ፈልግ

በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ የተካሄደ ዓለም አቀፍ ስብሰባ በሰብዓዊ ወንድማማችነት ላይ የተካሄደ ዓለም አቀፍ ስብሰባ 

በሕዝቦች መካከል ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚቻል የሚያሳይ ዝግጅት ተካሄደ

በሕዝቦች መካከል ሰብዓዊ ወንድማማችነትን ማሳደግ እንደሚቻል የሚገልጽ ዝግጅት ሰኔ 3/2015 ዓ. ም. በቫቲካን መቅረቡን የቫቲካን ሚዲያዎች ዘግበዋል። ሠላሳ የኖቤል ሽልማት አሸናፊዎች በተገኙበት ሥነ-ሥርዓት ላይ የሙዚቃ ዝግጅት እና ምስክርነቶች ቀርበዋል። “Not alone” በሚል ርዕሥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ዋና ዓላማ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ቤተሰብ መካከል የእርስ በርስ ውይይት እና የመተሳሰብ ባሕልን እንዲሁም ፍትሃዊነትን ለማሳደግ ለሚያደርጉት ጥረት ድጋፍ ለመስጠት እንደሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ የተካሄደውን       ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ወንድማማችነት ስብሰባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በታላቅ ምኞት ለብዙ ጊዜ ሲጠብቁት እንደ ነበር ተነግሯል። ከሰዓት በፊት በነበረው የስብሰባ ጊዜ 30 የሚሆኑ የኖቤል የሰላም ተሸላሚዎች ከወጣቶች እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመሆን የወንድማማችነትን አስፈላጊነት በማስመልከት “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን ውስጥ በተጠቀሰው ጭብጥ ላይ ለመወያየት ዕድል አግኝተዋል።

በስብሰባው ላይ የ76 ድርጅቶች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ከሕክምና ዕርዳታ እና ስምሪት አስተባባሪ ድርጅት አባላት በተጨማሪ የክርስቲያን ሠራተኞች እንቅስቃሴ አባላት፣ የዓለማዊ ፍራንችስካውያን ማኅበር አባላት እና የጣሊያን የግብርና ማኅበራት አባላት ተገኝተዋል። “Not alone” ወይም “ብቻችን አይደለንም” በሚል ርዕስ የተካሄደው ዓለም አቀፍ የወንድማማችነት ስብሰባ ዋና ዓላማ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን የወንድማማችነት ህልም ለማስቀጥል በዚህ ወቅት ሆስፒታል ውስጥ ሕክምና ላይ የሚገኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን በጸሎት ለማስታወስ እንደሆነ ታውቋል።

ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚወስደው ጎዳና ላይ ድንኳኖችን የመትከል ሂደት
ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በሚወስደው ጎዳና ላይ ድንኳኖችን የመትከል ሂደት

በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ስምንት አደባባዮች ጋር ማገናኘት

ከቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዕድገት አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ ከቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት እና ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ጋር በመተባበር ስብሰባውን ያዘጋጁት የ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ፋውንዴሽን ጠቅላይ ጸሐፊ አባ ፍራንችስኮ ኦኬታ፥ “የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዓለምን ለመለወጥ ከምን ጊዜም በላይ ክፍት ቦታ ነው” በማለት ተናግረው፥ “የዝግጅቱ ዋና ማዕከል በቫቲካን የሚገኘው ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ቢሆንም ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ስምንት ታዋቂ አደባባዮች የራሳቸውን የወንድማማችነት ልምድ ለማካፈል እና ለማስተዋወቅ በቴሌቭዥን ስርጭት በቀጥታ መገናኘታቸውን አባ ፍራንችስኮ ኦኬታ አስረድተዋል።

የዝግጅቱ ተሳታፊ አገራት እና ከተሞች፥ በጣሊያን (ትራፓኒ)፣ በኮንጎ (ብራዛቪል)፣ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ (ባንጊ)፣ ኢትዮጵያ፣ በአርጀንቲና (ቦነስ አይረስ)፣ በእስራኤል (ኢየሩሳሌም)፣ በጃፓን (ናጋሳኪ) እና በፔሩ (ሊማ) መሆናቸው ታውቋል። ለወንድማማችነት እንቅስቃሴ ምስክርነታቸውን ከሰጡ ታዋቂ የሥነ ጥበብ ሰዎች መካከል አንዱ ዕውቁ ጣሊያናዊ ድምጻዊ አንድሪያ ቦቼሊ ሲሆን፥ ለታዳሚዎች ዝግጅቶቻቸውን ያቀረቡት ልዩ ልዩ ቤተሰቦች እና ማኅበራት፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ድሆች እና መጠለያ አልባዎች፣ ስደተኞች፣ የጥቃት እና ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች እንደነበሩ ተመልክቷል።

የሩሲያ እና የዩክሬን ወጣቶች እጅ መጨባበጥ

የወንድማማችነት ተጨባጭ ምልክት የሆነውን የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ አምዶችን በማንፀባረቅ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ወጣቶች እጅ ለእጅ ተያይዘው አንድነታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነት እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት ሁለት የዩክሬን እና የሩሲያ ወጣቶች መላው የሰው ልጅ ለሰላም ያለውን ፍላጎት ለመግለጽ እጅ መጨባበጣቸውን የቫቲካን ከተማ ረዳት አስተዳዳሪ እና የ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ማውሮ ጋምቤቲ ተናግረዋል። በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ቤተ ክርስቲያን ጦርነትን በመቃወም ለጋራ ውይይት እና ለሰላም ግንባታ ያላትን ቁርጠኝነት ያረጋገጠችበት የወንድማማችነት ሰነድ በመላው ዓለም ፊት ተፈርሟል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚደረገው ስብሰባ ዝግጅት በመደረግ ላይ እያለ
በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለሚደረገው ስብሰባ ዝግጅት በመደረግ ላይ እያለ

የሥነ ጥበብ እና የልምድ ልውውጥ

በዕለቱ የተካሄደው ስብሰባ እና ሌሎች ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በቫቲካን መገናኛዎች እና በኢጣሊያ ቴሌቪዥን አማካይነት በመላው ዓለም ውስጥ በቀጥታ የተላለፉ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በፋውንዴሽኑ ድረ ገጽ፣ ፌስቡክ እና ዩቲዩብ ማኅበራዊ መገናኛዎች በኩልም ተሰራጭተዋል። የሴርከስ እና የጎዳና ላይ አርቲስቶችም በአደባባዩ ለተገኙት ሰዎች ትርኢቶቻቸውን ሲያሳዩ ከጣሊያን ገጠራማ አካባቢዎች የመጡ የግብርና ማኅበራት ምርቶቻቸውን ለሰዎች በመጋራት ወንድማማችነትን አሳይተዋል።

የዝግጅቱ ተሳታፊዎች የወንድማማችነት ተክልን የሚያበቅሉበት አፈር እና ምርጥ ዘር የተሰጣቸው ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት የሚያብበውን ተክል ለመንከባከብ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩበት እና ለዝግጅቱ ዳራ ከሚሆኑት ምስሎች መካከል ሴቶች እና ወንዶች ዕጽዋዕት የሚበቅልበት ምድር ሊንከባከቡት፣ ውሃ ሊያጠጡት፣ ሊኖሩበት እና ሊጠብቁት የተጠሩ መሆናቸውን በምልክት ታይቷል።

12 June 2023, 12:50