ፈልግ

የሥነ-ሕይወት ምርምር ጳጳሳዊ አካዳሚ ወርክሾፕ ተሳታፊዎች ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ሲገናኙ የሥነ-ሕይወት ምርምር ጳጳሳዊ አካዳሚ ወርክሾፕ ተሳታፊዎች ከር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ጋር ሲገናኙ  (Vatican Media)

ቫቲካን በግጭት ምክንያት ለሚፈጠር የምግብ እጥረት መፍትሄዎችን እንደምትፈልግ ተገለጸ

በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ምርምር ጳጳሳዊ አካዳሚ በምግብ ዋስትና እና ሰብዓዊ ቀውስ ዙሪያ የተወያየ ዓለም አቀፍ ወርክሾፕ ተካሂዷል። የወርክሾፑ ተሳታፊዎች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በተለያዩ ግጭቶች እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ምክንያት ለተጎዱት ሰዎች ላደረጉት ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ምግብ እና ሰብዓዊ ቀውስ፣ ግጭቶችን ለመከላከል እና የምግብ ዋስትና እጦትን ለመቅረፍ የሚያግዙ ሳይንሳዊ ምርምሮች እና ፖሊሲዎች” በሚል ርዕሥ በአካዳሚው ዋና ማዕከል ሲካሄድ ቆይቶ ረቡዕ ግንቦት 2/2015 ዓ. ም. የተጥናቀቀውን የሁለት ቀናት ወርክሾፕ ያዘጋጀው በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ እንደሆነ ታውቋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከረቡዕ ዕለት ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮአቸው ቀደም ብለው የወርክሾፑን ተሳታፊዎች ተቀብለው ባሰሙት ንግግር፣ በተለይም በጦርነት ጊዜ እና በዩክሬን ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት የምግብ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ጥረቶች እንዲጨምሩ ጠይቀዋል።

  በተባበሩት መንግሥታ የምግብ እና እርሻ ድርጅት ተባባሪነት የተዘጋጀው ይህ ወርክሾፕ የምግብ ዋስትናን በሚመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮች ዙሪያ ባለፉት ጊዜትም በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚ አዘጋጅነት ሲያካሂድ ቆይቷል። ከዚህ በፊት የተካሄዱ ወርክሾፖች ዘላቂ የምግብ ሥርዓትን ለማደራጀት የሚያግዙ የሳይንስ እና የፈጠራ ሥራዎች እና በተባበሩት መንግሥታት የምግብ ሥርዓት ዝግጅት” በሚል ርዕሥ ከሚያዝያ 13-14/ 2013 ዓ. ም.፣ እንዲሁም “የምግብ ውድመት እና ብክነት ቅነሳ” በሚል ርዕሥ ከኅዳር 1-2/2012 ዓ. ም. ወርክሾፖች መካሄዳቸው ይታወሳል።

ከዚህም በላይ በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ጥናት ጳጳሳዊ አካዳሚው ከአየር ንብረት ለውጥ እና ከብዝሃ ሕይወት ጋር የተገናኙ ወርክሾፖችን እንዲሁም በባዮ ሳይንስ ውስጥ ፈጠራዎችን የሚያብራሩ ወርክሾፖችን አካሂዷል። እነዚህ የተለያዩ ዝግጅቶች ለምግብ ሥርዓት እና ዋስትና ትኩረት የሰጡ ሲሆን፣ የእነርሱ ግኝቶች በዚህ ሳምንት ውስጥ በተካሄደው ወርክሾፕ ጽንሰ-ሀሳብ ላይ ጠቃሚ ዳራዎች እንዲኖሩ አስተዋጽኦን አድርጓል።

የወርክሾፑ ተሳታፊዎች ምላሽ

ለቫቲካን የዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የገለጹት የወርክሾፑ ተሳታፊዎች፣ የሮክፌለር ፋውንዴሽን የምግብ አቅርቦት እና ተነሳሽነት ዋና ዳይሬክተር እና ሮም በሚገኝ የተባበሩት መንግሥታት የቀድሞ የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ካትሪን ቤርቲኒ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጉዳዩ የሰጡትን ትኩረት አድንቀው በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

