዝብም እንዲያገኝ ያግዛል” ብለዋል።

ከወንድሞች ጋር ወደ ቅድስና መጓዝ

የጥምቀትን ምስጢር የተቀበሉት በሙሉ በጋራ የክኅነት ጸጋ አማካይነት ለአጠቃላይ የቅድስና ጥሪ ነጻ እና አስደሳች ምላሽ ለመስጠት በክኅነታዊ አገልግሎት እንደሚደገፉ መልዕክቱ ገልጾ፥ “የካህናት ቅድስና የእግዚአብሔር ሕዝብ ከካኅናት ጋር ካላቸው ግንኙነት ጋር የተያያዘ እንደ ሆነ፥ ደስታቸውን እና ተስፋቸውን፣ ጭንቀታቸውን እና ሕመማቸውን አብረው የሚካፈሉ መሆኑን መልዕክቱ አስረድቷል።

በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ ካህኑ ወንድሞቹን እና እህቶቹን መውደድ እና የቅድስና ዓላማም ከእነርሱ ጋር አብሮ መጓዝ መሆኑን እንደሚማር፣ በተሰበረ የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ ካህኑ በእግዚአብሔር መወደዱን እንደሚያውቅ እና በመንፈስም ተቀድሶ ለዓለም መዳን ራሱን ማቅረብን እንደሚማር በመልዕክቱ ላይ ተገልጿል።

ካኅናት ስለ እግዚአብሔር እንዴት እንመሰክራለን?

የማኅበረ ካኅናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዓመታዊ መልዕክቱ በመቀጠልም፣ እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን የቅዱሳን እረኞች ስጦታን ከእግዚአብሔር መለመን እንደሚገባ ጠይቆ፥ በዚህ የሲኖዶሳዊ ጉዞ ወቅትም መላዋ ቤተ ክርስቲያን ከሁሉም በላይ የእግዚአብሔርን ቃል በጋራ ለመካፈል፣ እውነተኛ እና አስደሳች ምስክርነት ለመስጠት መጠራቷን አስታውሷል። “እኛ ለሐዋርያዊ አገልግሎት የተሾምን ስለ እግዚአብሔር በምን ዓይነት መንገድ እንመሰክራለን?” በማለት የጠየቁት ብጹዕ ካርዲናል ላዛሮ ዩ ሄንግ ሲክ እና ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንድሬስ ገብርኤል ፌራዳ ሞሬራ፣ “ስለ እኛ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት እና ምእመናን ስለ ራሳቸው ሲናገሩ እና ስለ እግዚአብሔር ሲመሰክሩ የትኛውን አምላክ አይተው ወይም አግኝተው ይመሰክራሉ?” በማለት አክለው ጠይቀዋል። እግዚአብሔር በአንድ የክርስቲያን ማህበረሰብ ውስጥ ራሱን በቅዱስ ቁርባን በኩል እንደሚገልጽ እና እርሱን በሚያምኑት፣ በተሾሙት ካኅናት እና ምዕመናን መካከል ባለው ግንኙነት አማካይነት በግልጽ እንደሚታይ ተናግረዋል።

ካህን ቅርበቱን የሚገልጽባቸው አራት መንገዶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የዛሬው ካኅን ከምዕመናን ጋር ያለውን ቅርበት የሚገልጽባቸው አራት መንገዶች ብለው የተናገሩትን በመጥቀስ የሚያጠናቅቀው መልዕክቱ፥ ቅዱስነታቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የካቲት 17/2022 ዓ. ም. ለሲምፖዚየሙ ተካፋዮች ባሰሙት ንግግር፥ እንደ ክህነታዊ ሥነ-መለኮት አስተምህሮ መሠረት አንድ ካኅን ከሁሉ አስቀድሞ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ እንዳለበት፥ ካኅን እራሱን ወደ እግዚአብሔር ዘንድ በማቅረብ ብቻ ለአገልግሎቱ የሚያስፈልገውን ጥንካሬ ማግኘት እንደሚችል፥ ቀጥሎም ወደ ጳጳሱ መቅረብ እና መታዘዝ ይህም ማዳመጥን መማር እና ማንም ራሱን የእግዚአብሔር ፈቃድ ባለቤት ነኝ ማለት እንደማይችል ማስታወስ እና መረዳት እንዳለበት፥ በሦስተኛ ደረጃ በካኅናቱ በካከል መቀራረብ ሊኖር እንደሚገባ፥ ከብቸኝነት እና ከግዴለሽነት በመራቅ በትዕግስት እና በወንድማማችነት መንፈስ አንዱ በሌላው ሃላፊነት እንዲሰማው እና በመጨረሻም ካኅን ከምዕመናኑ ጋር ያለውን ቅርበት እንደ ግዴታ ሳይሆን እንደ ፀጋ መቀበል እንዳለበት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምክራችውን መለገሳቸውን በቅድስት መንበር የማኅበረ ካኅናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በዘንድሮ መልዕክቱ ላይ ጠቅሷል። 

17 June 2023, 17:34