ፈልግ

በቫቲካን ውስጥ የሚገኝ የሴት ዲፕሎማት ቡድን በሥራው ውጤታማ መሆኑ ተነገረ

በዲፕሎማሲ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴቶች ዓለም አቀፍ ቀን ምክንያት በማድረግ፥ በቅድስት መንበር የአውስትራሊያው አምባሳደር ወ/ሮ ኪያራ ፖሮ ስለ ሥራው ተግዳሮቶች እና የሚያስገኘውን ሽልማቶች በማስመልከት አስተያየታቸውን ገልጸዋል። አምባሳደር ኪያራ ሴት አምባሳደሮች በዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ያላቸውን አመለካከት በማስመልከት በሰጡት አስተያየት፥ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማት ሴቶች ቀን በየዓመቱ ሰኔ 17 ቀን መከበሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፥ በቫቲካን የሚገኝ የልዩ ልዩ አገራት የሴት ዲፕሎማት ቡድን በሥራው ውጤታማ መሆኑ ገለጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዲፕሎማሲያዊ ሥራ በተለምዶ በወንዶች የሚመራ እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ኪያራ፥ አውስትራሊያ ውስጥ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ተቀጥረው ሥራ የጀመሩባትን የመጀመሪያ ቀን በማስታወስ እንደገለጹት፥ በአውስትራሊያ የወጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ላለፉት ስድስት ዓመታት ሴቶችን ለመሪነት ለማብቃት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ተናግረዋል። በአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከአምስት ወይም ከስድስት ዓመታት በፊት በአምባሳደርነት ደረጃ ሥራቸውን የሚያካሂዱት ሴቶች ቁጥር 20% ብቻ እንደነበር ገልጸው፣ ነገር ግን ዛሬ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአውስትራሊያ የሴት አምባሳደሮች ቁጥር ወደ 40% ከፍ ማለቱን አስረድተዋል።

ወንዶች፣ ሴቶች እና ልዩነታቸው

ወንዶች እና ሴቶች አብረው ሲሠሩ ከፍተኛ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚችል የገለጹት አምባሳደር ኪያራ፥  ሴቶች በጾታቸው ላይ ተመሥርተው የተለየ አመለካከትን ሊያመጡ እንደሚችሉ ተናገረው፥ ሁላችንም አንድ ባለመሆናችን ሴቶችም እንደ ወንዶች ሁሉ የተለያዩ ውጤቶችን ማስመዝገብ እንደሚችሉ አስረድተዋል። “በዲፕሎማሲያዊ ሥራዎች አማካይነት አገራችንን እንወክላለን” የሚሉት አምባሳደር ኪያራ፥ ከዚህም ጋር ተያይዞ የአገራቸውን ገጽታ እንደሚወክሉ እና ይህም ልዩ ውጤቶችን በማስመዝገብ አኳያ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። አምባሳደር ኪያራ አክለውም በዓለም ዙሪያ ወንድ ዲፕሎማቶች ሁልጊዜ ሊደርሱ የማይችሏቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ሴት ዲፕሎማቶች መድረስ እንደሚችሉ በማስረዳት ከግጭት እና ከልማት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የብዝሃነትን አስፈላጊነት በማጉላት ሴቶች በዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት ተሠማርተው የሚሠሩ ከሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በመምራት እና የተጎዱትን ቶሎ በመድረስ ከፍተኛ ውጤቶችን ማምጣት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በዲፕሎማሲ ዘርፍ አገርን መወከል

በአውስትራሊያ ውስጥ የሚገኙ ብሔረሰቦች የተለያየ ገጽታን በአምባሳደርነት መወከል ማለት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉትን የበርካታ ሕዝቦች ድምጽ መወከል እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ኪያራ፥ ማለት ነው። አገራቸው አውስትራሊያ በዓለም ላይ እጅግ ጥንታዊ የሆነ እና ቀጣይነት ያለው የኑሮ ባሕል መገኛ እንደሆነች ተናግረው፥ በዚህ ወግ እና ባሕል እጅግ እንደሚኮሩ ገልጸዋል።

