ፈልግ

2023.05.24 Padre Corrado Maggioni, presidente del Comitato dei Congressi Eucaristici

በኤኳዶር የሚካሄደው የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ለአገሪቱ የተስፋ ምልክት እንደሚሆን ተገለጸ

የዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ጳጳሳዊ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አባ ኮራዶ ማጆኒ፣ ከጳጉሜ 3/2015 - መስከረም 4/2016 ዓ. ም. ድረስ በኪቶ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ እንደሚካሄድ ገለጸው፣ ጉባኤው መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በማበረታታት ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በአገሪቱ የምታቀርበውን የወንጌል ስርጭት አገልግሎት በድጋሚ እንድታጤን የሚያግዛት መሆኑንም አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በላቲን አሜሪካ አገር ኤኳዶር ሊካሄድ የታቀደው ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ፣ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ የሚገኝ የአገሪቱ ሕዝቦች እና ቤተ ክርስቲያን መካከል ወንድማማችነትን እና መልካም ተስፋን  ለማምጣት ያለመ መሆኑን አባ ኮራዶ የገለጹ ሲሆን፣ የጉባኤው አስተባባሪዎች የበዓሉን ዓርማ እና መዝሙር በማዘጋጀት ግንቦት 16/2015 ዓ. ም. በቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል በኩል ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።

የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ ከቡዳፔስት ወደ ኤኳዶር

አባ ኮራዶ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በሃንጋሪ መዲና ቡዳፔስት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2021 ዓ. ም. የተካሄደው ያለፈው ዓለም አቀፍ የቅዱስ ቁርባን ጉባኤ በሚቀጥለው ዓመት በኤኳዶር እንዲደረግ የተመረጠበት ምክንያት፥ አገሪቱ በልበ ኢየሱስ ስም የተቀደሰችበት 150ኛ ዓመት  በዓል ጋር የተያያዘ መሆኑን አብ ኮራዶ አስረድተዋል፣ በማከልም የኤኳዶር ብጹዓን ጳጳሳት የቅዱስ ቁርባን ጉባኤው መንፈሳዊ ኃይልን በመጨመር ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአገር እና ከአገር ውጭ የምታቀርበውን የወንጌል ስርጭት አገልግሎቷን በድጋሚ በማጤን ምስክርነቷን የምታጠናክርበት መንገድ እንደሚያመቻችላት ማሰባቸውን አባ ኮራዶ ገልጸዋል።

በወንድማማችነት ጭብጥ ላይ ያተኮረ

የጉባኤው ጭብጥ፥ “ዓለምን የሚፈወስ ወንድማማችነት” የሚል እና ኢየሱስ ክርስቶስም፥ “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” ያለውን ያስታወሱት አባ ኮራዶ፣ “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” የሚለውን የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ ምዕዳን በመጥቀስ፣ ይህም ለኤኳዶር ሕዝብ እና ለቤተ ክርስቲያኗ ወቅታዊ አጄንዳ መሆኑን አስረድተዋል። መሪ ሃሳቡ በኤኳዶር ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ለማሸነፍ፣ በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ባሕላዊ ዘርፎች መካከል ያሉ ግንኙነቶችን ለማጠናከር በአካባቢው ለሚደረገው ጥረት አስተዋፅኦን ለማድረግ ያለመ እንደሆነ፣ “ይህም ከቅዱስ ቁርባን ጭብጥ ጋር የተገናኘ በመሆኑ እራሳችንን እንደ እግዚአብሔር ልጆች፣ እንደ ወንድሞች እና እህቶች እንድንመለከት ይረዳናል” ብለዋል።

ከቅዱስ ቁርባን የሚገኝ ኅብረት

“ቅዱስ ቁርባን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የምንገናኝበት ዋስትና እንደሆነ እና ኢየሱስ ክርስቶስም ራሱን ከእኛ ጋር ያደረገበት፣ እኛም ከእርሱ ጋር የሆንንበትን ምስጢርን ያስታውሰናል” ብለው፣ “ዛሬም ቢሆን የኢየሱስ ክርስቶስ ሕያው አካል ለመሆን የተጠራንና ቅዱስ ቁርባንም ሕይወት ከኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እኛ የሚተላለፍበት መንገድ ነው” በማለት አስረድተዋል።

ዝግጅት በመካሄድ ላይ ይገኛል

የጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ምክር ቤት ግንቦት 15/2015 ዓ. ም. ከኪቶ ሊቀ ጳጳስ እና ከልዑካን ቡድኑ ጋር ባደረገው ስብሰባ የጉባኤውን ዓርማ እና መዝሙር በማቅረ ከማጽደቁ በተጨማሪ ሁሉንም የኤኳዶር እና የሌሎች አገራት ሀገረ ስብከቶችን የሚያካትት ዝግጅት በማድረግ የጉባኤውን መርሃ ግብር የሚገልጹ መመሪያችን በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። በተለያዩ የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች የተሰየሙት ልዑካን በመጭው መስከረም ወር የጉባኤውን ጠቅላላ አጀንዳ፣ ፕሮግራም እና የመገናኛ መንገዶችን ለማዘጋጀት በኪቶ እንደሚሰበሰቡ ይጠበቃል።

 

29 May 2023, 19:21