ፈልግ

የሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት የሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት  (Archivio Fotografico Vatican Media)

የቫቲካን መገናኛ ብዙሃን ዕድገት የተመለከተ አዲስ መጽሐፍ መታተሙ ተገለጸ

የቫቲካን መገናኛ ብዙሃን “ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እስከ ድረ-ገጽ” የሚል ርዕስ የተሰጠው አዲሱ መጽሐፍ የቤተ ክርስቲያኒቱን የማኅበራዊ መገናኛ ዕድገት እና የተወሰዱ የተሃድሶ እርምጃዎችን የሚገልጽ እንደሆነ ታውቋል። በጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፈው የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ አቶ አንጄሎ ሼልዞ ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቫቲካን መገናኛዎች አንጋፋ ባለሙያ የሆኑት አቶ አንጄሎ በአዲሱ መጽሐፋቸው የቅድስት መንበር ብዙኃን መገናኛ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እስከ አሁን የደረሰበትን ደረጃ እና ያሳየውን ለውጥ ጭምር አስረድተዋል።ሮም በሚገኝ “LUMSA” ዩኒቨርሲቲ በተከናወነው ሥነ-ሥርዓት ላይ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ እና የቫቲካን ሬዲዮ ዳይሬክተር የነበሩ ኢየሱሳዊ ካኅን አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ ተገኝተዋል።

የመጽሐፉ ጸሐፊ አቶ አንጄሎ ሼልዞ ንግግር ሲያደርጉ
የመጽሐፉ ጸሐፊ አቶ አንጄሎ ሼልዞ ንግግር ሲያደርጉ

የመጽሐፉ ጸሐፊ አቶ አንጄሎ ሼልዞ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2016 ዓ. ም. ድረስ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ሆነው የሠሩ ሲሆን፥ ከዚያ አስቀድመውም “ሮዜርቫቶሬ ሮማኖ” የተባለ የቅድስት መንበር ዕለታዊ ጋዜጣ ዳይሬክተር፣ ቀጥለውም በአውሮፓውያን 2000 ዓ. ም. የኢዮቤልዩ ዓመት የቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙሃን መገናኛዎች ሃላፊ፥ እንዲሁም በቅድስት መንበር ጳጳሳዊ ምክር ቤት የማኅበራዊ መገናኛዎች ምክትል ዋና ጸሐፊ ሆነው ሠርተዋል። አቶ አንጄሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበራዊ መገኛዎች ዘርፍ ሌሎች መጽሐፍትንም ጽፈዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ
ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ

በቫቲካን መገናኛዎች ላይ ትኩረት ማድረግ

የቫቲካን መገናኛዎችን በስፋት የተመለከተው አዲሱ የአቶ አንጄሎ መጽሐፍ በዘርፉ የታዩ በጎ ለውጦችን በመዳሰስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን አካትቷል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቤተ ክርስቲያኒቱ መገናኛ ዘርፍ እየታዩ ያሉትን ለውጦች ከማብራራት በተጨማሪ፥ ቅድስት መንበርን በመገናኛው ዘርፍ ያጋጠማትን ዋና ዋና ተግዳሮቶች ተጠቁመዋል። ጸሐፊው ቤተ ክርስቲያን በመገናኛው ዘርፍ ያለፈችባቸውን የተለያዩ ጉልህ ደረጃዎች በማብራራት በተለይም ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ እስከ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድረስ የታዩ ማሻሻያዎችን ዳስሰዋል። አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ ለመጽሐፉ መግቢያ እንዲሆን ባበረከቱት ጽሑፋቸው፥ ታሪክን ወደ ኋላ ተመልሶ የመመልከት አስፈላጊነትን በማስመልከት፥ “በቤተ ክርስቲያኒቱ በመገናኛ ዘርፎች ላይ ተሃድሶ ማድረግ ደፋር እና ቀጣይነት ያለውን ሥራን የሚጠይቅ ቢሆንም በረዥም የታሪክ ዕይታ የቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ታማኝነት ማረጋገጫ እና ለማንኛውም ግንኙነት ዋነኛ አካል ነው" ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በመጽሐፉ ላይ የተካሄደ የባለሙያዎች ውይይት

በመጽሐፉ ይዘት ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡት እንግዶች መካከል፥ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣ የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት ብጹዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ፣ አባ ፌዴሪኮ ሎምባርዲ የቀድሞው የቫቲካን ሬዲዮ ዋና ዳይሬክተር እና በቫቲካን የር. ሊ. ጳ. ቤነዲክቶስ 16ኛ ፋውንዴሽን ፕሬዚደንት፣ አቶ ማርኮ ታርኩዊኖ “Avvenire” የተሰኘ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ፣ አቶ ገብርኤሌ ሮማኞሊ “La Repubblica” የተሰኘ የጣሊያን ዕለታዊ ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ እና አቶ ፍራንችስኮስ ቦኒኒ በሮም “LUMSA” የተሰኘ ካቶሊካዊ ዩኒቨርሲቲ ዳይሬክተር ሲሆኑ፥ ዝግጅቱን የመሩት ቫለንቲና አላዝራኪ፥ በሮም የሜክሲኮ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘጋቢ ነበሩ።

የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣
የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፓውሎ ሩፊኒ፣
14 June 2023, 11:54