"በዓለም ዙሪያ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የበለጠ ጉዳዩን በግብረገብ ደረጃ ወስዶ የሚናገር ማንም የለም" ብለው፣ ቅዱስነታቸው ሰብዓዊ ዕርዳታዎችን ለማሳለጥ ዘዴዎችን እና ማሻሻያዎች ለማበጀት ፍላጎት እንዳላቸው፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደሚፈልጉ፣ በሴቶች እና በሕጻናት ሚና ላይ ፍላጎት ያደረቸው መሆኑን እና ዓለምን ወደ መልካም ለመለወጥ እነዚህን ሰዎች መድረስ እንደሚያስፈልግ መመኘታቸውን ወ/ሮ ካትሪን ቤርቲኒ ተናግረዋል።

ወ/ሮ ካትሪን ቤርቲኒ አክለውም ፣ “የቅዱስነታቸው ሳይንሳዊ አማካሪዎች ወደፊት ሊወሰድ እና ሁላችንም ምን ማድረግ እንዳለብን ምክሮችን በመስጠት ዓለምን እያሰባሰቡ ከሆነ ይህ ለጠቅላላው ሂደት በጣም አስፈላጊ እና በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ለውጥ የሚያያመጣ መሆኑን አስረድተዋል።

የቀውሶቹ መነሻ

የኢትዮጵያው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እና በአዲስ አበባ የኃይለማርያም እና የሮማን ፋውንዴሽን ሊቀመንበር የሆኑት ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚህ ሳምንት ውስጥ በቫቲካን ያካሄዱት ወርክሾፕ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደሆነ ገልጸው፣ “በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፋዊ ቀውስ የሆነውን የምግብ እና የሰብዓዊ ቀውስ ጉዳይን በጋራ በማራመድ ትልቅ ዕድገት ማምጣት እንችላለን” ብለዋል።

ለቫቲካን የዜና አገልግሎት እንደገለጹት፣ “የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ሁከትና ብጥብጥ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ለቀውሱ መንስኤ እንደሆኑ፣ ለችግሩ መፍትሄን ለመስጠት የዓለም መሪዎች እንዲተባበሩ በመጠየቅ፣ አብዛኛዎቹ የምሥራቅ፣ የምዕራብ፣ የሰሜን እና የደቡብ አፍሪካ ሀገራት በግጭት ምክንያት በሚፈጠር የምግብ ዋስትና እጦት እየተሰቃዩ ስለሚገኙ መሪዎቻችን መፍትሄ እንዲሰጡን እና የጦር መሣሪያዎችን ድምጽ ጸጥ እንዲያደርጉ እንፈልጋለን” ብለዋል።

በሱዳን እየደረሰ ያለ ውድመት

በሱዳን መዲና ካርቱም የሚገኝ የጳጳሳዊ ሳይንስ አካዳሚ አባል እና የብሔራዊ ሳይንስ አካዳሚ (SNAS) ፕሬዚዳንት የሆኑት ክቡር አቶ መሐመድ ሐሰን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት፣ በእነዚህ ጭብጦች ዙሪያ የቫቲካን የሥነ-ሕይወት ምርምር ጳጳሳዊ አካዳሚው ከዚህ በፊት ባዘጋጃቸው በርካታ ወርክሾፖች መሳተፋቸውን አስታውሰው፣ የዛሬው ዎርክሾፕ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል። ጳጳሳዊ የሳይንስ አካዳሚው በግጭት ወቅት የሚያጋጥም የምግብ እና የስደተኞችን ቀውስ አስመልክቶ ስብሰባ ሲያዘጋጅ ይህ የመጀመሪያው እነደሆነ ተናግረው፣ የወርክሾፑ ተሳታፊዎች ከልዩ ልዩ የዓለማችን ክፍሎች እና የአስተሳሰብ ልዩነቶች ዙሪያ መምጣታቸው እንዳስደሰታቸው፣ “ያቀረቧቸው አስተያየቶች ለተሳታፊዎች ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የሚጠቅሙ ናቸው" ብለዋል።

