ፈልግ

2023.05.17 Udienza pellegrini tedeschi

ቫቲካን፣ ፍጥረታትን ከጉዳት ለመጠበቅ መዋዕለ ንዋይን የማፍሰስ አስፈላጊነት መኖሩን አስታወቀ

በቫቲካን የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ መስከረም 16/2016 ዓ. ም. የሚከበረው የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ቀን መልዕክት ይፋ አድርጓል። ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ በዓመታዊ መልዕክቱ፣ ተፈጥሮ የእምነት ምስክር እንዲሆን እግዚአብሔር በአደራ የሰጠን በመሆኑ ለዘላቂነቱ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ማሳደግ እንደሚገባ አሳስቧል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፍጥረትን ለመንከባከብ ልዩ ተነሳሽነትን መወሰድ የምትፈልግበት ጊዜ በመሆኑ፣ በዚህ ዓላማም የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ አስተምህሮም ለሰው ልጅ ሕይወት አስፈላጊ በመሆኑ ይበልጥ ውጤታማ እና አወንታዊ በሆነ መንገድ ሊከናወን ይገባል” በማለት በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ መስከረም 16/2016 ዓ. ም. የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን ምክንያት በማድረግ ይፋ ባደረጉት መልዕክት ገልጸዋል።  

የ2016 ዓለም አቀፍ ቀን ያዘጋጀው በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት ሲሆን፣ ዓላማውም ለሰው ልጅ ዕድገት፣ ለምድራችን እንክብካቤ እና ብልጽግናን ለማምጣት የሚያግዙ በርካታ የተሻሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች መኖራቸውን ለማጉላት እንደሆነ ተጠቅሷል። የድርጅቱ ሌላው ዓላማ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ መንግሥታት፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የልማት አጋሮች እና የግሉ ሴክተር ባለሃብቶች በአዲሱ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ስትራቴጂ ዙሪያ በመተባበር ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ጥሪ ለማቅረብ እንደሆነ ታውቋል።

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ ዓርብ ግንቦት 18/2015 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት መልዕክታቸው፣ በዓለም ውስጥ ወንጌልን ለማሰራጨት የሚረዱ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ፍጥረትን ለመንከባከብ ልዩ ተነሳሽነት እና ዘላቂ የመዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ሊኖር እንደሚገባ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል። በማከልም ፍጥረትን ለመንከባከብ መዋዕለ ንዋይን በዘላቂነት ማፍሰስ የእምነት ምስክርነት አካል እንደሆነ ገልጸው፣ ይህም እግዚአብሔር በአደራ የሰጠን ተፈጥሮን በማክበር ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተዋል።

ሰብዓዊ ክብርን ማሳደግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በዋናነትም፣ በአጭር ጊዜ ሳይሆን በረጅምና ዘላቂ ጥቅም ላይ በማተኮር፣ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው የሰውን ልጅ ክብር በዘላቂነት ማሳደግ እንዳለበት አሳስበው፣ "የሥነ ምግባር የበላይነት በትርፍ ጥማት ጀርባ ሊደበቅ አይችልም" ብለዋል። ፖለቲካውም አዳዲስ መንገዶችን በመፍጠር፣ በጋራ ጥቅም ላይ ያተኮሩ እና ሕይወትን ወደ ተሻለ ጀረጃ የሚያደርሱ ተገቢ ፕሮጀክቶችን በተለይም ከማኅበረሰቡ የተገለሉን የሚደግፍ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

ባሕላዊ እና መንፈሳዊ እሴሮችን ማሳደግ እና መንከባከብ

የሥነ-ጥበብ እና የባሕል እሴቶች ተጠብቀው ሊቆዩ እንደሚገባ ያሳሰቡት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ ሥነ-ጥበብ እና ባሕል ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያውቁ ከመረዳት በተጨማሪ ክርስቲያናዊ መሠረታቸውም ቀጣይነት እንዲኖረው ያስችላቸዋል” ብለዋል። “ውበትን በሚገልጹበት የሥነ-ጥበብ መንገድ ወንጌልን ማወጅ እና የምዕመናንን መንፈሳዊነት ማሳደግ የተልዕኳችን ዋና አካል ነው” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፣ ባሕላዊ የሆኑ የጥበብ ሥራዎችን መጠበቅ የሁላችን ግዴታ እና ሃላፊነት ነው" ብለዋል።

ኃላፊነት ያለው ቱሪዝም እና ለምድራችን የሚደረግ እንክብካቤ

በመጨረሻም በቱሪዝም እና በፍጥረታት እንክብካቤ መካከል ያለውን ግንኙነት የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ፥ "የሰውን ልጅ እና አካባቢውን የሚያከብር ቱሪዝም በፍቅሩ ሁሉንም የሚያካትት የእግዚአብሔርን መልካምነት ለማወቅ መንገድ ይከፍታል" ብለዋል። በዚህም ረገድ በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ ሠራተኞች ልዩ የቱሪዝም ዓይነቶች መኖራቸውን ለማስተዋወቅ ዕድል እንዳላቸው ገልጸው፣ ይህም “ለሰው ልጅ እና ለተፈጥሮ የበለጠ ድጋፍ በመስጠት፣ የፍጆታ መጠንን በመቀነስ ተፈጥሮን ይበልጥ ለማክበር እና ውበቱንም በተለያዩ መንገዶች ለመግለጽ የሚረዳ የማሰላሰል ችሎታ ያለው ነው” በማለት አስረድተዋል።

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ሃላፊው ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በመጨረሻም፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. የሚከበረውን የኢዮቤልዩ በዓል ባስታወሱበት መልዕክታቸው፣ ተፈጥሮን መንከባከብ እና የወደ ፊት ጊዜን በጋራ የመገንባት ተስፋን አጥብቆ መያዝ ለመጪው የኢዮቤልዩ በዓል ዝግጅት ሊሆን እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። 

29 May 2023, 15:41