ፈልግ

የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባ - C9 የካርዲናሎች ምክር ቤት ስብሰባ - C9 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከካርዲናሎች ምክር ቤት አባላት ጋር ስብሰባ በማካሄድ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

በቅድስት መንበር የካርዲናሎች ከፍተኛ መማክርት ሰኔ 19/2015 ዓ. ም. ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር በመሆን ስብሰባ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ። የአሁኑ ስብሰባ ባለፈው መጋቢት ወር በምክር ቤቱ አባላት መካከል ለውጥ ከተደረገ በኋላ የተካሄደ የመጀመሪያ ስብሰባ ቀጣይ እንደሆነ ተመልክቷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በተገኙበት ከሰኔ 19/2015 ዓ. ም. ጀምሮ በቫቲካን ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን ስብሰባ በማስመልከት የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል እንዳስታወቀው፥ በሂደት ላይ የሚገኘው ስብሰባው በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጎ ፈቃድ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2013 ዓ. ም. ተቋቋሞ የነበረው እና በኋላም ባለፈው መጋቢት ወር ለውጥ በተደረገበት ከፍተኛ የካርዲናሎች መማክርት መካከል የሚደረግ ስብሰባ መሆኑን አስረድቷል።

በሚያዝያ ወር የተካሄደው ስብሰባ

ባለፈው ሚያዝያ ወር ዘጠኝ አባላት የሚገኙበት ከፍተኛ የካርዲናሎች ምክር ቤት በጠራው ስብሰባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ማርኮ ሜሊኖ መሳተፋቸው ይታወሳል። በስብሰባው ላይ ተነስተው ውይይት ከተደረጉባቸው የተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች መካከል በብዙ የዓለማችን ክፍሎች እየተካሄዱ የሚገኙ ጦርነቶች እና ግጭቶች፣ በመጭው ጥቅምት ወር 2016 ዓ. ም. ለሚካሄድ የቅዱስ ሲኖዶስ ጠቅላላ ጉባኤ ከሚደረግ ቅድመ ዝግጅት በተጨማሪ በምድራችን ውስጥ ሰላምን ለማምጣት መላው ቤተ ክርስቲያን ተባብሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጋቢት 19/2022 ዓ. ም. ይፋ የተደረገው እና “ወንጌልን ለአህዛብ ስበኩ” በሚል አርዕሥት ይፋ የሆነው ሐዋርያዊ ሕግ ተገባራዊ በሚሆንበት መንገድ ውይይት መካሄዱ ይታወሳል።  

በመጋቢት ወር የተካሄደው የአዲስ አባላት ምርጫ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ መጋቢት 7/2023 ዓ. ም. በተካሄደው ከፍተኛ የካርዲናሎች ስብሰባ ላይ የአዲሱ ምክር ቤት አባላት የተመረጡት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒትሮ ፓሮሊን፣ የቫቲካን ግዛት አስተዳደር ጳጳሳዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና የቫቲካን ከተማ ጠቅላይ አስተዳዳሪ ብጹዕ ካርዲናል ፌርናንዶ ቬርጌዝ አልዛጋ፣ በዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኮንጎ የኪንሻሳ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ፍሪዶሊን አምቦንጎ ቤሱንጉ፣ በሕንድ የቦምቤይ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ኦስቫልድ ግራሲያስ፣ በሰሜን አሜሪካ የቦስተን ከተማ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሲን ፓትሪክ ኦማሌይ፣ በስፔን የባርሴሎና ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሁዋን ሆሴ ኦሜላ ኦሜላ፣

በካናዳ የኪቤክ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ጄራልድ ላክሮክስ፣ የሉክሰምበርግ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዣን ክላውድ ሆሌሪች፣ በብራዚል የሳን ሳልቫዶር ደ ባሂያ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ ካርዲናል ሴርጆ ዳ ሮቻ እና የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊው ሆነው የተመረጡት ሞንሲኞር ማርኮ ሜሊኖ እንደነበሩ ይታወሳል።

ምክር ቤት የተቋቋመበት ዓላማ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከመስከረም 28/2013 ዓ. ም. ጀምሮ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጸደቀው ሠነድ፥ ምክር ቤቱ ዓለም አቀፋዊት በሆነች የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ማገዝ፣ የሮም ቤተ ክርስቲያን የካርዲናሎች መማክርት የሚያቀርቧቸውን ፕሮጄክቶች ማጤን እና “ወንጌልን ለአህዛብ ስበኩ” በሚል አርዕሥት ይፋ የሆነው ሐዋርያዊ ሕግ ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድ ማመቻቸት የሚሉ ርዕሦችን የያዘ ሰነድ እንደሆነ ታውቋል።

ዘጠኝ ካርዲናሎች የሚገኙበት አዲሱ ምክር ቤት የመጀመሪያውን ስብሰባ ያካሄደው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥቅምት 1/2013 ዓ. ም. እንደ ነበር ይታወሳል።

27 June 2023, 16:23