ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአፍሪካ ውስጥ ከ “ስኮላስ ኦኩራንቴስ” አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአፍሪካ ውስጥ ከ “ስኮላስ ኦኩራንቴስ” አባላት ጋር በተገናኙበት ወቅት 

‘ስኮላስ’ የተሰኘ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ኮንግረስ እንደሚያዘጋጅ ተገለጸ

“ስኮላስ ኦኩራንቴስ” በመባል የሚታወቅ ጳጳሳዊ ፉንስዴሽን የምሥረታውን አሥረኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የመጀመሪያውን ዓለም አቀፍ ጉባኤን ሊያካሂድ መዘጋጀቱ ታውቋል። በተለያዩ የትምህርት ማዕከላት መካከል ግንኙነትን በመፍጠር ወጣቶችን የሚሰበስብ ‘ስኮላስ’ የተሰኘ ጳጳስዊ ፋውንዴሽን ከላቲን አሜሪካ የልማት ባንክ ጋር በመተባበር በላቲን አሜሪካ እና በአውሮፓ የሚገኙ የ50 ከተሞች ከንቲባዎችን የሚያሳትፍ የመጀመሪያውን ጉባኤ ከግንቦት 15-17/2015 ዓ. ም. ለማካሄድ አቅዷል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ስኮላስ” የተባለ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽኑ ዓርብ ግንቦት 11/2015 ዓ. ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከግንቦት 15-17/2015 ዓ. ም. ድረስ የሚካሄድ ጉባኤ ማዘጋጀቱን አስታውቋል። ፋውንዴሽኑ በመግለጫው፣ በ “ስኮላስ” በኩል የሚዘጋጀው የትምህርት ዘዴ ዘላቂ ዕድገትን ከተለያዩ ማኅበረሰቦች በተውጣጡ ወጣቶች ተሞክሮ በመታገዝ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” በሚለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቃለ ምዕዳን ውስጥ በተጠቀሰው “ሁሉ አቀፍ ሥነ-ምሕዳር” በሚለው ሃሳብ ላይ መሠረት ያደረገ መሆኑ ገልጿል። ጉባኤውን የሚካፈሉ የ50 ከተሞች ከንቲባዎች ባለፈው ዓመት በተዘጋጀው የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” ጉባኤ ላይ ወጣቶች የቀሰሙት ልምድ ቀጣይነት እንዲኖው ለማድረግ እና ዕውቀቱን በየክልላቸው ተግባራዊ የሚያደርጉበትን ስልጠናን ያገኛሉ።

የጉባኤው ማጠቃለያ ሮም በሚገኝ ቅዱስ አጎስጢኖስ ተቋም ውስጥ ግንቦት 17/2015 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በዘጠኝ ሰዓት በድምቀት እንደሚከናወን ታውቋል። በጉባኤው ማጠቃለያ ዕለት ከንቲባዎች እና ታዋቂ ባለሙያዎች በ 10ኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ ተገኝተው የጉባኤውን ሃሳብ የያዘ ሠነድ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀርባሉ። በሥነ-ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአርጀንቲና፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በሜክሲኮ እና በኮሎምቢያ አማዞን ግዛት ውስጥ ከሚገኙት የ “ስኮላስ ኦኩራንቴስ” ፋውንዴሽን ወጣቶች ጋር በቀጥታ ይገናኛሉ። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም በስፔን ውስጥ ከሚገኘው እና የትምህርት ፕሮግራም አካል ከሆነው “አብሮ መሆን” ከተሰኘ የአረጋውያን እና የወጣቶች ቡድኖች ጋርም ይገናኛሉ።

“ስኮላስ ኦኩራንቴስ” በመባል የሚታወቀው ጳጳሳዊ ፉውንዴሽን በዓለም ዙሪያ ከ400 ሺህ በላይ የሚሆኑ የትምህርት ማዕከላትን በማዋሃድ፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ህጻናትን እና ወጣቶችን በመድረስ በ190 አገራት ውስጥ የሚገኝ ኔትወርክ ሲሆን፣ ተልዕኮው እስር በርስ የመገናኘት ባህልን ለመፍጠር እና ወጣቶችን በአንድነት ሰብስቦ ትምህርት በመስጠት ጥሪውን ለመመለስ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን ነው።

 

22 May 2023, 16:17