ፈልግ

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለባልካን አገራት ተወካዮች ንግግር ሲያደር ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለባልካን አገራት ተወካዮች ንግግር ሲያደር  

ካርዲናል ፓሮሊን በባልካን አገራት መካከል የግንኙነት ባሕልን ማጎልበት ይገባል አሉ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በስሎቬኒያ ውስጥ ካፖዲስትሪያ ከተማ ሰኔ 10/2015 ዓ. ም. በተካሄደው የሰላም እና የጋራ ውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል። ካርዲናል ፓሮሊን በንግግራቸው፥ የልዩ ልዩ ብሔረሰብ ሕዝቦች እና ሐይማኖቶች በሚገኙባቸው የባልካን አገራት መካከል የውይይት እና የሰላም ድልድይ መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በባልካን አገራት ተወካዮች መካከል በተካሄደው የአንድ ቀን የውይይት መድረክ ላይ የተገኙትን የስሎቬኒያውን ፕሬዚደንት እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርን፣ የአብያተ ክርስቲያናት እና የልዩ ልዩ እምነቶች ተወካዮችን ካመሰገኑ በኋላ፣ ስሎቬንያ የሕዝቦች መሸጋገሪያ እንደመሆኗ ለተለያዩ የዓለማችን ባሕሎች እና የባልካን አገራት ድልድይ መሆኗን ገልጸዋል።

የሰላም እና የውይይት ወሳኝነት

ካርዲናል ፓሮሊን ለውይይት መድረኩ ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፥ “በዩክሬን ያለውን ጦርነት እና በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ያለውን ውጥረት ስናይ ውይይት እና የሰላም ጥረቶች ወሳኝ ናቸው” በማለት ተናግረዋል።እነዚህን ጥረቶች በተለይም አሳዛኝ ጦርነት በሚካሄድባቸው የባልካን አካባቢዎች ውስጥ ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ ተናግረው፥ "በዘመናት ውስጥ በተለያዩ ጎሳዎች፣ ባሕሎች እና ሐይማኖቶች መካከል ያሉ በሰላም አብሮ የመኖር አስደናቂ ምሳሌዎችን መዘንጋት የለብንም" ብለዋል።

“በባልካን አካባቢ አገራት ውስጥ የባሕል እና የሐይማኖት ልዩነቶች እሴታዊ ሃብቶች ናቸው” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ እነዚህ እሴቶች በክልሉ በሚገኙ በርካታ የአብያተ ክርስቲያናት፣ የመስጊዶች እና የምኩራቦች የሥነ ሕንፃ ገጽታ በኩል እንደሚገለጹ አስረድተዋል።

የሰላም ፈጣሪዎች ለመሆን ተጠርተዋል

በማቴ. 5:9 ላይ፥ "ሰላምን የሚያወርዱ ብፁዓን ናቸው፤ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና" የሚለውን የጠቀሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ለዚህ ሁለንተናዊ ጠቅላላ ጥሪ ትኩረትን በመስጠት፥ በሠፊው የሰላም መድረክ መሳተፍ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል። ቅድስት መንበርም እንደ አንድ ሉዓላዊ እና ገለልተኛ ዓለም አቀፍ ተዋናይ ከማናቸውም ቁሳዊ ጥቅም የጸዳች፣ በክልሎች መካከል ያሉ ግጭቶችን ለማስታረቅ እና በተጣሉ ወገኖች መካከል እርቅ ለመፍጠር በሚቻላት ሁሉ የበኩሏን ጥረት በማድረግ ላይ እንደምትገኝ አስረድተዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1990ዎቹ ዩጎዝላቪያ ስትገነጠል በተዋናይ ወገኖች መካከል የሚደረገውን ያላሰለሰ ውይይት ለማበረታታት፣ አለመግባባቶችን ያለ ኃይል እርምጃ ለመፍታት እና በዩጎዝላቪያ ሕዝቦች መካከል በሰላም አብሮ የመኖር ባሕልን መልሶ ለማምጣት መልካም ጥረቶች ሲደረግ እንደ ነበር አስታውሰው፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በወቅቱ ለአማኞች እና ለሐይማኖት መሪዎች ባቀረቡት ጥሪ፥ በአዲሲቷ አውሮፓ ውስጥ በአንድነት ለመኖር የታቀደ የሰላም ድባብ እና በተለያዩ ሕዝቦች መካከል የግንኙነት ባሕልን በመፈለግ የውይይት እና የጋራ ተግባር እንዲጠናከር ደጋግመው ማሳሰባቸውንም አስታውሰዋል።

የግንኙነት ባሕል ለማሳደግ መሥራት

“ግጭቶች ሲከሰቱ እርስ በርስ ተገናኝቶ የመወያየት ባሕልን ማሳደግ ወሳኝ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በሐይማኖቶች መካከል የሚደረግ ውይይት ለሰላም ግንባታ አስፈላጊ መሆኑን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” የሚለውን ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በማስታወስ ተናግረዋል።ቅዱስነታቸው በሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳናቸው፥ "መቀራረብ፣ ራስን መግለጽ፣ መደማመጥ፣ እርስ በርስ ለመተዋወቅ እና ለመግባባት መሞከር እና አስታራቂ ነጥቦችን መፈለግ" እንደሚያስፈልግ መናገራቸውንም አስታውሰዋል። የጋራ ውይይቱ የላቲን እና የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ባሕልን እና እንዲሁም የእስልምና እምነት ባሕሎችን በሚከተሉ የባልካን አገራት የሰላም ጥረት ውስጥ አስፈላጊ መሆኑን ካርዲናል ፓሮሊን ጠቁመዋል።

የመገናኛ ድልድዮችን ማበጀት

“በሐይማኖቶች መካከል የሚደረግ የጋራ ውይይት በዓለማችን ውስጥ ወንድማማችነትን እና ሰላምን ለመፍጠር መንገድ ይከፍትልናል” በማለት ያከሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ይህም በሐይማኖቶች መካከል የሚታየውን የአክራሪነት ችግር ለመፍታት እንደሚረዳ፥ የጥል ግድግዳን ማቆም የሰላም ጥረቱን ፈታኝ እንደሚያደርገው ተናግረው፥ ሰላም ሕዝቦችን አንድ በማድረግ ኅብረት እንደሚፈጥር፣ ለውይይት እና ለትውውቅ በር እንደሚከፍት ጠቁመዋል።

የወንድማማችነት ጎዳና

ለሰላም እና ለጋራ ውይይት የተደረጉ በርካታ ጥረቶችን ያስታወሱት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ አውሮፓ የምትከተላቸው የሰላም እና የውይይት ጎዳናዎች መረጋጋትን በማጠናከር በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዘርፎች ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎችን ለማበረታታት ጥሩ ዕድል እንደሚሰጥ ጠቁመዋል። ቅድስት መንበርም ይህን ምኞት በመልካም እንደምትመለከተው እና በጽኑ እንደምትደግፈው ተናግረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አውሮፓን እንደ "የወንድማማችነት ጎዳና" እንደሚቆጥሩት እና “የዘመናዊ አውሮፓ መሥራች አባቶች ተነሳሽነት በማስታወስ በአውሮፓ ውስጥ ዘላቂ የሰላም መሠረት ለመጣል ጥረት ያደርጋሉ” ብለዋል።

 

19 June 2023, 13:08