ፈልግ

ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ ጉባኤ ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ ጉባኤ 

የቤተ ክርስቲያን እና የድርጅት መሪዎች በንግድ ሥነ-ምግባር መርሆዎች ላይ ተወያዩ

ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚ በንግዱ ዘርፍ የሥነ-ምግባር መርሆዎችን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል የሚያግዝ ከፍተኛ ጉባኤ ተካሂዷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የንግድ ድርጅት እና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፣ ምሁራን እና የተቋማት ባለድርሻ አካላት የተካፈሉበት ከፍተኛ የንግድ ሥነ-ምግባር ጉባኤ በቫቲካን ጳጳሳዊ ሳይንስ አካዳሚ ውስጥ ዓርብ ሰኔ 2/2015 ዓ. ም. የተካሄደ ሲሆን፥ የጉባኤው ዓላማ የሥነ ምግባር እና የሞራል መርሆችን በኮርፖሬሽኖች አካባቢ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ለመወያየት ነው።

ጉባኤው አካባቢን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና ወቅታዊ የሆኑ ማኅበራዊ ጉዳዮችን በተመከተ የንግዱ ዓለም በሚወስዳቸው ውሳኔዎች፥ ሥነ-ምግባር ማበርከት በሚችልባቸው መረጃዎች ላይ ተወያይቷል።ውይይቱ በአራት ዋና ዋና ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ የተካሄደ ሲሆን፥ እነርሱም የሰው ሃብት፣ የቴክኖሎጂ ሃብት፣ የአየር ንብረት ሃብት እና የተፅዕኖ ሃብት እንደነበሩ ተመልክቷል። በዚህ መሠረት አካዳሚው በሰው ሠራሽ አስተውሎት አማካኝነት የሰውን ልጅ ባማከለ መልኩ የሥነ-ምግባር መርሆዎችን ወደ ንግዱ ዓለም ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን የሚያጎላ ውይይት ለተሳታፊዎች አቅርቧል።

የፍልስፍና መሠረት ያለው የንግድ ሥነ-ምግባር

ሮም በሚገኝ የላተራን ጳጳሳዊ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ዲን የሆኑት አባ ፊሊፕ ላሬይ፥ በጉባኤው ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ሰዎችን - ፖለቲከኞችን፣ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎችን፣ ፕሮፌሰሮችን እና ሥራ ፈጣሪዎችን ለማሳተፍ መሞከራቸውን ተናግረዋል። "የንግድ ሥነ-ምግባር የንግድ ዓለም መርሆዎች መሠረት በማድረግ ትክክለኛውን እና የተሳሳተውን  የምንረዳበት መንገድን ነው” ብለው፥ “ከሞላ ጎደል ሁሉም ሰው ስህተትን ከመሥራት ተቆጥቦ መልካም ማድረግ እንደሚገባ ቢስማማም ነገር ግን ትክክል እና ስህተት በሆነው ነገር ላይ ሁልጊዜ የማይስማማ በምሆኑ ከፍልስፍና አንፃር የተለያዩ ማዕቀፎችን ለመመልከት ሞክረናል” ብለዋል።

የሰው ልጅን ማዕከል ማድረግ

ጉባኤውን ከተካፈሉት እንግዶች መካከል አንዱ የሆኑት ስኮት ኦ’ኔል፥ የጉባኤው የመጀመሪያ ቁልፍ ርዕስ መሠረት በማድረግ በሰጡት አስተያየት፥ "በሰው ልጅ ኢኮኖሚ ውስጥ ንግድ ለውጥ ለማምጣት እና ውድድር ለማካሄድ ቁልፍ የሆኑ ዋና ዋና ክንውኖች ማድረግ አለበት” ብለዋል። በማያያዝም የንግድ መሪዎች እና ሥራ አስፈፃሚዎች ከአካባቢ መንግሥታት ጋር በመተባበር መሥራት እንዳለባቸው እና በጋራ መፍታት ያሉባቸው እውነተኛ ችግሮች በመኖራቸው በዚህም የንግድ ድርጅቶች ከፍተኛውን ሚና መጫወት እንደሚችሉ ገልጸው፥ በኤኮኖሚው ሰዎችን ማዕከል የማድረግ አስፈላጊነት እና ይህም ለንግዱ ዓለም መልካም እንደሆነ ተናግረዋል። በአሁኑ ጊዜ የቢዝነስ መሪዎች በእምነታቸውና በእሴቶቻቸው ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተናግረው፣ የሚያጋጥሟቸው ጥያቄዎች መልካም ባሕሎችን እና ምቹ መድረኮችን ለመፍጠር እንደሚገፋፏቸው ጠቁመዋል።

ከሌሎች እየተማሩ ወደፊት መጓዝ

ከጉባኤው አስተባባሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ወ/ሮ ክርስቲያና ፋልኮኔ፥ የጳጳሳዊ ሳይንስ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ብፁዕ ካርዲናል ፒተር ተርክሰን “ጥሩ ሃብት፣ ጥሩ ፕላኔት፣ ጥሩ ሰዎች” ያሉት ሃሳብ ጥልቅ እና እራሳችንን እንድንጠይቅ የሚያስታውሰን ነው” ብለው፥ “ይህ መልካም ነበር? ይህ ትክክል ነበር? የሚሉት ጥያቄዎች የረሳናቸው ነገር ግን መሠረታዊ የሥነ ምግባር ጥያቄዎች ናቸው” ብለዋል።

ጉባኤው ስለሚሰጠው ተስፋ የተጠየቁት ወ/ሮ ክርስቲያና ሲመልሱ፥ በተሳታፊዎች መካከል ያለው መስተጋብር ከጉባኤው ዋና ዋና ውጤቶች መካከል አንዱ ነበር ገልጸው፥ “የጉባኤው ተካፋዮች ከውይይቱ በጥቂቱም ቢሆን መማር መቻላቸው ወይም የማያውቁትን አውቀው መመለሳቸው እና ከዚያም ሙከራዎችን በማድረግ የበለጠ እንዲማሩ መታገዛቸው የጉባኤው ውጤቱ እንደሆነ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

ወ/ሮ ክርስቲያና አክለውም በጉባኤው ላይ ውይይት የተካሄደባቸው አራት ጥናቶች በ “LUMSA” ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲ ለሚማሩ ተማሪዎች ለውይይት እንደሚቀርቡ ገልጸው፥ ዛሬ በአመራር ላይ ያለው ትውልድ እና ውሳኔ ሰጪዎች ውድቀታቸውን ወይም ስኬታቸውን ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ” በማለት ተናግረዋል።

 

14 June 2023, 14:32