ፈልግ

የሲኖዶሳዊነት ዓርማ የሲኖዶሳዊነት ዓርማ  

ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን በሙሉ ከነልዩነታቸው ተቀብላ የምታስተናግድ መሆን አለባት ተባለ

የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት ወር 2023 እና 2024 ዓ. ም. በሮም ለሚካሄዱ ሁለት ምዕራፍ የጠቅላላ ጉባኤዎች መመሪያ የሚሆን የተግባር ሠነድ አዘጋጅቶ ይፋ አድርጓል። ይህ ሠነድ ቤተ ክርስቲያን ሰዎችን በሙሉ ከልዩነታቸው ጋር ተቀብላ የምታስተናግድ መሆን እንዳለባት አሳስቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ወደ ስድሳ የሚደርሱ ገጾች ያሉት የተግባር ሠነዱ በሁሉም የዓለማች ክፍሎች የሚገኙ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ያጋጠማቸውን የጦርነት ስቃይ፣ የአየር ንብረት ለውጥ መዘዞች፣ ብዝበዛን እና የኑሮ አለመመጣጠንን በማስከትል ላይ የሚገኝ የኢኮኖሚ ሥርዓት ልምዶችን ያካተተ እንደሆነ ተመልክቷል።  ምእመናን በሰማዕትነት የሚሰውባቸው ቤተ ክርስቲያናት፣ ዝቅተኛ የክርስቲያን ቁጥር በሚገኝባቸው አገሮች ውስጥ በምዕመናን ላይ የሚደርስ ስቃይ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን ስደት የሚገልጽ፣ በምዕመናኖቻቸው ላይ ፆታዊ ጥቃት ተፈጽሞባችው የቆሰሉ ቤተ ክርስቲያናት ታሪክ፣ ስልጣንን እና ህሊናን ያለ አግባብ በሚጠቀሙ ሰዎች በኩል በሚሰነዘር ጥቃት የተጎዱ ቤተ ክርስርቲያናት ታሪክን የያዘ ሠነድ እንደሆነ ታውቋል። 

Instrumentum laboris”  ወይም  “የተግባር ሠነድ” የሚል ስያሜ የተሰጠው እና በቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ማክሰኞ ሰኔ 13/2015 ዓ. ም. ጠዋት ይፋ የሆነው ሰነዱ፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 2023 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ተጀምሮ ከአንድ ዓመት በኋላ በሁለተኛው ምዕራፍ ጉባኤ በሚጠናቀቅ የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለሚሳተፉ አባላት የውይይት መሠረት እንደሚሆን ተነግሯል።

ለሲኖዶሳዊ ጉዞ መነሻ እንጂ መድረሻ እንዳልሆነ የሚነገርለት የተግባር ሠነዱ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “እንደ ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለማደግ ምን እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለብን ማወቅ ያስፈልጋን” ባሉት ጥሪ መሠረት፥ ከመስከረም 30/2014 ዓ. ም. ጀምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት በዓለም ዙሪያ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በየአገራቱ የሚገኙ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ተሞክሮዎቻቸውን ሲያሰባስቡ ቆይተዋል። የተግባር ሠነዱ፥ በጠቅላላው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ወቅት ውይይቶችን በማስተዋል ለማካሄድ እንዲያግዝ ተብሎ የተዘጋጀ መመሪያ ሲሆን፥ እንደዚሁም የጉባኤው ተሳታፊዎች አስቀድመው እንዲዘጋጁበት ለማድረግ የተሰናዳ እንደሆነ ታውቋል። የሲኖዶሱ ሂደት ዓላማ ቀደም ሲል ለአህጉራዊ መድረክ ላይ የተፃፈውን ሃሳብ በመድገም ሠነዶችን ለማዘጋጀት ሳይሆን የቤተ ክርስቲያኗን ተልዕኮ ለማሳካት የተስፋ አድማሶችን መክፈት መሆኑን የተግባር ሠነዱ አመልክቷል።