የአገራቸውን ቀደምት ብሔረሰብ ቅርሶች እና ባሕሎቻቸው በዓለም ዙሪያ እንዲታወቁ ማድረግ የውጭ ፖሊሲያቸው ዋና አካል እንደሆነ የገለጹት አምባሳደር ኪያራ፥ በዚህም ማንነትን መግለጽ እና የአገሬውን ነባር ተወላጆች ድምጾችን ወደ ዓለም መድረክ ማምጣት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጵጵስና ዘመናቸው ሁሉ በዓለም ዙሪያ ያሉ ተወላጆችን መብት መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባ ከፍተኛ ድምጽ በማሰማት ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።

በዚህ ረገድ ቅድስት መንበር እና አውስትራሊያ በጥሩ ሁኔታ አብረው እንደሚሠርሩ የተናገሩት አምባሳደር ኪያራ፥ ከጥቂት ሳምንታት በፊት በአውስትራሊያ ውስጥ የቀደምት ነዋሪዎች አባል የሆኑት የዕድሜ ባለጸጋ ሴት ወደ ቫቲካን ተጉዘው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸውን አስታውሰው፥ ከቅዱስነታቸው ጋር በነበራቸው ውይይትም ትምህርት፣ በአገር በቀል ጥበብ ላይ ያላቸው ልምድ እንቅፋቶችን ለማስወገድ በአውስትራሊያ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል ድልድይ ለመፍጠር ማገዙን ገልጸው፣ ይህን ጥረት የሚያግዙ በርካታ ውጥኖችም በሂደት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በዲፕሎማሲ ውስጥ የሴቶች የወደፊት ዕጣ

አምባሳደር ኪያራ በቅድስት መንበር ለዚህ ተግባር በመመረጣቸው የተሰማቸውን እርካታ ገልጸው፥ “ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በቅድስት መንበር ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ሴት አምባሳደሮች ጋር አብሮ መሥራት የሚያበረታታ እንደሆነ ገልጸዋል።

አታሼዎችን ጨምሮ ባሁኑ ወቅት ወደ 25 የሚጠጉ ሴት አምባሳደሮች ቡድንን በመፍጠር በኅብረት እየሠሩ እንደሚገኙ አምባሳደር ኪያራ ተናግረው፥ ይህ እውነታ ትልቅ የድጋፍ ምንጭ እንደሆናቸው እና በዚህም ሴቶች አድሎአዊ አመለካከቶችን መቃወም እንደቻሉ፣ ድምፃቸውን ለውይይት በማቅረብ እንደ ሴት መሪነታቸው የሚያመጡትን ልዩ ችሎታ እና አመለካከቶች በማጉላት መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። "ሴት አምባሳደሮች ለውይይት የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች እውቅናን እያገኙ እና እያደጉ የመጡ ይመስለኛል" ያሉት አምባሳደር ኪያራ፥ “ከዚህም በተጨማሪ አገራት በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ውስጥ ልዩነታቸውን መወከል እንዳለባቸው የተገነዘቡ ስለሆነ መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን አስባለሁ” ብለዋል።

በራስ መተማመን እና ግልጽነት 

በዲፕሎማሲ ሙያ መቀጠል ለሚፈልጉ ሴቶችም ሆነ ወንዶች ባስተላለፉት የማበረታቻ መልዕት፥ "እያንዳንዳችን ለውይይት በምናቀርባቸው ሃሳቦች ላይ ግልጽነት እንዲኖራቸው በማድረግ፣ መተማመን እና ዋጋ መስጠት ያስፈልጋል” ብለዋል። ገዳማውያት እህቶች በርካታ ርዕሠ ጉዳዮችን ለውይይት ሲያቀርቡ የጥበብ ቃላትን እንደሚጠቀሙ የተናገሩት አምባሳደር ኪያራ፥ በኅብረት ለመሥራት ችሎታ ሊኖር እንደሚገባ እና ለሌሎች ግልጽ መሆን እንደሚያስፈልግ በመናገር አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ተባብረን ካልሠሩ ለውጥን ማምጣት እና ሴቶችን ለመሪነት ደረጃ ማብቃት እንደማይቻል ተናግረው፣ ወንዶች በዚህ ላይ መሳተፍ እንዳለባቸው እና ድጋፋቸው ሁሉንም ሊጠቅም እንደሚችል በመግለጽ አስተያየታቸውን ደምድመዋል።

 

 

26 June 2023, 16:51