አቶ መሐመድ ሐሰን ለቫቲካን የዜና አገልግሎት በሰጡት አስተያየት፣ በወርክሾፑ የተነሱ ርዕሠ ጉዳዮች እጅግ በጣም ወሳኝ እንደሆኑ፣ ስለ ቀውሶች ሲነሳ በተለምዶ ስለ አየር ንብረት ለውጥ፣ ስለ ብዝሃ ሕይወት መጥፋት እንጂ ስለ ጦርነት፣ ስለ ውስጥ ግጭቶች እና በታጣቂ ቡድኖች መካከል በሚከሰቱ ግጭቶች ላይ ትኩረት እንደማይሰጥ ገልጸው፣ በገዛ አገራቸው ሱዳን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ግጭት እጅግ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል።

በሳምንቱ ውስጥ የተሳተፉበት ይህ ወርክሾፕ በሳይንስ አካዳሚው አስተባባሪነት የተዘጋጀ በመሆኑ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራን አስፈላጊነት በማጉላት የተቻላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን እና የተሰጡት ገለጻዎችም ገንቢ እንደነበሩ አቶ መሐመድ ሐሰን ተናግረው፣ ከዚሁ ጎን ለጎን በአገራቸው ሱዳን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ግጭት ፖለቲካዊ እርምጃን እና ፍላጎትን የሚሻ መሆኑን አስረድተዋል። ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መገናኘታቸው እንዳስደሰታቸው የገለጹት አቶ መሐመድ ሐሰን፣ ግጭቶችን የመቀነስ ዘዴዎችን እና መንገዶችን በተመለከተ፣ በአጠቃላይ ስለ ጦርነቶች የተናገሯቸው ጠንካራ ቃላቶች፣ ግጭቶች ለብዙ ሰዎች ሕይወት እና ለአገር ሃብት ምን ያህል አደገኛ እንደሆኑ ላቀረቡት ገለጻዎች አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ማትኮር

በቫቲካን የሥነ-ሕይወት ምርምር ጳጳሳዊ አካዳሚ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ዮአኪም ቮን ብራውን፣ ለዎርክሾፑ ተሳታፊዎች ሰላምታን ካቀረቡ በኋላ የሰብዓዊ እና የምግብ ቀውስን በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፣ ተሳታፊዎቹ እንደ ኮንጎ እና ሱዳን በመሳሰሉ፣ በዓረቡ ዓለምም እንደ ሶርያ እና የመን እንዲሁም በአፍጋኒስታን ውስጥ የሚታዩ ቀውሶችን የሚያጠኑ ብቻ ሳይሆን የሚፈቱም ጭምር በመሆናቸው የተሰማቸው ደስታ ገልጸዋል።

“የወክሾፑ ዋና ትኩረት መፍትሄዎችን ማፈላለግ ነው” የሳይንሳዊ አካዳሚው ፕሬዚደንት ዮአኪም ቮን ብራውን፣  “ዓላማውም ሃሳብ መለዋወጥ ብቻ ሳይሆን መዋዕለ ንዋይን የት እና በምን ላይ ማፍሰስ እንደሚገባ፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሥርዓቱን እንዴት ማጠናከር እንደሚቻል የመፍትሔ አቅጣጫዎችን መለየት እና የወርክሾፑ ታዳሚዎች ረቡዕ ግንቦት 2/2015 ዓ. ም. ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ያደረጉት ትኩረትም ይህ ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በግጭት ወቅት የስደተኞችን ችግር ለመፍታት አዲስ መንገድ መፍጠር ቁልፍ ሚና እንዳለው መናገራቸውን አስታውሰው፣ ከማኅበረሰቡ የተገለሉ ሴቶች እና የአገሬው ነባር ተወላጆች ጉዳዮችን መፍታት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን እና ሰላም ከሌለ ቀውሱ ሊፈታ ስለማይችል በሰላም ግንባታ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት መስጠታቸውን ተናግረዋል።

11 May 2023, 17:07