ማክሰኞ ሰኔ 13/2015 ዓ. ም. ይፋ የተደረገው የተግባር ሠነዱ የሲኖዶሳዊነት ጽንሰ-ሀሳብ ዕይታን የሚያሳዩ ገላጭ ጽሑፎችን እና አሥራ አምስት የተግባር ገጾች ያሉት እንደሆነ ተመልክቷል። የተግባር ሠነዱ ዋና ዋና ክፍሎች፤ በክፍል (1) ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የተሰበሰቡ የእግዚአብሔር ሕዝብ ልምዶችን በማጉላት ቤተ ክርስቲያን የበለጠ ሲኖዶሳዊት የምትሆንበትን መንገድ የሚያሳይ፣ ክፍል (2)  “ኅብረት፣ ተልዕኮ፣ ተሳትፎ” የሚለው ርዕሥ ቅድሚያ በሚሰጥባቸው ሦስት ጉዳዮች ላይ እነርሱም፥  ማንንም ወደ ጎን ሳይሉ ሁሉንም ሰው በመቀበል በኅብረት ማደግ፣ የምስጢረ ጥምቀት ጸጋን የተቀበለ እያንዳንዱ ምዕመን ከተልዕኮ አንጻር ለሚያበረክተው አስተዋፅዖ እውቅና እና ዋጋ መስጠት፣ ተልዕኮ ባላት ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በጊዜ ሂደት ተሳትፎን እና ስልጣንን ለመግለጽ የአስተዳደር መዋቅሮችን እና የለውጥ ኃይሎችን መለየት የሚሉ ርዕሦች ይገኙበታል።

እነዚህን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ይገባል ያለው የተግባር ሠነዱ፣ ቤተ ክርስቲያን በተቋማቷ፣ በአወቃቀሯ እና በአሠራር ሂደቷ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲኖዶሳዊት የመሆን ፍላጎት እንዳላት ያረጋግጣል። “ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያ ደረጃ የልጆቿን ድምጽ የምታዳምጥ፣ በትኅትና ይቅርታን መጠየቅ እና ብዙ መማር እንዳለባት የምታውቅ ናት” በማለት የተግባር ሠነዱ ገልጿል። የተግባር ሠነዱ ሲቀጥል፥ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በከባድ ቀውሶች እና ፈተናዎች ውስጥ እንደምትገኝ ገልጾ፥ ቀውሶቹ በብዙ መልኩ ከፆታዊ ጥቃት፣ ከስልጣን፣ ከገንዘብ እና ከህሊና አላግባብ ከመጠቀም ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ በመታገዝ እራሷን እንድታድስ የሚጠይቅ የሕሊና ምርመራን በማድረግ የእርቅ፣ የፈውስና የፍትህ መንገዶችን በሚከፍት የንስሐ ጉዞን ማድረግ እንዳለባት የተግባር ሠነዱ ያሳስባል።

ሲኖዶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን እና የእምነት ተቋማት፣ ባሕሎች እና ማኅበረሰቦች ጋር የምትገናኝበት የውይይት መድረኮችን ማበጀት ይኖርባታል ያለው ሠነዱ፥ ቤተ ክርስቲያን የአስተሳሰብ እና የባሕል ልዩነቶችን ጨምሮ በውስጧ ለያዘቻቸው ማንኛውም ዓይነት ልዩነቶች ሳትፈራ አንድ ወጥ እንዲሆኑ ሳታስገድድ ለሁሉም ዋጋን የምትሰጥ መሆን እንደሚገባ በማሳሰብ፥ ቤተ ክርስትያን ሲኖዶሳዊት መሆን የምትችለው በተለያዩ ቋንቋዎች እና ሥርዓቶች አማካይነት በየዕለቱ የምታቀርበውን ተመሳሳይ የአምልኮ ሥርዓቶችን ስትለማመድ መሆኑን ሠነዱ ገልጿል።

የቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥልጣኖችን የተመለከቱ ሌሎች የተግባር ሠነድ አንቀጾች፥ "በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስልጣን የሚመነጨው ዓለማዊ የሥልጣን ሞዴሎችን በመከተል ወይንስ በአገልግሎት ላይ የተመሠረተ ሥልጣንን መሠረት በማድረግ?" በማለት ጠይቆ፤ ሁሉ አቀፍ ትምህርቶችን ለእግዚአብሔር ሕዝብ በሙሉ በቀጣይነት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ በመጥቀስ፣ በሥርዓተ አምልኮ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በትምህርተ ክርስቶስ፣ በቅዱሳት ስነ ጥበባት፣ እንዲሁም ለምዕመናን እና ለሰፊው ሕዝብ የሚውል የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አገልግሎት ባሕላዊ እና ዘመናዊ የቋንቋ እና የጽሑፍ ዘዴዎችን በመጠቀም እና እነዚህን ሃብቶች በአግባቡ በመጠቀም ለዘመናችን ሰዎች በሙሉ ተደራሽ እና ማራኪ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ መሆን አለበት” በማለት ሠነዱ ያስገነዝባል። 

21 June 2023, 16:28